አብዱ ኪያር ዩሱፍ የተባለ ተከሳሽ በጳጉሜን 01 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡30 ሰዓት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ ቀርሳ ቢላ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የ17 ዓመት የሆነችውን የግል ተበዳይ ከእኔ ጋር በፍቅር ጓደኝነት ለመቀጠል ፈቃደኛ አልሆነችም በሚል ምክንያት መንገድ ላይ ጠብቆ አንገቷን አንቆ በመያዝ በአካባቢው ወደሚገኝ ካባ በሚወስዳት ጊዜ ላለመሄድ ስትታገለው በለበሰችው ልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ አንገትዋን አንቆ መሬት ላይ በመጣል በወደቀችበት የግብረ-ስጋ ግንኙነት ሊፈጽምባት ሲል የግል ተበዳይ ጩኸት ስታሰማ በድጋሚ በልብስ ማሰሪያው ጨርቅ አንገቷን አጥብቆ በመያዝና እራስዋን እንዳትከላከል በማድረግ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸመባት እና አንገቷን በእጅ እና በልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ በማነቅ ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕግ አንቀጽ 620(2)(ሀ) እና (3) መሠረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንደሌለው በመግለጹ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡