በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ 1ኛ አስጨናቂ ኃይሉ እና 2ኛ አስራት ኃ/ማርያም በተባሉ ግለሰቦች ላይ ፈጽመዋል ባለው ሀሰተኛ መንግስታዊ እና ሕዝባዊ ሰነዶች መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ችሎት ሁለት ክሶችን በዛሬው ዕለት መሰርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)፣የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(2)(ሀ) እና (3) ሥር የተደነገገውን እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 881/2005 አንቀጽ 33 እና አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) ሀ፣ለ፣ሐ እና (2) ሀ ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ሲል የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያመላክታል፡፡
የወንጀል አፈጻጸም ሂደቱን በተመለከተ የዐቃቤ ሕግ 1ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሹ በ12/02/2015 ዓ.ም በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ቡልጋሪያ ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት የግል ተበዳይ በአቶ መሀመድ ስንዴዉ ስም ከተከፈተ ተንቀሳቃሽ የሂሳብ ቁጥራቸዉ ላይ ቼክ ፈርመው ባልሰጡበትና ቸኩ ባልታወቀ መንገድ ከእጃቸው ተወስዶ ሀሰተኛ በሆነ ሁኔታ ተመሳስሎ በተፈረመ ቼክ ላይ 1,100,000 (አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ) ብር በካሽ እንዲከፈል በሚል በተዘጋጀዉን የቼክ ቅጠል አስጨናቂ ኃይሉ የተባለው ተከሳሽ በሕጋዊ ግብይት የተቀበለው አስመስሎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡልጋሪያ ቅርንጫፍ ቀርቦ በመመንዘር በቼኩ ላይ የተጠቀሰውን ብር ወደ ራሱ የንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲተላለፍ ያስደረገ በመሆኑ በፈጸመው በሀሰተኛ መንግስታዊ እና ሕዝባዊ ሰነዶች መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ 2ኛ ክስ የሆነውና በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የቀረበው የክስ መዝገብ ላይ የተመላከተው የወንጀል ድርጊት አፈጻጸምም ተከሳሾች ከላይ በ1ኛ ክስ በተገለፀው መልኩ በተመሳሳይ ቀን የሙስና ወንጀል የተፈጸመበትን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ለማቅረብ በማሰብ ወደ አንደኛ ተከሳሽ የሂሳብ ቁጥር ገቢ የተደረገው ገንዘብ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸ በራሳቸው ስምና በሌሎች ግለሰቦች ስም በተከፈቱ ተንቀሳቃሽ የሂሳብ ቁጥሮች የተለያዩ የማስተላለፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም 1ኛ ተከሳሽ ብሩን ያስተላለፈ በመሆኑ 2ኛ ተከሳሽም በቅርንጫፍ ባንኩ ከ1ኛ ተከሳሽ የተላለፈለትን ብር 100,000 (አንድ መቶ ሺ ብር) ወጪ አድርጎ ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ በአጠቃላይ ተከሳሾች በተመሳሳይ ቀን በተቀናጀ መልኩ በሙስና ወንጀል የተገኘውን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው ለማቅረብ በመስራታቸው በፈፀሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
የተከሳሾችን የዋስትና መብት በተመለከተ ዐቃቤ ሕግ የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትናን የሚያስከለክል መሆኑንና ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ ዋስትናቸው ተነፍጎ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ለችሎቱ አሳስቧል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው ችሎትም የ1ኛ ተከሳሽን የክስ መቃወሚያ ለመቀበልና ፖሊስ ሁለተኛ ተከሳሽን አስሮ እንዲያቀርብ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ውጤቱን ለመጠባበቅ ለመጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽም በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡