በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከ148 ሺ ብር በላይ ሀሰተኛ ገንዘቦችን ይዞ ተገኝቷል ባለው ግለሰብ ላይ ክስ መስርቶበት በ7 ዓመት ከ8 ወር እስራት እና በ1 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ አድርጓል፡፡
የክስ መዝገቡ እንደሚስረዳው ተከሳሽ ክንፈ አሰፋ በ1ኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ በኢትዮጵያ እንደ እውነተኛ ለማዘዋወር በማሰብ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ህጋዊ መገበያያ የሆነውን የኢትዮጵያ ብር ባለ የ100 እና 200 መቶ ብር ኖቶች፣ አጠቃላይ ብዛቱ 148 ሺ 500 ብር በሐሰት አዘጋጅቶ ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈጸመው ሀሰተኛ ገንዘብ ማዘጋጀት ወንጀል ተሰሷል፡፡
በተመሳሳይ በ2ኛ የዐቃቤ ሕግ ክስ ተከሳሽ በሕገ-ወጥ መንገድ ሊሰራበት በማሰብ ከተከሳሽ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ብርበራ ገንዘቦችን አስመስሎ ለመሥራት የሚያገለግሉ ኢፕሰን ብዛታቸው ሁለት የሆኑ ፕሪንተሮች፣ በተለያየ መጠን ተቆርጦ የተዘጋጀ የብር ኖቶች፣ ወረቀቶች፣ ዶክመንቶች እና የተለያየ አይነት ቀለም (ኬሚካሎች) ይዞ የተገኘ በመሆኑ በፈጸመው ሐሰተኛ ነገሮችን ለመሥራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎችና መስሪያዎችን ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ መመስረቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ ፈጣን የወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት ክሱን አልቃወምም ነገር ግን የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲል ክዶ የተከራከረ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ክሱ ላይ የተገለጸውን ፍሬ ነገር ያስረዳሉ ያላቸውን ማስረጃዎች በማቅረብ በበቂ ሁኔታ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ ሲያስረዳ ተከሳሹ በበኩሉ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ቀጠሮ መሠረት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ቢያቀርብም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ሊያስተባብል ባለመቻሉ ተከሳሹ ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል፡፡
ፍርድ ቤቱም መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት ተከሳሽ ጥፋተኛ በተባለባቸው በሁለቱም ክሶች መነሻ በማድረግ ሪከርድ ያልቀረበበት፣ የኩላሊት ህመም ያለበት፣ በልማት ስራዎች የሚሳተፍና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ፣ በድምሩ 4 የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ተይዘውለት በ7 ዓመት ከ8 ወር እስራትና በ1 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡