መድረኩ ከየካቲት 12 ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ አለምአንተ አግደው እንዲሁም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ፣ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ኢሳ ቦሩ እና ሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ሲሆኑ በንግግራቸዉም የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ መድብል በሀገራችን የሕግ ሥርዓት ትልቅ ፋይዳ ያለውና ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር እንደ ምሶሶ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለዉም ቀድሞ የነበረው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ በርካታ ችግሮች ያሉበትና ሳይሻሻል ለ60 ዓመት የቆየ መሆኑን ጠቁመው በአዲሱ መድብል ከዚህ ቀደም በሕግ ሥርዓቱ ያልነበረ የማስረጃ ሕግ እንዲካተት የተደረገ በመሆኑ በፍትሕ ሥርዓቱ እመርታ የተመዘገበበት ነው ያሉ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴ አባላት በመድብሉ የተካተቱ ጉዳዮችን በሚገባ አይተውና መርምረው በማጽደቅ ታሪካዊ ኃላፊነታቸዉን እንደሚወጡ ያላቸዉን እምነት ገልጸው የመድብሉ መጽደቅ ከዚህ ቀደም በፍትሕ ሥርዓቱ ጥያቄ እያስነሱ የነበሩ ጉዳዮችን ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ መድብል አስፈላጊነትና መሠረታዊ ጉዳዮችን በማሰመልከት የወንጀል ሥነ-ስረዓት እና የማስረጃ ሕግ ማስተባባሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት መሐቤና ሌሎች የአርቃቂ ቡድኑ አባላት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይም አሁን ባለንበት ዘመን ወንጀሎች ዓለም ዓቀፍ ገፅታን እየተላበሱ፣ በአይነታቸው፣ በብዛታቸው እና በአፈፃፀማቸው ውስብስብ እየሆኑ እንዲሁም በየጊዜውም ስልታቸውን አየቀያየሩ የሚፈፀሙ በመሆናቸው ይህን ለማጣጣምና የወንጀል ሕጉን በተሟላ ሁኔታ ለማስፈፀም የሚያስችል የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግና የማስረጃ ሕግ በማስፈለጉ ይህንን መድብል ለማርቀቅ ተችሏል ብለዋል፡፡
በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው ይህ የሕግ መድብል በውስጡ በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ፣ የፍትሕ አካላት ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት፣ ስለወንጀል ምርመራ ተግባራት፣ ስለማስረጃ አሰባሰብ፣ ስለዋስትና ጉዳይ፣ በምርመራ መዝገብ ላይ ስለመወሰን፣ ስለአማራጭ መንገዶች እንደ እርቅና ባህላዊ ሥርዓት እና ተለዋጭ መፍትሔዎች፣ ስለጥፋተኛነት ድርድር፣ ክስ የመመስረት ውሳኔ፣ ስለክርክር ሥነ-ሥርዓት፣ ስለዳኝነት ሥልጣን፣ ስለችሎትና ግልፅነት፣ ከፍርድ እና ከፍትሕ ሂደት ስለመነሳት፣ ስለመጥሪያ፣ የቅድመ ክስ ስለመስማት ተግባራት፣ ስለክርክር ሥነ-ሥርዓቶች፣ ክስ ስለመስማት፣ ስለፍርድና ቅጣት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስከበሩ ድንጋጌዎች የተካተቱ ስለመሆኑ በስፋት ተብራርቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱም በአርቃቂ ቡድኑ ከቀረበላቸው ማብራሪያ ተነስተው የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን የሕግ መድብሉን አርቅቆ አሁን ላለው ደረጃ እንዲደርስ ያደረጉ የአርቃቂ ቡድኑን አባላት እና ሚኒስቴር መስርያ ቤቱን አመስገነው ለሕግ መድብሉ መጽደቅ የበኩላቸዉን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በስተመጨረሻም በመድረኩ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው በቋሚ ኮሚቴ አባላትም ሆነ በአርቂ ቡድኑ የተነሱ ሀሳቦች እጅግ መሠረታዊ ነጥቦች መሆናቸንዉን በመግለጸ ይህንን ሕግ የማርቀቁ ሂደት ረጅም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ጸድቆ ስራ ላይ ሲዉል ትልቅ ጠቀሜታ ይዞ የሚመጣ ከመሆኑም በላይ አሁን በስራ ላይ ያለዉን አዲሱ የወንጀል ሕግና የወንጀል ፖሊሲን ለማስፈጸም የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና የማስረጃ ሕግ ተግባራዊ መደረጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡