በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀሎችን መከላከልና ተፈጽመው ሲገኙም ሕግ የማስከበርና እንዲከበር የማድረግ ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ተናገሩ
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ይህንን ያሉት ከመስከረም 13/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው የፌዴራልና የክልል ፍትሕ አካላት የውይይት መድረክ ላይ ሲሆን በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀል፣ አስከፊና ዜጎችን የሚያዋርድ እንዲሁም የሀገርን ክብር የሚነካ ነው ብለዋል፡፡
ወንጀሉን ለመከላከልም እንደ ሀገር ባለፉት ዓመታት ሕጎችን ከማሻሻል ጀምሮ ወንጀሎቹን በሚገባ ለመከላከልና ተፈጽመው ሲገኙም አጥፊዎችን ለማስቀጣት የተለያዩ አደረጃጀቶችን በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሠረት የተለያዩ ስራዎችን የሚተገብሩ አካላትን እንዲያስተባበር በተደራጀው ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ሥር በተዋቀረወ የወንጀል መከላከልና የሕግ ማስከበር ሥራ ቡድን በኩል የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡
ወንጀሎችን የመከላከልና ተፈጽመው ሲገኙም መርምሮ ሕግ እንዲከበር ማድረግ የፍትሕ ተቋማት ኃላፊነት መሆኑ ቢታወቅም ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ሀገራት ሪፖርት እየተገለጸ እንዳለው ወንጀሎቹን በመከላከልና ተፈጽመው ሲገኙም መርመሮ ጥፋተኞችን በማስቀጣት ረገድ ያለን ጥረት እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተመላክቷል ያሉ ሲሆን በዘርፉ እያስመዘገብን ያለው ውጤትም ከወንጀሉ ስፋትና እያስከተለ ካለው አሉታዊ ተጽዕኖ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
በመሆኑም በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በመገምገም ከዚያ በመነሳት ምንድነው ያልሰራነው/ምንድነው የጎደለን፣ የፍትሕ አካላትስ ሚናችንን እየተወጣን ነው ውይ የሚለዉን በሚገባ በመፈተሽ፣ በተለይ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያለን ኃላፊዎች የመሪነት ሚናችንን በአግባቡ በመወጣት ዜጎቻችንን ከአስከፊ እንግልትና የሰብዓዊ መብት ጥስት እንዲሁም የሀገራችን ክብር እንዲጠበቅ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይጠበቀብናል ብለዋል፡፡