በጠበቆች ፍቃድና አስተዳደር ህግ፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህግ እና የወንጀል ህግ ዙሪያ የተከናወኑ እና ሊከናወኑ ስለሚገቡ የማሻሻያ ስራዎች ዉይይት ተካሄዷል

Consultation Held on Reforms to Lawyers’ Licensing, Administration Law, Charity Organizations Law, and Criminal Code

ውይይቶቹ የተካሄዱት በባህርዳር የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የምክክር እና የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ ነው፡፡

በፌዴራል ደረጃ ተሻሽለዉ ወደ ስራ ከገቡ ህጎች መካከል አንዱ የሆነዉ የጠበቆች ፍቃድና አስተዳደር ሕግን ወደ ክልል በማዉረድ ማሻሻል የሚያስፈልግበት ዋና ዋና ምክንያቶችን በተመለከተ ዉይይት ተካሂዷል፡፡

የመወያያ ፅሁፉን ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄነራል አቶ በላይሁን ይርጋ ክልሎች አሁን እየተጠቀሙበት ያለዉን የጥብቅና አስተዳደር አዋጆች በመዳሰስ በአዋጆቹ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አንስተዋል፡፡

ቀጥለዉም በቀጣይ ህጎችን ሲያሻሽሉ ሊከተሏቸዉ በሚገቡ ጉዳዮችና የጥብቅና ዘርፍ እንዴት መመራት እንንዳለበት የሚያመላክቱ ሀሳቦችን አንስተዉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ከጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የጥብቅና ሕግ ማማከር አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከመፍታት አንጻር የጠበቆችን ሙያዊ ስነ ምግባር ከማረጋገጥ አንጻር መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮች አጽዕኖት ተሰጥቷቸው ሊታዩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የዉይይቱ ተካፋዮች የጠበቆች አስተዳደር አዋጆች ታሪካዊ ዳራን ጨምሮ ተያያዥ አበይት ጉዳዮች ለዉይይት መቅረባቸው ችግሮቹን ለይቶ ለተሻለ ስራ ለመዘጋጀት እንደሚያግዛቸዉና የተሸሻለዉ የጠበቆች አስተዳደር አዋጅም እንደ ትልቅ መነሻ እንደሚሆናቸዉ ገልፀዉ የፌዴራሉ አዋጅ ሲሻሻል ያልታዩና አሁን በክልሎች አዋጁ ሲሻሻል መታየት የሚገባቸዉ ጉዳዮች ካሉ የሚሉና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችንና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

ከተወያዮች ለተነሱ ጥያቄዎች የጽሁፉ አቅራቢ አቶ በላይሁን ይርጋ ምላሽ የሰጡ ሲሆን የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደዉ ዉይይቱን ሲያጠቃልሉ እንዳሉት ክልሎች የጠበቆች አስተዳደር አዋጅን ሲያስቡ በዋናነት አገልግሎቱን እንደ አንድ ትልቅ ተቋም መቁጠር እንዳለባቸዉና የፍትሕ ጥያቄዎችን የሚመልስ በህብረተሰቡ ማኅበራዊ ህይወት ትልቅ ቦታ ያላቸዉ መሆኑን ታሳቢ ከማድረግ በተጨማሪ በጥብቅና አገልግሎቱ አሰጣጡ ያለዉን መተማመን ለመገንባት ጠበቆች ራሳቸዉን በራሳቸዉ ማስተዳደር መቻላቸዉ አንደኛዉና ዋነኛዉ መፍትሄ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ጠበቆች ራሳቸዉን ማስተዳደር ሲችሉም ከስነ ምግባርም ሆነ ከአቅም የሚነሱ ክፍተቶችን ኃላፊነት በመዉሰድ ማህበሩ ራሱን በራሱ እያበቃ የሚሄድበትን እድል እንደሚፈጥርና በቀጣይም አገልግሎቱ እየተስተካከለ ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታ የጠቆሙ ሲሆን ክልሎችም የጀመሯቸዉን የማሻሻያ ስራዎች አጠናክረዉ እዲቀጥሉና በማንኛዉም ሕግ ዝግጅት ተገቢውን እገዛ ለማድረግ ፍትሕ ሚኒስቴር ዝግጁ መሆኑን ለመድረኩ ተሳታፊዎች ገልፀዉላቸዋል፡፡

በመድረኩ በወንጀል ሕግ ውስጥ መሻሻል ስላለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች በሕግ ምሁሩ አቶ ወርቁ ያዜ፣ የበጎ አድራጎት አዋጅ ሕግ ማሻሻያን በተመለከተ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ መነሻ ጽሁፍ አቅራቢነት እንዲሁም በአቶ መርሃጽድቅ መኮንን እና በአቶ አብራሃም አያሌው አወያይነት ጥልቅ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡

Tagged Under: Charity Law Criminal Code Legal Reform
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች