የምስራቅ አፍሪካ የግልግል ዳኝነት ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ ዉስጥ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረዉ ተጠቆመ

Hosting the East Africa Arbitration Conference in Ethiopia Highlighted as Having Multifaceted Benefits

11ኛዉ የምስራቅ አፍሪካ የግልግል ዳኝነት ኮንፈረንስ በዛሬዉ እለት በአዲስ አበባ መካሄድ መጀመሩን ተከትሎ በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን በኮንፍረንሱ የመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደተናገሩት ኮንፈረንሱ በአገራችን መካሄዱ በተለይም በዘርፉ ወደፊት ሊከናወኑ የታቀዱ ተግባራትን ለማከናወን የሚኖረዉ ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሃብሄር ፍትሕ አስተደደር ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ንጉሴ ትዛዙ በበኩላቸው የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ የግልግል ዳኝነትን በአፍሪካ ማሳደግ ሲሆን በተጨማሪ አገራችን ለግልግል ዳኝነት ማእከልነት ምቹ መሆኗን ማስተዋወቅን ያለመ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት የሕግ ማዕቀፍ፣ በቂ የሕግ ባለሙያዎች መኖር እንዲሁም የኢትዮጵያ የአየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች አስቻይ የሆኑ መሰረተ ልማቶች መኖራቸዉን ለታዳሚዎች ከማሳወቅ በተጨማሪ የግልግል ዳኝነትን የሚመለከተዉን የኒውዮርክ ኮንቬንሽ ስምምነት መፈረሟ ደግሞ የበለጠ ተመራጭ የግልግል ዳኝነት ማእከል መዳረሻ መሆን እንደምትችል ለማሳየት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አቶ ንጉሴ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ተግባር ጋር በተያያዘ በአገር ዉስጥ የሚገኙ የግልግል ዳኝነት ማእከላትን ለመመዝገብና ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ዓለም ዓቀፍ ማእከላትም በአገራችን የግልግል ዳኝነት ቢሮ ከፍተዉ እንዲሰሩ ለማድረግ ኮንፈረንሱ እድል ይሰጣል ሲሉ አክለዋል፡፡

በዚህ ሂደት በኮንፈረንሱ ከተሳታፊ የሆኑ በርካታ ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ማእከላት እንዳሉና ለአብነትም ለንደን ኮርት ኢንተርናሽናል አርቢትሬሽን ጋር ወደ አገራችን መጥተዉ እንዲሰሩ ለማድረግ ጎን ለጎን ዉይይቶች መካሄዳቸዉንና በተጨማሪም በአቅም ግንባታ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርጉ ከአፍሪካን ኢንሸቲቭ ፎር ሌጋል ሳፖርት ጋር መነጋገር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም የፍትሕ ዘርፍ የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ፍኖተ ካርታ ዉስጥ ካሉ አምዶች ኢትዮጵያ ዉስጥ የግልግል ዳኝነት ማእከል እንዲኖር ማድረግ አንዱ መሆኑንና ይህንን ለማሳካትም ኮንፈረንሱ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ተገልዖል፡፡

ኮንፈረንሱ በሁለት ቀናት ቆይታዉ በተለይም አፍሪካ የጀመረቻቸዉን ለዉጦች አለም ከደረሰበት የቴክኖሎጅ ለዉጥ ጋር እንዴት ማጣጣም እደሚያስችልና አረንጓዴ ልማት ጋር ተከትሎ የሚመጡ ልማቶችን በግልግል ዳኝነት እንዴትና በምን መልኩ ከአሁናዊ ለዉጦች ጋር ማስተሳሰር በሚቻልባቸዉ ሁኔታዎች ላይ ትኩረታቸዉን ያደረጉ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዉ ዉይይት የሚደረግበትና የቤት ስራ የሚወሰድበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የግልግል ዳኝነት የንግድ ነክ አለመግባባቶች በሚከሰቱበት ጊዜ ሰዎች ከመደበኛዉ ፍርድ ቤት ዉጭ ካሉ አማራጭ አለመግባባት መፍቻ መንገዶች ዉስጥ አንዱ ሲሆን ተዋዋይ ወገኖች በሚመርጡት ዳኛና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች አማካኝነት አስገዳጅ ዉሳኔ የሚሰጥበት የፍትሕ ሥርዓት ነዉ፡፡

ኮንፈረንሱን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከ I-Arb Africa በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን፣ የማላዊ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ታህቦ ቻካካን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣የመንግሥት ባለድርሻ አካላት፣የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

Tagged Under: addis ababa adr african alternative alternative dispute resolution (adr) Arbitration Capacity Building commercial commercial arbitration conference dispute Dispute Resolution east framework i-arb africa Infrastructure Development international International Arbitration Investment investment arbitration legal legal framework Legal Professionals Legal Reform new york convention reform resolution transformation plan
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች