የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 58ኛው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የከፍተኛ ደረጃ መድረክ ጎን ለጎን ከተለያዩ አባል ሀገራት እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ከነዚህ ውይይቶች መካከል ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚስተር ቮልከር ቱርክ ጋር ያደረጉት ውይይት ይገኝበታል።
ክብርት ወ/ሮ ሀና ከከፍተኛ ኮሚሽነሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ስርዓቶች ውስጥ በምታደርገው ተሳትፎ የኮሚሽነሩ ድጋፍ ተነጥሎን አያውቅም ካሉ በኋላ በተለይም ከወራቶች በፊት ሀገራችን ባቀረበችው የሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ መድረክ ሀገራዊ ሪፖርት ዝግጅት ወቅት ለተደረገው ሙያዊ ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመድረኩ 316 ምክረ ሀሳቦች እንደተሰጧት አስታውሰው በቀጣይ ምክረ ሀሳቦቹን ለመተግበር ተገቢው ጥረት እንደሚደረግ ገልጸው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤቱ የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ አያይዘውም መንግሥት ያለፉትን በደሎች እነ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ፤ እንዲሁም መሠረታዊ ልዩነቶችን ደግሞ በሀገራዊ ምክክር እልባት ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተው ነጻ እና ገለልተኛ የሽግግር ፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችም በመዘጋጀት ላይ እንደሆኑ ገንጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ስርዓት ውስጥ በንቃት ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው በሁሉን አቀፍ ሰብዓዊ መብት ግምገማው ላይ የተሰጧትን ምክረ ሀሳቦች በአብዛኛው ተቀብላ እንደምትተገብር አምናለው ብለው ቢሯቸው በትግበራ ምዕራፉም ኢትዮጵያን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።