በሐሰተኛ ቼክ ከባንኩ ደንበኛ እውቅና ውጪ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ባስተላለፉት የአትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ሥ/አስኪያጅን ጨምሮ በ4 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

Four Accused, Including CBE Customer Service Manager, Charged with Aggravated Corruption for Transferring Over 5 Million Birr via Forged Check Without Customer Authorization

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በሐሰተኛ ቼክ ከባንኩ ደንበኛ እውቅና ውጪ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ባስተላለፉት የአትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ሥ/አስኪያጅን ጨምሮ በ4 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሰረተባቸው፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ ሳምሶን ተከስተ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እህል ዴፖ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን፣ 2ኛ አንተነህ ነጋሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አየር አምባ ሚካኤል ቅርንጫፍ የፊት የደንበኞች ግንኙነት ባለሙያ፣ 3ኛ አልማዝ ክንፉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አየር አምባ ሚካኤል ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥ/አስኪያጅ፣ 4ኛ ተስፋዬ ለታ በግሉ የሚሰራ ሲሆን፣ በ4 ተከሳሾች ላይ የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ ሶስት ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡

1ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን ተከሳሹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እህል ንግድ ቅርንጫፍ በፊት የደንበኞች ግንኙነት ባለሙያነት ሲያገለግል በነበረበት ወቅት የማይገባ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በባንኩ የተጣለበትን የስራ ምስጢር ያለአግባብ መጠቀም እንደማይቻል የተደነገገውን ድንጋጌ እና በባንኩ የአሠራር መመሪያዎች የተጣለበትን የደንበኞችን መረጃ የመጠበቅ ግዴታ በመጣስ በባንኩ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ደንበኛ Food for Hunger Ethiopia (FH Ethiopia) የሂሳብ ቁጥር የፈራሚዎችን ዝርዝር ሁኔታ እና የፊርማ ናሙናዎች ከባንኩ የT-24 የኮምፒዩተር መረጃ ሲስተም ላይ በመውሰድ በመኖሪያ ቤቱ ካስቀመጠበት ሀምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ በ7፡00 በፍ/ቤት በተሰጠ የብርበራ ትእዛዝ አማካኝነት ታዛቢዎች በተገኙበት ቤቱ ሲበረበር የፊርማ ናሙናዎቹን የያዙት ሰነዶች በመገኘታቸው በፈጸመው በስራ ተግባር የሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡

በተመሳሳይ 2ኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 3ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆነው 4ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በሀሰተኛ ቼክ የባንኩን መመሪያ በመጣስ ቼኩ የተቀነሰበት ሂሳብ ባለቤት ለሆኑት ተበዳይ ስልክ ሳይደውሉ እና Post No Debit ክፍያ እንዳይከፈል በሲስተም ላይ የታሰረውን እግድ በመጣስ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ ለ4ኛ ተከሳሽ በስፔሻል ክሊራንስ አማካኝነት በሀሰተኛ ቼኮች 5 ሚሊዮን 334 ሺ ብር በማስተላለፍ በዚሁ ልክ ጉዳት እንዲደርስ እና ለራሳቸው ያልተገባ ጥቅም እንዲውል ያደረገ በመሆኑ በፈጸሙት የከባድ በሥልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

3ኛ ክስ በ4ኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን ተከሳሹ ከላይ በአንደኛ ክስ በተጠቀሰው አመንጪ ወንጀል የተገኘውን ብር 5 ሚሊዮን 334 ሺ ብር በጥሬ ገንዘብ ወጪ በማድረጉና ወደ ተለያዩ ሰዎች በማስተላለፉ በፈጸመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሷል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ቀርበው ክሱ ደርሷቸው ከጠበቃ ጋር ሲቀርቡ ክስ ለመስማት ለመጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም እና እንዲሁም 1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችን ፖሊስ እንዲያቀርብ ለሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Tagged Under: aggravated corruption • bank • bribery • cbe • charges • commercial • commercial bank of ethiopia • Corruption • court • court case • Crime • criminal • Criminal Charges • embezzlement • Federal High Court • financial • Financial Crime • Forgery • Fraud • laundering • Legal Proceedings • lideta branch • misappropriation • money • Money Laundering • Theft
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች