ግለሰባዊ ግንኙነቶችን እና መብቶችና ግዴታዎችን (private relationships, rights and obligations) የሚደነግገውንና የሚገዛውን እንዲሁም የንብረት፣ የውል፣ የቤተሰብ፣ የውርስ፣ ከውል ዉጭ ኃላፊነትን እና የመሳሰሉትን ሕግጋት አካትቶ የሚይዘውን የፍትሐ ብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ለማስቻልና በተቀናጀ መልኩ የለውጥ ስራ እንዲሰራ የሚያግዝ የፍትሐ ብሄር ፍትሕ አስተዳደር ፖሊሲ ለማርቀቅ የሚያስችል ጥናት የማከናወን ስራ ተጀምሯል፡፡
ጥናቱ ለረዥም አመታት በስራ ላይ የቆዩትን የዘርፉን ሕግጋት፣ አተገባበራቸውን እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ሀገራዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ለውጥ የሚዳስስ ሲሆን ፖሊሲውን ለማርቀቅ የሚረዱ ምክረ ሀሳቦችን አጎልብቶ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
በጥናቱ ውጤት መነሻነት የሚረቀቀው ፖሊሲም የፍትሐ ብሄር ክርክር ስርዓቱን፣ የአማራጭ የግጭት መፍቻ አተገባበርን፣ ነጻ የሕግ ድጋፍን፣ የፍትሐ ብሄር ሕግጋት መሻሻልን፣ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ማዘመንን እና የመሳሰሉትን ወሳኝ እና አስቻይ ነጥቦችን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡ የፖሊሲው መዘጋጀት ከዚህ ቀድሞ ወጥ እና የተጠና አሠራር ስርዓት ባልነበረበት ሁኔታ ያገጥም የነበረውን ችግር ከመፍታትም በዘለለ ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ በመርህ የሚመራ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን የህዝቦች ተጠቃሚነትንም የሚያሰፋ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የመንግሥት ተቋማትን የፍትሐ ብሄር ክርክር ተጋላጭነት መንስዔዎችን ቀድሞ ለማወቅ እና ለመከላከል የሚረዳ የአሠራር ስርዓት በጥናት ላይ በመመስረት የመዘርጋት ስራም ተጀምሯል፡፡ ይህ የአሠራር ስርዓት የመንግሥት ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ሲያጋጥሟቸው በነበሩ የፍትሐ ብሄር ክርክር ጉዳዮች ምክንያት ሲባክን የነበረን ከፍተኛ ሀብት የሚያድን ከመሆኑም በላይ ተቋማቱ በሕግ በተቋቋሙለት ዓላማ ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳል ተብሏል፡፡
ሁለቱም ጥናቶች በፍትሕ ሚኒስቴር እና በዩ ኤስ ኤይድ ፍትሕ ፕሮጀክት ትብብር የሚከናወኑ ሲሆን በጥናቶቹ ሂደት ውስጥ በዘርፉ የላቀ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡ በስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ በተቋሙ የፍትሔብሄር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ሄኖክ ተስፋዬ፣ በዩ ኤስ ኤይድ ፍትሕ ፕሮጀክት የስራ ሃላፊዎች እና ጥናቱን የሚመሩት ባለሙያዎች ጥናቶቹን በተመለከተ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በስተመጨረሻም የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በመድረኩ ተገኝተው የስራ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ በዚሁም የጥናቶቹ ዝግጅት በይፋ ተጀምሯል፡፡