በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ በተከሳሾችና ምስክሮች አለመቅረብ ጋር ተያይዞ በሚቋረጡ መዛግብት ዙሪያ በመምከር በቀጣይ ሊቀመጡ የሚገባቸዉን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ዉይይት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችና አባላት ጋር በዛሬዉ እለት አካሂዷል፡፡
ዉይይቱን በንግግር የከፈቱት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ በተከሳሽና ምስክር አለመቅረብ ምክንያት የሚቋረጡ መዛግብትን አስመልክቶ ማነቆዎቹን በመፍታት ችግሩን ለመቅረፍ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የሆኑ ዉይይቶች ከድሬድዋ ፖሊስ ጋር መካሄዱንና በዛሬዉ እለት ደግሞ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመነጋገር ያሉ አጠቃላይ የምርመራ ስራዎችንና አሰራሮችን እንዲሁም አፈፃፀሞችን ተመልክቶ በቀጣይ መፍትሄ ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
ቀጥሎም በተከሳሽና ምስክር አቀራረብ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችና ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ ርምጃዎች በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍና ዳሰሳዊ ጥናት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን ፣እንደሳቸዉ ገለፃ የፍትሕ ስርአቱ ጠንካራ እንዲሆንና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ምስክሮችና ተከሳሾች በሚፈለገዉ ደረጃ መቅረብ እንደሚገባቸዉ ገልጸዉ ይህ ካልሆነ ግን የፍትሕ ስርአቱን አደጋ ላይ ከመጣሉ በተጨማሪ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ችግር እንደሚሆን አዉስተዋል፡፡
አያይዘዉም ባለፉት ዘጠኝ አመታተ ከ76 ሺህ በላይ መዛግብት ተከሳሾችና ምስክሮች ባለመቅረባቸዉ የተዘጉ መሆናቸዉን የተካሄደዉ ጥናት ማመላከቱን ገልፀዉ ለነዚህ መዛግብት መቋረጥ የፍርድ ቤት፣የዓቃቤ ሕግ፣የፖሊስና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች መኖራቸዉን በስፋት ካብራሩ በኋላ ለችግሮቹ መፍትሄ ናቸዉ ያሏቸዉን ሀሳቦችም አንስተው በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የሕግ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ልኡል ካህሳይ በበኩላቸዉ በተለያዩ ምክንያቶች የሚዘጉና የሚቋረጡ መዛግብት አፈፃፀምን አስመልክቶ ባቀረቡት ጽሑፍ የሚዘጉና የሚቋረጡ መዛግብት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸዉንና ለዚህም ምክንያት ናቸዉ እንዲሁም ማሳያ ይሆናሉ ያሏቸዉን ሀሳቦች አብራርተዋል፡፡
የዉይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸዉ ለዉይይት የቀረቡ መረጃዎች የሁሉንም ችግር በትኩረት የዳሰሱ መሆናቸዉ ችግሩን ተገንዝቦ ለማስተካከል የሚኖረዉ ሚና የጎላ መሆኑን በመግለፅ ሁሉም ባለድርሻ አካል የተሰጠዉን ኃላፊነት በመወጣት ምስክርና ተከሳሽ ባለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብትን ቁጥር ለመቀነስ ልንሰራ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ በበኩላቸዉ ለተከሳሽና ለምስክር አቀራረብ የሚሰጡ ትኩረቶች ዝቅተኛ መሆናቸዉንና ለዚህም ደግሞ በጊዚያዊና በወቅታዊ ስራዎች መወጠር ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑና ነገር ግን ኃላፊነት ወስዶ ለስራዉ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ በቀጣይ መሰራት የሚገባቸዉን ስራዎች አስመልክተዉ በሰጡት የስራ አቅጣጫ በተለይም በዓቃቤ ሕግና በፖሊስ የስራ ጥምረት ያሉ ሁኔታዎች በደንብ ሊታዩ ይገባል ካሉ በኋላ የጋራ የሆኑ አሠራርና ማንዋሎችን በማዘጋጀትና በየጊዜዉ እየተነጋገሩ በመሥራት በተከሳሽና በምስክር አለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ለመቀነስ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡