በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በአዲስ አበባ የሚገኙ 11 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም ድሬዳዋ እና ሀዋሳን ጨምሮ በ2016 በጀት ዓመት እቅድ የ9 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የጽህፈት ቤቶቹ የስራ ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች በተገኙበት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱ ሁሉም ጽህፈት ቤቶች ያላቸውን የአፈፃፀም ቁመና መዝነው በቀጣዮቹ ወራት የበለጠ ተግተው በመሥራት የበጀት ዓመቱን በላቀ አፈፃፀም ለማጠናቀቅ የሚችሉበትን አጋጣሚ የሚያገኙበት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ባለፉት 9 ወራት የወንጀል ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ አቅምንና ተደራሽነትን ከማሳደግ አንፃር የወንጀል ምርመራ መዛግብት ውሳኔ የመስጠት ወይም የማጥራት ምጣኔን ወደ 95% ለማሳደግ ታቅዶ በዚሁ ረገድ መወሰን ካለባቸው 35,069 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ በ34,548 (98.5%) መዝገቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ መስጠቱ ተመላክተዋል፡፡ ውሳኔ በመስጠት ረገድም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ 9 ወራት ውስጥ ከነበረው አፈፃፀም በተሻለ የ12,086 ተጨማሪ መዛግብት ላይ ውሳኔ መሰጠቱንና የውዝፍ ምጣኔውንም ከ5.3% ወደ 1.5% ማውረድ መቻሉን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
የወንጀል ክሶችን የመርታት ምጣኔን በሚመለከት በአጠቃላይ በሁሉም መዛግብት የመርታት ምጣኔ በተከሳሽ 92% እንዲሁም በመዝገብ 95% ለማድረስ ታቅዶ በክርክር ላይ ከነበሩት 28,682 መዛግብት እና 33,290 ተከሳሾች ውስጥ ፍርድ ቤት በ9,389 መዛግብት እና በ11,563 ተከሳሾች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ9,120 መዛግብት እና በ11,205 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት እንዲሁም በ269 መዛግብት እና በ358 ተከሳሾች ላይ ነፃ በሚል ፍርድ የሰጠ ሲሆን አፈፃፀሙ በመዝገብ 97.13% በተከሳሽ ደግሞ 96.9% ሆኖ በአማካይ አፈፃፀሙን 97.02% በማድረስ ከዕቅድ በላይ መፈፀም እንደተቻለ ተመልክቷል፡፡
የላቀ የፍትሕ አገልግሎትን ከመስጠት አኳያ በበጀት ዓመቱ 9 ወራት በአጠቃላይ 1,177 ዜጎች በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀርበው በሁሉም ጥያቄዎች ላይ በስታንዳርዱ መሠረት 100% የሕግ ምክር አገልግሎት እንደተሰጠ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
የፍትሐ ብሔር የቀጥታ ክስ ክርክር አፈፃፀምን 96.5% ለማድረስ ታቅዶ በቀጥታ ክስ በክርክር ላይ ካሉ 226 የቀጥታ ክሶች ውስጥ ፍርድ ቤት በ95 መዛግብት ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ዐቃቤ ሕግ በ85 መዛግብት ላይ በመርታት አፈፃፀሙን 91.5% ማድረስ መቻሉን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ክርክር አፈፃፀምን 90% ለማድረስ ታቅዶ በክርክር ላይ ከነበሩን 17 መዛግብት መካከል በ9 ወራት ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት በ9 መዛግብት ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ዐቃቤ ሕግ በ8 መዛግብት ላይ በመርታት አፈፃፀሙን 88.9% እንዲሆን ማድረጉን፤ ከዚህ በተጨማሪ ዐቃቤ ሕግ መልስ ሰጪ የሆነባቸው የይግባኝ መዘግብት ክርክር አፈፃፀምን 80% ለማድረስ አቅዶ በክርክር ላይ ከነበሩ 19 መዛብግት ውስጥ ፍርድ ቤት በ12 መዛገብ ላይ ውሳኔ በመስጠቱ በውሳኔው ዐቃቤ ሕግ በመርታት አፈፃፀሙን 100% ማድረስ መቻሉ ታውቋል፡፡
የሰብዓዊ መብት የማክበርና የማስከበር አፈፃፀምን ለማሳደግ በ9 ወራት በተከናወኑ ተግባራት መሠረት በአጠቃላይ ለ15,316 ተጠርጣሪዎች እና ድሬ ዳዋ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ጉብኝት በማድረግ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ መስጠት ወይም እንዲሰጥ የማድረግ ስራ መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ሌላ ከተመረጡ የሕዝብ እና ሲቪል ማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር በየሩብ ዓመቱ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ዕቅድ እና አፈፃፀም ላይ ውይይት የማድረግ እና የንቃተ ሕግ ሥልጠናዎችን በመስጠት ህብረተሰቡን በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የማሳተፍ ስራዎች መከናወናቸው ታውቋል፡፡
እነዚህን እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ያካተተው ሪፖርት በዝርዝር ከቀረበ በኋላ ባደረጉት ውይይት በጎ አፈፃፀሞችን በማጠንከር የተስተዋሉ ክፍተቶችን ደግሞ አስተካክሎ ወደ ፊት ለመቀጠል የሚያስችሉ ገንቢ ሀሳቦች ተነስተው አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል፡፡