መሃመድ ፈረጃ ምራ የተባለ ተከሳሽ ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራንዬ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ቤቴል ወይራ ሰፈር አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በር ላይ የትዳር አጋሩ የሆነችውን የግል ተበዳይ ሀሰነት ሰኢድ መኪና ውስጥ ተቀምጣ እያለ ሌላ ባል አግብተሽ ልጆቹን ይዘሽ ወደ ውጪ ልትሄጂ ነው በሚል ምክንያት ቆራርጨ ነው የምጥልሽ እያለ እጁን ወደ መኪናው ጋቢና በማስገባት እንዳትጮህ አፏን ካፈናት በኋላ ከተር እየተባለ በሚጠራ ስለታማ የምንጣፍ መቁረጫ የተለያዩ የሰውኑት አካሏን በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ከመኪና ውስጥ ጎትቶ በማውረድ መሬት ላይ ጥሏት በወደቀችበት በያዘው ስለት ጀርባዋን እና ትከሻዋን ደጋግሞ በመውጋት የግድያ ሙከራ በማድረስ ወንጀል፤
በተጨማሪም በታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9፡30 ከላይ በተጠቀሰው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የ15 ዓመት የሆነችው ልጁ ከት/ቤት ስትመለስ አርፍደሻል በሚል ምክንያት በመጥረጊያ እንጨት እና በመጋረጃ መስቀያ ብረት ደጋግሞ በመምታት እጇ፣ ጭንቅላቷ እና እግሯ እንዲያብጥ በማድረግ እንዲሁም በነሀሴ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢም ይህች የ15 ዓመት የሆነችው ልጁ ያለምንም ምክንያት በኤሌክትሪክ ገመድ ጀርባዋ እና እግሮቿን ደጋግሞ በመምታት ጀርባዋ እና እግሮቿ እንዲቆስሉና እንዲያብጡ በማድረግ ከተሰወረ በኋላ በክትትል ተይዞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕ/አ በ27/1/ እና 539/1/ሀ/ እንዲሁም በወ/ሕ/አ 556/2/ሀ እና /ሐ/ ላይ በተደነገገው መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡