በፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ባለፉት ስድስት ወራት የተሸለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገለጸ ሲሆን የስራ ክፍሉ ባሉት ሦስት ማስተባበሪያዎች አማካኝነት በርካታ የምርመራና ክስ ስራዎችን ማከናወኑን አሳውቋል፡፡
ከስራ ክፍሉ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ማብራሪያ የሰጡት የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ዘላለም ፍቃዱ ሲሆኑ የስራ ክፍሉ በ2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያዉ ስድስት ወራት ዉስጥ 897 የምርመራ መዛግብት ለዉሳኔ ቀርበዉለት የነበረ መሆኑን በማስታወስ በ602 መዛግብት ላይ ዉሳኔ የተሰጠ መሆኑን ተናግረው በቀሪ 295 መዛግብት ላይ ደግሞ በቀጣይ ዉሳኔ የሚሰጥባቸዉ መሆኑን ግለጸዋል፡፡
በስድስት ወራት ዉስጥ በተከናወነው ስራ በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠባቸው ተከሳሾች ላይ ከተወሰነባቸው የእስራት ቅጣት በተጨማሪም 655,500.00 የገንዘብ መቀጮ የተጣለባቸው ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለረዥም ጊዜ ዉሳኔ ሳያገኙ በዐቃቤ ሕግና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተከማቹ ዉዝፍ የሙስና ወንጀል መዛግብትን ትኩረት ሰጥቶ ማጥራት ይቻል ዘንድ ፕሮጀክት ቀርጾ በንቀሳቀስ በተለይ ዐቃቢያነ ሕግ በክረምት ወራት ጊዜያቸዉን እዚሁ ስራ ላይ እንዲያዉሉት በመደረጉ በርካታ ውዝፍ መዛግብትን ማጥራት ተችሏል፣ ቀጣይ ለሚሰራው የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ሥራም ያለንን የሰው ኃይል በማሰማራት ውጤታማ ስራ ለማከናወን የሚያስችለን ይሆናል ብለዋል፡፡
አቶ ዘላለም የስራ ክፍሉን አሠራር ውጤታማ ለማድረግና ተንሰራፍቶ የሚታየዉን የሙስና ወንጀል መቀነስ እንዲያስችል የሙስና ወንጀል መረጃ ከማግኘት ጀምሮ አጠቃላይ ምርመራና ክስ የሚመራበትን ስርዓት ለመዘርጋት የስትራቴጂ ሰነድ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚፈለገው መጠን ዳብሮና የባለድርሻ አካላትን ሚና አካቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በስድስት ወር ውስጥ በተለይ በሙስና ወንጀል አድራጊነት በተጠረጠሩ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እንዲሁም ግብረአበሮቻቸው፣ ህገ-ወጥ የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ 16.5 ሚሊዮን ብር የሚሆን ህገ-ወጥ ካሳና መሬት በወሰዱ የወረዳ ኃላፊዎችና ግብረአበሮቻቸው፣ የልማት ተነሺ ባልሆኑና የአከባቢው ነዋሪ ባልሆኑ 21 ሰዎች ስም 67 ሚሊዮን ብር ካሳ ተቀብለው ለግል ጥቅማቸው የዋሉ ተከሳሾችና ግብረአበሮቻቸው ተይዘው የሙስና ወንጀል የማጣራት ሥራ እየተሰራ ከመሆኑም በተጨማሪም ከብድር መያዣና ዋስትና ጋር በተያያዘ በተፈጸመ የሙስና ወንጀል የ290 ሚሊዮን ብር ህገ-ወጥ ድርጊት ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ሰነዶችን በሐሰት በማዘጋጀትና በመገልገልም እስከ 1.5 ቢሊዮን ብር ለመውስድ ሙከራ ያደረጉ አጥፊዎች ላይ ከበድ የሙስና ወንጀል ክስ የመመስረት ሥራ የተሰራ ሲሆን በባንኮች ላይ ከሚፈጸም ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ የተመዘበረ በመሆኑ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ዉሳኔ አግኝቶ አጥፊዎች እስከ 18 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ስለመደረጉ አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡
አቶ ዘላለም በተለይም ከሙስና ተግባር ጋር ተያይዞ ዜጎች ገንዘብ ካልከፈሉ በስተቀር መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት አለመቻል፣ የመሬት ሙስናና የካሳ ክፍያ፣ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ምዝበራ፣ ሀሰተኛ መንግሰታዊ ሰነዶችን ማዘጋጀትና መገልገል፣ ከባድ ማታለል፣ ጉቦ መጠየቅና መቀበል እንዲሁም ህገ-ወጥ እስርን በመፈጸም ገንዘብ መቀበልን የመሳሰሉ የሙስና ወንጀሎች በስፋት እየተፈሙ መሆናቸው በመረጋገጡ በቀጣይ ስድስት ወራት ከሙስና ወንጀል ጋር ተያይዞ የሕግ ማስከበር ስራው ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሙስናን ወንጀል ከማጋለጥና መረጃ ለሕግ አስከባሪ አካላት ከማቅረብ ረገድ የሚቀርቡ ጥቆማዎች ብዛትና ጥራት በቂ ባልመሆኑ ምቹ፣ ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀና ተደራሽ የመረጃ መቀበያ ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ይገኛል ያሉ ሲሆን የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት በተለይም የመንግሥት ተቋማት አሰራሮች ላይ ሥልጠና መስጠት፣ የወንጀል ምዝገባ ስርዓት ማሻሻል፣ ወንጀሉ በስፋት ይታይባቸዋል ተብለው በተለይ ተቋማትና የአገልግሎት አይነቶች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ በኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለሕግ ማቅረብ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራባቸውና በተለይም ከፌዴራል የሥነ-ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን እንዲሆም ከፌዴራል ዋና ኦዲተርና እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለዉን ቅንጅታዊ አሠራር የማጎልበት ተግባር በትኩረት ይሰራል ብለዋል ፡፡