በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ የቅርንጫፍ ባንኩን መመሪያ እና አሠራር በመጣስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላይ 3 ሚሊዮን 900 ሺ ብር ጉዳት እንዲደርስበት ያደረገው የየረር በር ቅርንጫፍ የባንኪንግ መኮንን ላይ በሥልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶበታል፡፡
ተከሳሽ ዮናታን ወንዳፈር በአትዮጵያ ንግድ ባንክ የረር ቅርንጫፍ የቅርንጫፍ ባንኪንግ መኮንን ሲሆን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ለ/ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 9/1/ሀ/ እና /2/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶበታል፡፡
በዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር ላይ ተከሳሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የረር በር ቅርንጫፍ የባንኪንግ መኮንን ሆኖ ሲያገለግል የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በአንድ ድርጅት መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን፣ ለቅርንጫፍ ባንኩ በተሰጠው ሚና እና ተግባር ብቻ መሰራት እንዳለበት የሚደነግገውን የባንኩን መመሪያ እና አሠራር በመጣስ የተሰጠውን ሥልጣን ወይም ኃላፊነት በግልጽ ተግባር ያለአግባብ በመገልገል፤
ተከሳሽ በሚሰራበት የረር ቅርንጫፍ ሊንቀሳቀስ የማይገባን ሂሳብ እ.አ.አ. 18/9/2023 ላይ ከሂሳቡ ባለቤት/ደንበኛ ፈቃድ፣ እውቅና እና ሂሳቡ ከተከፈተበት ዓላማ ውጪ፣ ያለዝውውር ሰነድ ከሂሳቡ ላይ 3 ሚሊዮን 900 ሺ ብር ተከሳሽ በሚጠቀምበት የኮምፒዩተር መለያ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሆኑት ላይ የቲ-24 የሲስተም መግቢያ ፈቃድ ከእውቅናቸው ውጪ በመጠቀም ከሂሳቡ ላይ ይህን ገንዘብ ተቀናሽ በማድረግ፣ 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሆኑት ላይም የቲ-24 የሲስተም መግቢያ ፈቃድ ከእውቅናቸው ውጪ በመስረቅና በመጠቀም ግብይት የማጽደቅ እና ኦዲት የማድረግ ምንም ግብይት በሌለበት ሁኔታ ወደ ግል ድርጅት ዝውውር ያደረገ በመሆኑ፤
እንዲሁም ከብሔራዊ ባንክ ሂሳብ ቁጥር ገንዘቡን ተቀናሽ በማድረግ ወደ ድርጅቱ ሂሳብ ገቢ ካደረገ በኋላ ሌሎች ከልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመመሳጠር ከአንድ የባንኩ ደንበኛ ከሂሳብ ቁጥሩ ላይ 3 ሚሊዮን 900 ሺ ብር ተቀንሶ ወደ ድርጅቱ ሂሳብ የገባ መሆኑን የሚገልጽ ሀሰተኛ የንግድ ባንክ የገቢ ማረጋገጫ ደረሰኝ ለድርጅቱ በማቅረብ ድርጅቱም ገንዘቡ ገቢ መሆኑን በማረጋገጥ 96 ሺ 768 ፍሬ የሶፍት ጥቅሎችን ጠቅላላ ዋጋ ቫትን ጨምሮ 3 ሚሊዮን 899 ሺ 363 ብር ከ33 ሳንቲም በመሸጥ ከድርጅቱ መጋዘን እ.አ.አ. 18/9/2023 ተረክበው በሶስት ተሸከርካሪዎች ጭነው ከወሰዱ በኋላ ተከሳሽ ወደ ድርጅቱ ሂሳብ ያለአግባብ ገቢ ያደረገውን 3 ሚሊዮን 900 ሺ ብር ከድርጅቱ ፈቃድ እና እውቅና ውጪ ተከሳሽ በሚጠቀምበት የኮምፒውተር መለያ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሆኑት የቲ-24 የሲስተም መግቢያ ፈቃድ ከእውቅናቸው ውጪ በመጠቀም የባንኩን መመሪያ እና አሠራር በመጣስ ከድርጅቱ ሂሳብ ቅልበሳ በማድረግ እንዲሁም 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑትንም የቲ-24 የሲስተም መግቢያ ፈቃድ ከእውቅናቸው ውጪ በመስረቅና በመጠቀም ግብይት የማጽደቅ እና ኦዲት የማድረግ ሚና በህገ-ወጥ መንገድ ለውጥ በማድረግ ተከሳሽ ቅልበሳውን በማጽደቅ እና ኦዲት በማድረግ የተጠቀሰውን ገንዘብ መጀመሪያ ወደ ተቀነሰበት የብሔራዊ ባንክ ሂሳብ ቁጥር ተመላሽ በማድረግ በድርጅቱ እና በባንኩ ላይ የ3 ሚሊዮን 900 ሺ ብር ጉዳት እንዲደርስ ያደረገ በመሆኑ እንዲሁም ተከሳሽ በድርጊቱ በተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ልክ ከፍተኛ ጥቅም ያገኘ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀመው በሥልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሹ ቀርቦ ክሱ ደርሶት ከተነበበለት በኋላ የተከሳሽን የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡