የፍትሕ እና የዳኝነት አካሉ ቅንጅት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደርን ዉጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ያለዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል፡፡ በዚህ መሠረት ሁለቱ አካላት የየራሳቸዉ የአሠራር ነጻነት እንደተጠበቀ ሆኖ በብዙ ጉዳዮች በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ዛሬ ለዉይይት የቀረበዉ የሥርዓተ ጾታ ጉዳዮች የሥልጠና ካሪኩለም እና የሥልጠና ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት የዉይይት መድረክ አንዱ የቅንጅት አካል ነዉ ብሎ መዉሰድ ይቻላል፡፡
የጥናቱን ዉጤት መነሻ በማድረግ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ሚኒስቴር ከአውሮፓ ህብረት ቴክኒካል አሲስታንት ዩኒት ጋር በመሆን በጋራ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከፌደራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም ከፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊዎችና ዳኞች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የአውሮፓ ህብረት ቴክኒካል አሲስታንት ዩኒት ቡድን መሪ ሚስተር ፔጅ ኔል እና የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መዝሙር ያሬድ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የመድረኩ ዓላማ እንደ ፍትሕ ተቋም የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማመጣጠንና አካቶ ከመተግበር አንጻር ከተቋማቱ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠበቅ በመሆኑ በአውሮፓ ህብረት በሚደገፈው ፕሮጀክት አማካሪ በመቅጠር ከሥልጠና ሥራዎች አንፃር ያለውን ክፍተት ለመለየት የተደረገውን የዳሰሳ ጥናት ውጤት እና ምክረ ሀሳቦች ለመገምገም መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይት መድረኩም በሁለቱ ተቋማት የተዘጋጁ የሥልጠና ካሪኩለሞችና ማኑዋሎች ከሥርዓተ ጾታ አካታችነት አንጻር እንዲሁም በቀጣይ በተቋማቱ የሥርዓተ ጾታ ጉዳዮችን አካቶ ለመፈጸም እንዲያስችል ለማድረግ በቀጣይ የሥልጠና ማኑዋል ሊዘጋጅባቸው የሚያስፈልጉ የሥልጠና ፍላጎቶች በተመለከተ የዳሰሳ ጥናቱን ባከናወኑት አማካሪ ወ/ሮ ዜናዬ ታደሰ በዝርዝር ቀርቧል።
በዳሰሳው ውጤት መሠረትም በሁለቱ ተቋማት በተዘጋጁ የሥልጠና ካሪኩለሞችና የተለያዩ የሥልጠና ማኑዋሎች ከሥርዓተ ጾታ ጉዳዮች አንጻር ክፍተት ያለባቸው መሆኑ ተጠቅሷል። በተመሳሳይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በየተቋማቱ የሥርዓተ ጾታ ጉዳዮችን አስመልክቶ የተሰጡ ሥልጠናዎች አነስተኛ መሆናቸው ተመላክቷል። ከዚህ በተጨማሪም የሥርዓተ ጾታ ጉዳዮችን ከማካተት አንጻር በቀጣይ ሥልጠና እንዲሰጥባቸው የሚያስፈልጉ ርእሰ ጉዳዮች የተለዩ ሲሆን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሥልጠና ማኑዋል የሚዘጋጅና የአሰልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱ ተገልጿል።