የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮች ላይ በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ የህዝብ ምክክሮች መጠናቀቅ

የኢትዮጵያ መንግሥት – የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ – ለአገራችን ዘላቂ ሰላም፡ ዲሞክራሲ እና ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመገንዘብ – ሂደቱን በተሟላና በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በዚህ ረገድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማርቀቅ ስራ ለመጀመር የሚያስችለው ‘የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች’ መነሻ ሰነድ የፍትሕ ሚኒስቴር ባደራጀው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን የተዘጋጀ ሲሆን – ለፖሊሲ ዝግጅት እና ግብአት አሰባሰብ የሚያስፈልገው ብሔራዊ ምክክር የማስጀመሪያ ስነ-ሥርዓት የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል።

ይህን ተከትሎም በክልሎች ደረጃ የሚካሄደው ህዝባዊ ምክክር በመላው አገሪቱ በሚገኙ ከሀምሳ ስምንት በላይ ከተሞች ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለማከናወን መርሀ-ግብር ወጥቷል። በዚህ አግባብ የመጀመሪያው ምእራፍ የሕዝብ ምክክር በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 12 ከተሞች (አዳማ፡ አሰላ፡ ጪሮ፡ ሻሸመኔ፡ ባሌ ሮቤ፡ ቡሌ ሆራ፡ ኣዶላ፡ ወሊሶ፡ አምቦ፡ ጅማ፡ መቱ እና ነቀምት) ከሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በስኬት እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተካሂዷል።

በሁሉም የምክክር መድረኮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ እና የሂደቱን ልዩ ግብ ታሳቢ ባደረገ ሂደት የተመረጡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂ ግለሰቦች፡ የእምነት እና የማኅበረሰብ መሪዎች፡ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፡ የወጣቶች እና ሴቶች ተወካዮች፡ እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ድምጽ የሚወክሉ ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ንቃት ተሳትፈዋል። በባለሙያዎች በቀረቡ አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦች ላይ ሰፊ ክርክር አካሂደዋል፡፡ ጠቃሚ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን የማጠናከሪያ እና በአማራጭነት ሊያዙ የሚገቡ ምክረ-ሀሳቦችንም በስፋት አቅርበዋል።

በጥቅሉ ሲታይ – ከየከተሞቹ እና ራቅ ካሉ አዋሳኝ ወረዳዎች የተጋበዘው ሕዝብ በሙሉ – ረጅም ጉዞ በመጓዝ፡ በየመድረኮቹ ያለምንም መጓደል በመገኘት፡ እና በምክክር መድረኮቹ ላይም ከታቀደው በላይ ረጃጅም ሰአታትን በመጠቀም ያሳየው በባለቤትነት ስሜት የታጀበ ከፍተኛ ተሳትፎ – ገና ከጅምሩ ህዝቡ በሂደቱ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ያሳየበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ለዚህም ከፍተኛ ክብር እና ምስጋና ይገባዋል።

በዚህ አጋጣሚ ከሰነዶች ዝግጅት ጀምሮ – በቦታዎች እና ተሳታፊዎች መረጣ እና በሎጂስቲክስ እና ፋይናንስ ዝግጅት ባሉ የምክክር ሂደቶቹ ስራዎች አይነተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድርኮች የሚካሄዱ ሲሆን በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙት ሶስቱ ክልሎች የምክክር መድረኮች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

የሽግግር ፍትሕ ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን

ፍትሕ ሚኒስቴር

ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም

ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ያጋሩ

ፌስቡክ
ኤክስ
ሊንክዲን
ቴሌግራም

ሌሎች ጋዜጣዊ መግለጫዎች