የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ፤ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ የተደራጀ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት ከዚህ በኋላ ተቋሙ ተብሎ የሚጠራው፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ 84/ 2016 አንቀጽ 22 እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 መሠረት እንዲሁም በአዋጆቹ መሠረት የሚወጡትን ደንቦችና መመሪያዎች በትክክል በሥራ ላይ መዋላቸውን የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ተቋሙ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመተግበርና ለማስተግበር፤ መመሪያ ሲያወጣም ሆነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲሰጥ፤ የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን ተከትሎ መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥ ይህ ክትትል ሊካሄድ ችሏል።
ይህንን ክትትል ለማድረግ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮችን ተጠቅመናል። የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች በተቋሙ ማቋቋሚያና ማስፈጸሚያ ሕጎች ዳሰሳ እና በየደረጃው ያሉ የተቋሙ የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር የተደረገ ቃለ መጠየቅ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ደግሞ በተቋሙ የኢንስፔክሽን ዳስክ የምርመራ ቡድን አማካኝነት በዘጠኝ ተቋማት ላይ የተዘጋጀ ሪፖርት፣ የተለያዩ የአቤቱታ ማቅረቢያ እና መልስ መስጫ ቅጾች፣ እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የዜጎች ቻርተር፣ አቅጣጫ መጠቆሚያ ጣብያዎች፣ አስተያየት መስጫ ሳጥንና መዝገብ፣ የተገልጋዮች እርካታ መሙያ ቅጽ፤ የተገልጋይ እርካታ ዳሰሳ ጥናት ተጠቅመናል።
የናሙና አወሳሰድ ዘዴን በተመለከተ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ለማግኘት እንዲያስችል ዓላማ-መር (purposive sampling Technique) ተጠቅመናል። የተሰበሰቡ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ መረጃዎችን በመውሰድ ገላጭ በሆነ ሁኔታ ለመተንተን ተሞክሯል።
በተቋሙ የወጡ መመሪያዎች በሕግ በተሰጠ የውክልና ሥልጣን መሠረት የወጡ መሆኑ፣ ከአዋጁ መውጣት በፊት በሥራ ላይ የነበሩ ሦስት ነባር መመሪያዎችን እንዲሁም አዋጁ ከወጣ በኋላ የወጡ ስምንት አዳዲስ መመሪያዎችን ለፍትሕ ሚኒስቴር ልኮ ማስመዝገቡ፣ ለሚመለከታቸው የአስተዳደር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የመመሪያዎቹን ቅጂ እንዲደርሳቸው ማድረጉ፣ በየደረጃው ባሉ ጽ/ቤቶች ጭምር ሚኒ ላይብረሪ በመክፈት መመሪያዎችን ተደራሽ ማድረጉ፤ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ማቋቋሙ፣ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ለሚያቀርቡ ጉዳያቸውን በማዳመጥና በመመርመር መወሰንና ውሳኔውን ለተገልጋዩ መስጠት በዋናነት በጥንካሬ የሚጠቀሱ ሲሆን መዝገብ አለማደራጀት፣ ማስታወቂያ አለማውጣት፣ የማብራሪያ ጽሁፍ አለማዘጋጀት፣ በድረ-ገጽ አለመጫን፣ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል መቋቋሙን ለተገልጋዮች በድረ-ገጽ ይፋ አለማድረግ በዋናነት የታዩ ክፍተቶች ናቸው።
ተቋሙ የቅድመ መመሪያ አወጣጥ ድንጋጌዎችን ሳይከተል ያወጣው መመሪያ የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት በመ/ቁ/208307 በ29/11/2013 ዓም እንዲሰረዝ የሰጠው ውሳኔ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
በአጠቃላይ በዚህ ክትትል የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ከፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ጋር በማገናዘብ በዝርዝር ለማየት ተሞክሯል። በመጨረሻም በተቋሙ የታዩ ጥንካሬዎች እንዲቀጥሉ የታዩ ክፍተቶች ደግሞ እንዲታረሙ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።