ሕገ-ወጥ የሰዎች በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር እና ስደቶኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደ እና እየተባባሰ፣ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና እንግልት እየዳረገ በመሆኑ፣ ችግሩን ለመፍታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የሕግ ማዕቀፉ በመከላከል ላይ የተመሠረተ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤
የወንጀሉ ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና መልሶ ማቋቋም ሊደረግላቸው እንደሚገባ በመገንዘብ እና ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸውን፣ ጾታቸውንና ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ የተለየ ጥበቃ፣ እንከብካቤ እና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በማመን፤
በወንጀል ሕጉም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተቀመጡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ ምላሽ የማይሰጡ በመሆናቸው እና ወንጀለኞች ላይ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመጣል የሚያስችል ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 18 (2) በተደነገገው መሠረት በሰዎች መነገድ የተከለከለ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል የተደረሰውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ አገር በመሆኗ፣ ስምምነቱን ተከትለው በወጡት ሕገ-ወጥ የሰዎች በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር ለመከላከል ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት በወጣው ፕሮቶኮል እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት ለመከላከል የወጣ ፕሮቶኮልን ያጸደቀች በመሆኗ፣ እንዲሁም ከሕገ መንግስቱ እና ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ጋር የተጣጣመና የተሟላ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
•