የደን ዘርፈ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም ትልቅ ሚና የሚጫወት በመሆኑና በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ በደን መመናመን ምክንያት እየተከሰተ ያለውን አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመግታት ዘላቂ የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ፤
እየተከሰተ ያለውን የአፈር መከላት፣ የበረሃማነት መስፋፋትና የብዝሐ ሕይወት መመናመን ለመግታት የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ፤
የደን ዘርፉ የህብረተሰቡን የደን ውጤት ፍላጎትና አቅርቦት ልዩነት ለመሙላት፣ የግብርና ምርት እድገትን በማስቀጠል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ፤ መንግስት ለዘላቂ የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ያወጣቸውን ፖሊሲዎችና እና ስትራቴጂዎች ለማስፈጸም በመንግስት እና በግል ባለቤትነት ከሚለማው ደን በተጨማሪ የማህበረሰብና የማህበራት ባለቤትነትን በማረጋገጥ በህብረተሰብ ተሳትፎ ደንን ማልማት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ ስለታመነበት፣
ለዘላቂ የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ደን ከአካባቢያዊ፤ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አንፃር በምርት ሰጪነት፤ በጥብቅ እንዲሁም በፍፁም ጥብቅ ደንነት መለየትና ማስተዳደር አስፈላጊ በመሆኑ፤
ከዘርፈ ብዙ እና ከሁለትዮሽ ስምምነቶች የደን ዘርፍ ሊያስገኝ የሚያስችላቸውን አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ይበልጥ ማሳደግ በማስፈለጉ፤
በደን ዘርፉ የምርምር፤ የትምህርት፤ የኢንቨስትመንት፣ የግብይት እና የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 (5) እና አንቀጽ 55 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
•