በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር የሠራተኛን ውጤታማነት ለማሳደግ በሠራተኛውና በኮርፖሬሽኑ መካከል የሚደረግ የህብረት ስምምነት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ሠራተኞች በመልካም ሥነ-ምግባርና በሙሉ ሙያዊ አቅም ከፍተኛ የሕዝብና የመንግሥት ኃላፊነት የተጣለበትን ኮርፖሬሽን ለማገልገል መብትና ግዴታቸውን በግልፅ ማስቀመጡ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የባቡር ኢንዱስትሪ የሚጠይቀውን ጠንካራና ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ-መግባር የተላበሰ ሠራተኛ በመፍጠር ዘርፉን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማድረግ ሃገራችን ከዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ሁለንተናዊ ጥቅም ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በኮርፖሬሽኑና በሰራተኞች መካከል የሚደረግ የህብረት ስምምነት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡መብቱና ጥቅሙ ተከብሮለት ኃላፊነቶቹንና ግዴታውን የሚወጣ፣ የስራ አፈፃፀሙ በውጤት የሚለካ፣ለኮርፖሬሽኑ ተልዕኮ መሳካት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ለተቋሙ ደንበኞችና በለድርሻዎች ደኅንነት ተገቢውን ጥንቃቄ የሚያደርግ፣ አውቀቱንና ሙያውን በማዘመን ለኮርፖሬሽኑ ውጤታማነት ቀን ከለሊት የሚተጋ ሠራተኛን መፍጠር የባቡር ዘርፉ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በታለመው መልኩ እንዲደግፍ ለማድረግ በህብርት ስምምነት የሚቀመጡ ዝርዝር የአሰሪና የሠራተኛች መብትና ኃላፊነቶች ወሳኝ በመሆናቸው ይህን ህብረት ስምምነት መፈራረም አስፈልጓል፡፡
በመሆኑም፡- ይህ የሕብረት ስምምነት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት በተቋቋመውና በሚተዳደረው ከዚህ በታች “ኮርፖሬሽን” እየተባለ በሚጠራው በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 እና 494/98 (እንደተሻሻለው) መሠረት በተቋቋመውና በተመዘገበው ከዚህ በታች “ማህበር” እየተባለ በሚጠራው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር መካከል በሚከተሉት ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ ዛሬ ጥር 22, 2011 ዓ.ም ተፈርሟል፡፡