የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የታየውን ለውጥ ለማስቀጠልና ዘላቂ ለማድረግ ለተማሪዎች የሚሰጠውን የመማር ማስተማር አገልግሎት ግልጽ፣ ፈጣንና ውጤታማ እንዲሆንና ተጠቃሚነትን ለማስፈን በርካታ የለውጥ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ለውጦች መካከል ዋነኛው የከተማ አስተዳደሩን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አሠራር እንደገና በማዋቀር ተግባርና ሀላፊነታቸውን የሚመጥን መዋቅራዊ አደረጃጀትና የመሠረታዊ የስራ ሂደት ክለሳ ጥናት አካሂዷል፡፡
በዚህም መሠረት ለተዘጋጁ የስራ መደቦች ከመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ጋር የሚጣጣም የአፈፃፀም መመሪያና ቅደም ተከተልን መሠረት ያደረገ ጥናት ለየሥራ መደቦቹ በተሰጠው ደረጃ ዋና ርዕሰ መምህራንና ምክትል ር/መምህራንን መደቦች ላይ ብቃት ያላቸውን የትምህርት ቤት አመራሮች በውድድር ለመመደብ እንዲያስችል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ በመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 አንቀጽ 97 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን የዋና ርዕሰ መምህር እና ምክትል ርዕሰ መምህራን የድልድል አፈጻጸም መመሪያ አውጥቷል፡፡