የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ተቋማት የመድኃኒት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መወሰኛ ደንብ ቁጥር 74/2008 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መውጣቱ ይታወሳል፤
ደንቡ ሲወጣ ያደረጋቸው ታሳቢዎች መካከል የመድኃኒት አጠቃቀምና አያያዝን በሚመለከት የሚያጋጥም የጥራት ችግር እና ብክነትን ለመከልከል እንዲያስችል፤ለመድኃኒት አስተዳደር የሚያገለግል ሰነዶች ግልፅነት እንዲኖራቸው፤ኦዲት እና ቆጠራ ለማከናወን እንዲያመች፤ የጤና ተቋማት የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ፤
መሠረታዊ መደኃኒቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ እንዲያመች በማስፈለጉ ነው፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ስር ባለ የጤና ተቋማት እየተስተዋለ ያለትን የመድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ብክነት ለመቀነስና ብሎም ለማስወገድ እንዲያመች፣የመድኃኒት ክምችት ያለባቸው ተቋማት ላይ እጥረት ወደገጠማቸው ተቋማት በዝውውር የሚገለገለበትን አሠራር በግልፅና በሕግ የተደገፈ አሠራርን ማስቀመጥ በማስፈለጉ፣ በዕርዳታ ገቢ የሚሆኑ መድኃኒቶች ለብላሽ አሠራርና ለሙስና በር እንዳይከፍቱ ግልፅ የሆነ አሠራር ማስቀመጥ በማስፈለጉ፤
የጉድለት ተጋላጭነት ማካካሻ አፈፃፀም መመሪያ በማስፈለጉ፣ የመድኃኒት አገልግሎት አሰጣጡ ስርዓት በሚገባ እንዲመራ እና ተጠያቂነት ያለበት አሠራርና የተደራጀ የሰው ኃይል የያዘ አደረጃጀት ማስቀመጥ በማስፈለጉ፣ አገልግሎት ላይ የማይውል የመድኃኒት አወጋገድ ስርዓትና በሀገር አቀፍ ደረጃ በወጣው ሕግ መሠረት መፈፀም በማስፈለጉ፣የቅድመ መድኃኒት ግዢ ዕቅድ ዝግጅት ፣ አቅርቦት፣ ክምችትና አያያዝ፣ ስርጭት፣ ሽያጭና አወጋገድ ስርዓት እንዲሁም መድኃኒት አጠቃቀምና አገልግሎት አሰጣጥ ሥነ-ምግባር በግልፅ ማስቀመጥ በማስፈለጉ፤
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ደንብ ቁጥር 74/2008 አንቀጽ 28 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡