አንድ ሀገር በኢኮኖሚ እድገት የሚያሳየው፣ ዜጎች በትጋት ምርታማ (productive) ሆነው ስራቸውን መሥራት ሲችሉ እና በአንፃሩ መብትና ጥቅማቸው በሕግ አግባብ መከበር ሲችል ነው። በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለውን የስራ ግንኙነት ለማስተዳደር ሁለቱንም አካል ሊገዛ የሚችል ሕግ መውጣት እንዳለበት እሙን ነው። ሠራተኞችና አሠሪዎች የየራሳቸውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅና ግዴታዎቻቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንዲያስችላቸው የኅብረት ስምምነት ድርድር በማድረግ፤ በመካከላቸው የሚነሱ የወልም ሆነ የግል የሥራ ክርክሮች፣ የማኅበራዊ ምክክር ሥርዓትን ጨምሮ በተጨማሪ አማራጭ መድረኮች በተቀላጠፈ ሁኔታ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶችንና ግዴታዎችን ለመጠበቅ እንዲቻል የአሰሪና ሠራተኛ ሕግ በኢትዮጵያ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡
በዚህ አጭር ጽሁፍም በግል በተቋቋሙ ድርጅቶችና መንግስታዊ በሆኑ የልማት ድርጅቶች ተቀጥረው በሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ተፈጻሚነት ባለው የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ላይ ተደንግጎ የሚገኘውን የሰራተኞች ቅነሳ እና ውጤቱን እንመለከታለን።
የሰራተኞች ቅነሳ መቼ ይደረጋል?
የሰራተኞች ቅነሳ በአንድ ድርጅት ውስጥ ሊደረግ የሚችለው የድርጅቱን ድርጅታዊ አቋም ወይም የሥራ እንቅስቃሴ በሚመለከት በሚከተሉት ምክንያቶች የሥራ ውል ሲቋረጥ ነው:-
- ሠራተኞች የተሰማሩባቸው ሥራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና ለዘለቄታው የሚያስቆም የሥራ ውል መቋረጥ የሚያስከትል ሁኔታ ሲከሰት፤
- በአዋጁ አንቀጽ 18(5) እና (6) ላይ የተቀመጡት ከስራ ውል የሚመነጩ መብቶችና ግዴታዎች ለጊዜያዊ የሚታገዱበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አሠሪው በሚያመርታቸው ምርቶች ወይም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተፈላጊነት መቀነስ ምክንያት የድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ ወይም ትርፍ እየቀነሰ በመሄዱ የሥራ ውል ማቋረጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፤
- የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ የአሠራር ዘዴዎችን ለመለወጥ ወይም በአዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሲባል የሚደረግ የሥራ ውል መቋረጥ የሚያስከትል ውሣኔ ናቸው፡፡
የሰራተኞች ቅነሳ ነው ሊያስብል የሚችለው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ቁጥራቸው ከድርጅቱ ሠራተኞች ቢያንስ ከመቶ አሥር የሚያህለውን ወይም የሠራተኞች ቁጥር (የአንድ ዓመት አማካኝ የሰራተኞች ቁጥር) ከሀያ እስከ ሀምሳ በሆነበት ድርጅት ቢያንስ አምስት ሠራተኞችን የሚመለከት ከአሥር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የሚቆይ የሥራ ውል መቋረጥ ሲከሰት እንደሆነ በአስሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 29 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የሰራተኞች ቅነሳ ሂደት
በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት የሰራተኞች ቅነሳ ሲደረግ አሰሪ በራሱ ጊዜ የፈለገውን ሠራተኛ መቀነስ የማይችል ሲሆን ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የሰራተኞች ቅነሳ ሲደረግ በመጀመሪያ አሠሪው ከሠራተኞች ማኅበር ወይም ተወካይ ጋር በመመካከር የሥራ ችሎታ ያላቸውና ከፍተኛ የምርት ውጤት የሚያሳዩ ሠራተኞች በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ያደርጋል ወይም ከማይቀነሱ ሰራተኞች መካከል ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን በድርጅቱ ውስጥ ተመሳሳይ የሥራ ችሎታ ያላቸውና ተመሳሳይ የምርት ውጤት የሚያመርቱ ሠራተኞች በሚኖሩ ጊዜ የሰራተኞች ቅነሳ የሚደረገው በሚከተለው ቅደም ተከተል መሠረት ይሆናል:-
- በድርጅቱ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሠራተኞች፤
- አነስተኛ ቁጥር የሆነ ጥገኞች ያሏቸው ሠራተኞች፤
- ከተራ ቁጥረ (4) እስከ (7) ከተዘረዘሩት የሠራተኛ ክፍሎች ውጭ የሆኑ ሠራተኞች ቅነሳው በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከታቸው ይሆናል፤
- አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሠራተኞች፤
- በድርጅቱ ሳሉ በሥራ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች፤
- የሠራተኞች ተጠሪዎች፤
- ነፍሰጡር ሠራተኞች ወይም ከወለዱ እስከ 4 ወር ድረስ የሆናቸው ሴት ሠራተኞች ናቸው፡፡
በልዩ ሁኔታ የኮንስትራክሽን ስራ ማለትም ሕንጻ፣ መንገድ፣ የባቡር ሐዲድ፣ የባሕር ወደብ፣ የውሃ ግድብ፣ ድልድይ፣ የመሣሪያ ተከላና ሌላም ተመሳሳይ ሥራ የመሥራት የመለወጥ፣ የማስፋፋት፣ የማደስና የመጠገን ሥራ ተከታታይነት እያለቀ ሲሄድ የሥራው መጠን በመቀነሱ ምክንያት ተቀጥረው በሚሰሩ ሠራተኞች ላይ ቅነሳ ሲደረግ አሠሪው በዚህ ከላይ የተመለከቱትን የሠራተኞች ቅነሳ ሥነ ሥርዓት መከተል አይጠበቅበትም፡፡ ነገር ግን ሰራተኞች የተቀጠሩበት ሥራ ከማለቁ በፊት ከሆነ የሠራተኛ ቅነሳ ሲደረግ በአዋጁ ላይ የተገለጸውን ሥነ-ሥርአት መከተል የግድ ይለዋል። በተጨማሪም ቅነሳ ለማካሄድ አሰሪው የሁለት ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሚቀነሱት ሰራተኞች የመስጠት ግዴታ አለበት (አንቀጽ 35/1/መ)፡፡ እንዲሁም ድርጅቱ የሚወስደው እርምጃ፣ ከሰራተኞች ጋር የህብረት ስምምነት ካለው ይህንኑ እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በዚህ ረገድ የሚያወጣውን መመሪያ ያከበረ መሆን አለበት፡፡
የሰራተኞች ቅነሳ ያለው ውጤት
አንድ ሠራተኛ በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 29 መሠረት በሰራተኞች ቅነሳ ምክንያት የስራ ውሉ ሲቋረጥ የስራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት አለው። የስራ ስንብት ክፍያ መጠንን በተመለከተ ለመጀመሪያው የአንድ ዓመት አገልግሎት የሠራተኛው ማለትም የተቀነሰው ሠራተኛ የመጨረሻ ሣምንት አማካይ የቀን ደመወዙ በ30 ተባዝቶ ይከፈለዋል፡ከአንድ ዓመት በታች አግልግሎ ለተቀነሰ ሠራተኛ ግን እንደአገልግሎት ጊዜው እየተተመነ ተመጣጣኝ ክፍያ ያገኛል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎ በሠራተኛ ቅነሳ ምክንያት የስራ ውሉ የተቋረጠበት ሠራተኛ ከላይ በተጠቀሰው ክፍያ ላይ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአገልግሎት ዓመት ከላይ የተጠቀሰው ክፍያ አንድ ሦስተኛ እየታከለ የስራ ስንብት ክፍያው ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን ጠቅላላው ክፍያ ከሠራተኛው የ12 ወራት ደመወዝ መብለጥ የለበትም፡፡
በሰራተኞች ቅነሳ ምክንያት የስራ ውሉ ተቋርጦ ከስራ የተሰናበተ ሠራተኛ ከላይ ከተጠቀሰው የስራ ስንብት ክፍያ በተጨማሪ የሠራተኛው የመጨረሻ ሣምንት አማካይ የቀን ደመወዝ በ60 ተባዝቶ እንደሚከፈለው በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 40 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ አለመግባባት የሚፈጠር ከሆነ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ሰላም ለመፍጠር፣ ምርታማነትን ለማሻሻል ብሎም የሰራተኞች ህጋዊ መብቶች ለማስክበር በስራና ክህሎ ሚኒስቴር በሚመደብ አስማሚ ችግሩ እንዲፈታ መመልከት ወይም ይህን መሰል ጉዳይ የወል ስራ ክርክር በመሆኑ ለአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ዳኝነት መጠየቅ ይቻላል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ