የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ የዳኝነት ችሎት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

አገራችን የንግዱን ህብረተሰብ ከጸረ-ውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ለመጠበቅ እንዲሁም ሸማቾቹን የሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎችን ለመከላከል፣ ለነጻ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ስርዓትን ለማስፈን ብሎም የሸማቾችን ጤንነት እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ ዕቃ እና አገልግሎት መስፋፋትን ለመግታት እንዲቻል እና ሸማቾች ላወጡት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ ዕቃ እና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በማሰብ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ዓ/ም አውጥታለች፡፡ በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ለሸማቹ፣ ለነጋዴው እና ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ የሚደረጉ ጥበቃዎችን ለማስፈፀም የአስተዳደረዊ ዳኝነት ችሎቶችን በማቋቋም በሥራ ላይ አውላለች፡፡

በ2014 ዓ.ም የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ዓ/ም በአንቀጽ 22/1(ኘ)፣(አ) እና ከ መሠረት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ለንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም በአዋጅ 551/1999 ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ተሰጥተው የነበሩ ከዳኝነት ችሎት ሥራ ውጪ ያሉ ተግባርና ኃላፊነቶችን እንደ ተሰጡት በአዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡ በአንፃሩ በአዋጁ አንቀጽ 40(2)መ መሠረት በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እና በኢትየጰያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን አዋጅ ቁጥር 551/1999 የተቋቋሙት አስተዳደራዊ ዳኝነት አካላት በፍትሕ ሚኒስቴር ስር እንዲሆኑ በተደነገገው መሠረት ችሎቶቹ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ሆነው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ጽሁፍ ስለ የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደረዊ ዳኝነት ችሎት እና ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም አጠቃላይ የአስተዳደረዊ ችሎት የዳኝነት ሂደቶች በአጭሩ የሚዳስስ ይሆናል፡፡

የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ የዳኝነት ችሎት ሥልጣንና ተግባር

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 32 የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ የዳኝነት ችሎት ሥልጣን እና ተግባር በዝርዝር አመልክቷል፡፡ ይኸውም፡-

የመጀመሪያው በነጋዴዎች እና ነጋዴ ባልሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚፈሙ በአዋጁ ላይ የተከለከሉ ጸረ- ንግድ ውድድር ተግባራትን ማለትም በላይነት የተያዘ ገበያን አላአግባብ መጠቀም፣ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ጸረ-ውድድር ስምምነቶች እና በህብረት የሚያዙ አቋሞችና ውሳኔዎችን ማድረግ፣ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር መከናወን እና ከውህደት ጋር የተያያዙ ህገ-ወጥ ተግባራት ተፈፅመው ሲገኙ ተገቢውን አስተዳደረዊ እርምጃ እና አስተዳደራዊ ቅጣቶች የሚተላለፉበት ነው፡፡

አዋጁ የአስተደደራዊ የዳኝነት ችሎት የሚወሰዱ የአስተዳደረዊ እርምጃዎች እና የገንዘብ መቀጮ ምንነት እና መጠንን በመዘርዘር ያስቀምጣል፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 32(2) መሠረት አስተዳደራዊ እርምጃዎች የምንላቸው ተገቢ አይደለም የተባለው ድርጊት እንዲቆም ማድረግ፣ የተጎጂውን የመወዳደር አቅም ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ የሚያስችል ተገቢ እርምጃ መውሰድ ወይም የአጥፊው የንግድ ፈቃድ እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ የማድረግ እርምጃዎችን እንደሚያካትት በህጉ ላይ ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡

ሌላው በአዋጁ አንቀጽ 42 ላይ ስለ አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣት መጣልን የሚመለከት ሲሆን ይህም በህጉ ላይ የተከለከሉ ጸረ- ንግድ ውድድር ተግባራትን ማለትም በበላይነት የተያዘ ገበያን አለ አላግባብ መጠቀምን፣ የበላይነትን ማረጋገጥን፣ ጸረ-ውድድር ስምምነቶች ማድረግን እና በህብረት የሚያዙ አቋሞችና ውሳኔዎችን ማድርግን፣ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ማከናወንን እና ከውህደት ጋር የተያያዙ ህገ-ወጥ ተግባራት በፈፀሙ ነጋዴዎች እና ሌሎች ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ስለሚጣል አስተዳደራዊ መቀጮዎች የደነገገ ሲሆን ማንኛውም የዚህን ድንጋጌዎች ጥሶ የተገኘ ነጋዴ ነጋዴው ከዓመታዊ የሽያጭ ገቢ ላይ ከ5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት መጣልን ያካትታል፡፡ በሌላ በኩል ከላይ ከተዘረዘሩት ጥፋቶች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የማንኛውም ነጋዴ ያልሆነ ሰው ተሳትፎ መኖር ከተረጋገጠ ከብር 10,000 (አስር ሺ) እስከ 100,000 (መቶ ሺ) በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ነር ግን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተውን ጥፋት በመፈፀም ተግባር የተሳተፈና ስለተፈፀመው ጥፋትና ስለተባባሪዎቹ ሚና በቂና በሌላ አኳኋን ሊገኝ የማይችል መረጃ የሰጠን ሰው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክስ እንዳይመሠረትበት ሊያደርግ ይችላል በማለት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ሁለተኛው በአዋጁ ላይ የተከለከሉ ጸረ- ንግድ ውድድር ተግባራት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ነጋዴዎች በአስተደደራዊ የዳኝነት ችሎት ቀርበው ለደረሰባቸው ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ካሳ የሚጠይቁበት እና ተገቢውን የካሳ ውሳኔ የሚያገኙበት ነው፡፡

ሶስተኛው በዚህ አዋጅ ክፍል ሦስት የተመለከቱ የሸማቾች ጥበቃ ማለትም የሸማች መብቶች፣ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ስለማመልከት፣ ስለ ንግድ ዕቃዎች መግለጫ፣ ደረሰኞችን ስለመስጠትና ቀሪዎችን ስለመያዝ፣ ራስን ስለመግለፅ፣ ስለንግድ ማስታወቂያ፣ በንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ስለሚገኙ ጉድለቶች፣ መብትን የሚያስቀሩ የውል ግዴታዎች እና የተከለከሉ ድርጊቶች በመጣስ ለሚደርስ ጉዳት እና በአዋጁ ክፍል ሶስት ንዑስ ክፍል ሁለት ስር የተደነገገውን የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ስርጭት ማለትም የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን ስርጭት ስለመቆጣጠር፣ የንግድ ዕቃዎችን ማከማቸት እና መደበቅ፣ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን ዋጋ ስለመወሰን፣ ስለ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎች ስርጭት የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተጥሰው በአዲስ አበባ ወይም በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በተፈፀመ ግብይት የተነሳ ጉዳት የደረሰባቸው ሸማቾች ለደረሰባቸው ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንዲካሱ ለማድረግ የሚያስችል የዳኝነት ሥልጣን ይኖራቸዋል በማለት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ የአስተዳደራዊ ዳኝነት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሥልጣንና ተግባር

በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 33 መሠረት የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ የአስተዳደራዊ ዳኝነት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በአስተዳደራዊ የዳኝነት ችሎቱ በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በይግባኝ የማየት፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በውህደት ጉዳይ እና በአሳሳች ማስታወቂያዎች ላይ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች በይግባኝ አይቶ የማረም ሥልጣን አለው፡፡

ይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ችሎቱ የቀረበለትን ይግባኝ የአስተዳደራዊ የዳኝነት ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ ማጽናት፣ ማሻሻል ወይም መሻር ወይም እንደአግባቡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወይም የአስተዳደራዊው የዳኝነት ችሎት ጉዳዩን እንደገና መርምሮ እንዲወስን አስፈላጊው መመሪያ በመስጠት ሊመልስ እንደሚችል በአዋጁ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የአስተዳደራዊ ዳኝነት ችሎት የዳኝነት ሂደት

በሁሉም ደረጃ ያሉ የአስተዳደራዊ የዳኝነት እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ዳኝነት ሲያዩ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች እና ሰነዶችን ማንኛውም ሰው እንዲያቀርብላቸው የማዘዝ፣ ምስክሮች ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ የማዘዝ፣ ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎችና ትዕዛዞች የማስፈፀም፣ ፖሊስን ወይም አግባብ ያለውን ሌላ አካል የማዘዝ እና የንግድ ዕቃዎች እንዲታገዱ እንዲያዙና እንደሸጡ የማድረግ ሥልጣን አላቸው፡፡

በተጫማሪም የአስተዳደራዊው የዳኝነት ችሎት የአስተዳደር ቅጣት ወይም አስተዳዳራዊ እርምጃ በሚወስንበት ጊዜ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡-

  • የተፈፀመውን ጥፋት ባህሪ፣ የቆይታውን ጊዜ፣ የጥፋቱን ክብደትና መጠን
  • በተፈፀመው ጥፋት ምክንያት የደረሰውን የጉዳት መጠን፣
  • ጥፋቱ የተፈፀመበትን የገበያ ሁኔታ፣
  • ከተፈፀመው ጥፋት አጥፊው ያገኘውን ጥቅም፣
  • የአጥፊውን የኢኮኖሚ ደረጃ፣
  • በምርመራው ወቅት አጥፊው ያደረገውን ትብብር እና የአጥፊውን የቀድሞ ባህሪና የጥፋት ሪከርዶች ከግምንት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት በህጉ ተደንግገጎ ይገኛል፡፡

ሌላው ይግብኝን በተመለከተ በአዋጁ አንቅጽ 39 ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ውህደትን ለመከልከል ወይም የውህደት ፈቃድን ለመሰረዝ ወይም የንግድ ማስታወቂያውን ለማገድ በሰጠው ውሳኔ ወይም በማንኛውም የየዳኝነት ችሎት ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ለይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት በሚቀርብለት ይግባኝ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ ሆኖም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 33(3) መሠረት ይግባኝ ሰሚው አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የበሰጠውን ውሳኔ በሚመለከት የሕግ ስህተት ተፈጽሟል የሚል ወገን ውሳኔው በተሰጠ በ30 ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንደ ሚችል በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

ማንኛውም መንግስታዊ አካል ያልሆነ ሰው ለአስተዳደራዊው የዳኝነት ችሎት ክስ ሲያቀርብ ወይም ለይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሲያቀርብ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለበት የተደነገገ በመሆኑ የዳኝነት ክፍያ መፈፀም አለበት፡፡ አስተደደራዊ የዳኝነት ችሎቶች ጉዳዮችን በሚያዩበት ወቅት እንደሁኔታው የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

ማጠቃለያ

የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አስተዳደረዊ ዳኝነት ችሎት እና ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከላይ የተመለከቱ ሥልጣንና ተግባራት ያላቸው በመሆኑ ህብረተሰቡ በአስተዳደራዊ ችሎቶቹ ሥልጣን ሥር የሚታዩ ጉዳዮች ሲገጥሙ ጉዳዩን ለችሎቶቹ በማቅረብ ዳኝነት የመጠየቅ ልምዱን ሊያዳብር ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ