ደን ተፈጥሮአዊ ወይም ሰው ያለማው ሊሆን የሚችል ሲሆን ተፈጥሮአዊ ደን በተፈጥሮ የበቀሉ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች፣ ቁጥቋጦና ሌሎች የእንጨትነት ፀባይ ያላቸው ተክሎች የበቀሉበት እና ከፍተኛ የብዝሀ ህይወት ክምችት የሚገኝበት ነው፡፡ የተፈጥሮ ደን አካባቢዎች መኖር የሥነ-ምህዳራዊ (ecosystem) ጤንነትን እና ከፍተኛ ብዝሀ ህይወት ስብጥር እና ክምችትን በመጠበቅ የአካባቢ ንብረት መለወጥን (climate change) በመከላከሉ ረገድ የማይተካ ሚና ከመጫወታቸው በተጨማሪ ሰፊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ሆኖም ለነዚህ የተፈጥሮ ደኖች የሚደረገው ጥበቃ አጥጋቢ ባለመሆኑ በደን የተሸፈኑ መሬቶች ወደ ሌላ የመሬት አጠቃቀም እየተለወጡ በከፍተኛ ሁኔታ በመመናመን ላይ ይገኛሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የደን ሀብት መመናመን በአካባቢ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበረሰብ ላይ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመግታት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ በአለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት የደን ሀብትን በማልማት እና በመጠበቅ ዙሪያ የተዘጋጁ ስምምነቶችን በመቀበል እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ሀገራችንም የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ስምምነትን ጨምሮ ሌሎች ከደን ሀብት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላለች፡፡ በዚህ አጭር የፅሁፉ ይዘት ደንና የደን ውጤቶች ምንነትና ጠቀሜታ፣ የተከለከሉ ተግባራትና የሚያስከትሉትን ቅጣት እንመለከታለን፡፡
ደንና የደን ውጤቶች ምንነት
በ2010 ዓ/ም የወጣው የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/10 በአንቀጽ 2(1) መሠረት ደን ማለት በደን መሬት፣ በመንገዶች ዳርቻ፣ ወንዝ ዳርቻ፣ በእርሻና የግጦሽ መሬቶች ውስጥና በዙሪያቸው እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢዎችና ፓርኮች ውስጥ በተፈጥሮ የበቀሉ ወይም ተተክለው ወይም በሌላ ዘዴ የለሙ የዛፎችና የዕፅዋቶች እንዲሁም ሌሎች ብዝሀ-ሕይወቶች ክምችት እንደሆነ ትርጉም ሰጥቶታል፡፡
በዚሁ ሕግ በአንቀጽ 2(18) መሠረት የደን ውጤት ማለት ማንኛውም ከደን የሚገኝ የእንጨትነት ባህርይ ያለውና የሌለው ምርት እንዲሁም የደን ካርበንን ጨምሮ ማንኛውንም የደን ሥርዓተ-ምህዳራዊ ግልጋሎት የሚያካትት ነው በማለት ተርጉሞታል፡፡ በመሆኑም የደን ውጤት ሲባል የእንጨትነት ባህሪ ካላቸው እንደጣውላ፣ ቅጠላ ቅጠልና አጣናን ጨምሮ የእንጨትነት ባህሪ የሌላቸው እንደከሰል፣ የዛፍ ብስባሾች፣ ፍቅፋቂዎችና የእንጨት ዱቄቶችንም ሊያካትት ይችላል፡፡
ደንና የደን ውጤቶች ጠቀሜታ
የደን ሀብት የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የደን ዋነኛ ጠቀሜታው የተፈጥሮን ሚዛን በመጠበቅ የከፋ የአየር ንብረት ለውጥ እንዳይከሰት ማድረጉ ነው፡፡ ደን ዓለማችን በተለያየ ምክንያት የምታመነጨውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የተሰኘውን ጋዝ/አየር በመምጠጥ በምላሹ ህይወት ላላቸው ፍጥረታት ህልውና ጠቃሚ የሆነውን ኦክስጅን የተባለውን ጋዝ/አየር ይሰጠናል፡፡ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የተባለው አደገኛ ጋዝ በደኖች ባይመጠጥ ኖሮ የፀሀይ ሙቀት በቀጥታ መጥቶ መሬት ላይ እንዳያርፍ ሀይሉን የመቀነስ አቅም ያለውን ኦዞን የተባውን የጋዝ ንጣፍ የማሳሳት ባህሪ ወይም አቅም ስላለው ኦዞንን በማጥፋት ወይም በከፍተኛ ደረጃ እንዲሳሳ በማድረግ በመሬት ላይ የምንኖር ፍጥረታት የፀሀይን ሙቀት መቋቋም ወደ ማንችልበት ደረጃ እንደርስ ነበር፡፡
ሌላኛው የደን ጥቅም የመሬት ለምነትን እንዲጠበቅ ማድረጉ ነው፡፡ ደኖች በስሮቻቸው የመሬትን አፈር አቅፈው በመያዝ በጎርፍ ተሸርሽሮ እንዳይወሰድ ይረዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የደኖች ብስባሽ በጊዜ ብዛት ወደ አፈርነት ስለሚለወጥ መሬት በመአድናትና በንጥረ ነገሮች እንድትበለፅግ የራሱን አስዋፅኦ ያበረክታል፡፡ የደን ልማት ላይ በሚገባ የሰሩና በቂ የደን ክምችት ያላቸው አካባቢዎች የዝናብ እጥረት አያጋጥማቸውም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የድርቅ መከሰት ዕድሉ የጠበበ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መሬቱ ለም ከሆነና በበቂ ሁኔታ የዝናብ ስርጭት ካለ አርሶ አደር ከመሬቱ ሊያገኝ የሚገባውን የምርት መጠን ያገኛል፡፡ በዚህም የኑሮ ደረጃውንም ለማሻሻል ይረዳዋል ማለት ነው፡፡
በተጨማሪ ደን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ከኃይል ምንጭነት ጀምሮ ለግንባታና ለፋብሪካዎች በግብአትነት ያገልግላል፡፡ ደን እና በውስጡ የሚይዛቸው የብዝሀ ህይወት ስብጥር የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ ወይም ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ በመሆን ለስራ ፈጠራና ለውጪ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
የተከለከሉ ድርጊቶች
ከደንና የደን ውጤቶች ጋር በተገናኘ ህበረተሰቡ ሊያከናውናቸው የሚገቡና እንዳይፈፅማቸው የተከለከሉ ድርጊቶች በአዋጅ ቁጥር 1065/2010 ላይ ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህም መሠረት ህጉ ለአጠቃቀማቸው ገደብ የጣለባቸውና ፈፅሞ ሊነኩም የማይገቡ የደን ዓይነቶችን በዋናነት በሁለት ከፍሎ እንደሚከተለው አስቀምጧቸዋል፡፡
እንዳይቆጠሩ የተከለከሉ ደኖች
እነዚህ የደን ዓይነቶች ‘‘በመጥፋት ላይ የሚገኙ በተፈጥሮ የበቀሉ ሆነው በመንግሥት አለያም በማኅበረሰብ ይዞታ ስር…’’ የሚገኙ የደን ዓይነቶች ሲሆኑ እንዳይቆረጡ ህጉ ክልከላ አስቀምጦላቸዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ምናልባትም የደን ዓይነቶቹ ቀድሞውኑ በመጥፋት ስጋት ላይ ያሉ በመሆናቸውና አንዴ ከጠፉ በኋላ ለመተካት የማይቻል ወይም ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ አንፃር ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም፡፡ የደኖቹን ዓይነት በተመለከተ ማለትም አንድ ዛፍ በመጥፋት አደጋ ላይ መሆን ስላለመሆኑ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በመመሪያ በሚወስነው መሠረት ሊሆን እንደሚገባ በአዋጁ አንቀጽ 25/2/ ስር ተመላክቷል፡፡ ይህ ሚኒስቴር መ/ቤት የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 36(17) በኋላም አሁን በሥራ ላይ ባለው የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 106(37) መሠረት ሥልጣን ተግባሩ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተላልፏል፡፡
በግል ይዞታ የሚገኝ ደን
አንድ ግለሰብ በራሱ ይዞታ ስር እራሱ ያለማው ደን ኖሮት ለመጠቀም ቢፈልግና የደኑ ዓይነት በመጥፋት አደጋ ላይ የሚገኝ ከሆነ ለደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ሥልጣን የተሰጠው አካል አረጋግጦ በሚሰጠው ፈቃድ መሠረት መጠቀም የሚችል መሆኑ ተደንግጓል፡፡
ከግል ይዞታ ውጪ ያለ ደን
ከላይ የተገለፀው ሀሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ሰው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወይም አግባብነት ካለው የክልል ባለሥልጣን የጽሑፍ ፈቃድ ካልተሰጠው፣ ከግል ባለይዞታው ፈቃድ ውጪ ወይም ደኑ በይዞታው ስር የሚገኝ ካልሆነ በስተቀር ከማንኛውም ደን ውስጥ፡-
- ዛፍ መቁረጥ
- በቋሚነትም ሆነ በጊዝያዊነት በደኑ ውስጥ መስፈር
- የቤት እንስሳትን ለግጦሽ በደኑ ማሰማራት
- አደን ማካሄድ
- የእንጨት መሰንጠቅያ መጋዞችና ሌሎች ለደን መጨፍጨፍያ የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ይዞ በደኑ ውስጥ መገኘት
- በደኑ ውስጥ ቀፎ መስቀል፣ ማር መቁረጥም ሆነ መሰል ድርጊቶችን መፈፀም ክልክል መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 25/4/ ተደንግጓል፡፡
ሌሎች የተከለከሉ ተግባራት፡-
- የደን ምልክቶችን ማጥፋት፣ ማበላሸት ወይም ከቦታቸው ማዛወር፣
- ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት እሳት በመለኮስም ሆነ በሌላ ሁኔታ በደን ላይ ጉዳት ማድረስ፣
- ደንና የደን ልማት መሬት ተብሎ በተከለለ ስፍራ መስፈር፣ የእርሻ ቦታ ማስፋፋት ወይም ማንኛውንም ግንባታ ማካሄድ፣
- ያልተፈቀደ የደን ውጤት ማጓጓዝ፣
- የደን ባለቤት ሆኖ በደኑ ውስጥ ተባይ፣ ተስፋፊነት ያላቸው አረሞችና በሽታዎች መከሰታቸውን እያወቀ ለሚመለከተው አካል አለማሳወቅ፣
- የደን ባለቤት ሆኖ በደኑ ውስጥ ያልተፈቀዱ ዕፅዋትን፣ እንስሳትን ወይም ደቂቅ ነፍሳትን ማስገባት የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፡፡
ቅጣት
በህገ ወጥ መንገድ ለማገዶ እንጨት፣ ለከሰል፣ ለጣውላ ውጤቶች መስርያ ወዘተ ደንን የሚጨፈጭፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ለመቀነስ ከማስተማር አና ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ በዚህ ለማይገደቡ ግለሰቦች ክልከላውን ተላልፈው ሲገኙ ለሌላው የህበረተሰብ ክፍልም ማስተማሪያ የሚሆን ቅጣት መስጠቱ ተገቢነት ያለው በመሆኑ አዋጁ ለየጥፋት ዓይነቶቹ ተከታዩን ቅጣት አስቀምጧል፡፡ እኛም አንባብያን በቀላሉ ይረዱት ዘንድ እንደሚከተለው አስቀምጠነዋል፡፡
- በአዋጁና አዋጁን ለማስፈፀም በሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት ካልሆነ በስተቀር ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብ እና ከግል ደኖችና የደን መሬቶች ዛፎችን ከባለ ይዞታው ፈቃድ ውጭ የቆረጠ ወይም የደን ውጤቶችን የወሰደ፣ ለዚህ ተግባር የተባበረ ወይም በማንኛውም በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ የደን ውጤት ይዞ የተገኘ ወይም የተጠቀመ ማንኛውም ሰው የደን ውጤቱ መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ1 እስከ 5 ዓመት ፅኑ እስራት ከ10 ሺ እስከ 20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- የደን የወሰን ምልክቶችን ያጠፋ፣ ያበላሸ ወይም ያዛባ ከ1 እስከ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ከ10 ሺ እስከ 30 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- ሆነ ብሎ እሳት በመለኮስ ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ በደን ላይ ጉዳት ያደረሰ ከ10 እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት –
- ጉዳቱ የደረሰው በቸልተኝነት ከሆነ ከ1 እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ከ5 እስከ 10 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- ደን እና የደን መሬት ተብሎ በተከለለ ስፍራ የሰፈረ ወይም የእርሻ ቦታ ያስፋፋ ወይም ማንኛውንም ግንባታ ያካሄደ ከ2 እስከ 4 ዓመት ፅኑ እስራት ከ10 እስከ 40 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- ያልተፈቀደ የደን ውጤት ያጓጓዘ ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ቀላል እስራት ከ5 ሺ እስከ 10 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- ማንኛውም የደን ባለቤት በደን ውስጥ ተባይ፣ ተስፋፊነት ያላቸው አረሞችና በሽታ መከሰቱን እያወቀ አግባብ ላለው አካል በአፋጣኝ ያላሳወቀ እንደሆነ ከ6 ወር አስከ 1 ዓመት ቀላል እሰራት ከ1 ሺ እስከ 5 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- ማንኛውም የደን ባለቤት በደን ውስጥ ያልተፈቀዱ ዕፅዋትን፣ እንስሳትን ወይም ደቂቅ ነፍሳትን ያስገባ እንደሆነ ከ1 እስከ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ከ10 ሺ እስከ 30 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
- ዝርያቸው በመጥፋት ላይ የሚገኙ የዛፍ አይነቶችን በህገወጥ መንገድ ከመንግሥት፣ ከማህበራት፣ ከማኅበረሰብና ከግል ይዞታ ላይ የቆረጠ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸና ለሽያጭ ያቀረበ ከ5 እስከ 8 ዓመት ፅኑ እስራት ከ15 ሺ እስከ 20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ
ደን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ብሎም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያለው በመሆኑ ዜጎች ደን እንዲጠበቅ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ህጉን ማክበር እና በሌሎችም እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ