እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1987 ዓ/ም የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት በርካታ የቡድን እና የግለሰቦች መብቶች እውቅና እንዲኖራቸው በማድረግ ስራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ህገ-መንግሥት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ አብሮ ለመኖርና ለማድግ ያስችላቸው ዘንድ የግለሰብና የብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች መሠረታዊ መብቶች መከበር የግድ አስፈላጊ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተቀምጦ ይገኛል፡፡
የግለሰብ መብት መከበር የግድ በመሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት ላይም ተከብሮ ይገኛል፡፡ በዚህ ህገ-መንግሥት የተካተቱ የግለሰብ መብቶች በክፍል ሶስት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚለው ርዕስ ስር የተቀመጡ ሲሆን ከነዚህ የግለሰብ መብቶች መካከል ዋናዋናዎቹ በህይወት የመኖር መብት፣ የእኩልነት መብት፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የግል ህይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት፣ የሀይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት እና ቤተሰብ የማፍራት መብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት ለግለሰብ (Individual rights) መብት ብቻ ሳይሆን እውቅና የሰጠው ለቡድን (Group rights) መብትም እውቅና ሰጥቷል፡፡ እውቅና ከተሰጣቸው ወይም ጥበቃ ከተደረገላቸው የቡድን መብቶች መካከል የህጻናት መብት፣ የሴቶች መብት፣ የእምነት ነጻነትና የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች የጋራ ቃልኪዳናቸው አድርገው አፅድቀውታል፡፡
የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ፣ ባህሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ እንዲሁም ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንዳለው ህገ-መንግስቱ በግልጽ አስቀምጦት ይገኛል፡፡
በቋንቋ የመናገር፣ የመጻፍ እና ቋንቋውን የማሳደግ መብት፡- ስንል የአንድ ብሄረሰብ አባል የሆነ ሰው ሲወለድ ጀምሮ የተወለደበትን ብሄረሰብ ቋንቋ የአፍ መፍቻው የማድረግ መብት እንዳለውና ሲማርም በዚሁ አፉን በፈታበት ቋንቋ መማር እንደሚችል፣ የሚናገረውን ቋንቋ በተለያየ መንገድና ሁኔታ ማሳደግ የሚችል መሆኑን ያሳያል፡፡
ባህልን የመግለጽና የማዳበር መብት፡- ሲባል ማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱ የሆነውን ባህልና ቱፊት በማክበር የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ባህሉን ለሌላው ማሳወቅ እንደሚችልና ይህን ባህሉንም ካለበት ደረጃ ከፍ በማድረግ ጎጂ የሆነውን ልማድ በማስወገድ ወይም ባህሉን ማዳበር እንደሚችል ያሳየናል፡፡
ታሪክን የመንከባከብ መብት፡- ሲባል ያለውን ታሪክ በማስተማር፣ ሙዝየም በማደራጀትና በመሳሰሉት መንገዶች ታሪኩን ተንከባክቦ መጠበቅ እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡
ሌላው ለማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረስብ፣ ሕዝብ የተሰጠ መብት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሲሆን ይህ መብት ብሔር፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክአ ምድር ራሱን ለማስተዳደር የሚችል የመንግሥት ተቋም የማዋቀርና በፌደራሉ መንግሥት ውስጥም ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳለው በህገ-መንግስቱ ላይ ተደንግጓል፡፡ ይህ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ራሱን በራሱ ከማስተዳደርም አልፎ እስከመገንጠል የሚደርስ መብት እንዳለው በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብት በህገ-መንግስቱ ትልቅ ቦታ የተሰጠውና ዋና መሠረታዊ መብት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 105 ስለ ህገ-መንግሥት ማሻሻያ በሚያትተው አንቀጽ ላይ በህገ-መንግስቱ ምእራፍ ሶስት ስር ያሉ መብቶች ሊሻሻሉ የሚችሉት ጥብቅ በሆነ ስነ-ስረአት እንደሆነ ያስቀመጠ መሆኑ ነው፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህገ-መንግሥት ለቡድንና ለግለሰብ መብቶች ጥበቃና ከለላ የሚያደርግ ሲሆን የግለሰብም ሆነ የቡድን መብትን በተጣጣመ መንገድ ተፈፃሚ እንዲሆኑ እና ማንኛውም ሰው የማክበርና እንዲከበርለት የማድረግ መብት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የተረጋገጠላቸው ከመሆኑም በላይ ባሕላቸውን የማሳደግ፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብት እንዳላቸው አረጋግጧል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ