መግቢያ
አካባቢ ማለት በመሬት፣ በአየር፣ በአየር ሁኔታ እና በአየር ንብረት፣ በውሃ፣ በህያውያን፣ በድምጽ፣ በሽታ፣ በጣዕም፣ በመሀበራዊ ጉዳዮች እና በሥነውበት ሳይወሰን በተፈጥሮዊ ሁኔታ ወይም በሰው አማካኝነት ተሻሽለው ወይም ተለውጠው የሚገኙ ነገሮች በሙሉና ያሉበት ቦታ፣ እንዲሁም መጠናቸውን ወይም ሁኔታቸውን ወይም ዳግም የሰው ወይም የሌሎችን ሕያዋን ሁኔታን የሚነኩ መስተጋብሮቻቸው ድምር መሆኑን የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/995 ይደነግጋል፡፡
የአካባቢ ደኅንነት መብት የዜጎችን ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ንፁህና ለጤና ተስማሚ የሆነ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች ሊበከል ስለሚችል በአካባቢያችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ብክለት በመከላከል ንጹህ፣ ጽዱ እና ለኑሮ አመቺ የሆነ አካባቢን ለመፍጠርና ለመጪው ትውልድም ለማስረከብ አካባቢን ከሚያበላሹ ነገሮች መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ የቆዩ ሲሆን ሀገራችንም የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችና ሌሎች እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፡፡ በዚህ ጽሁፍም በሀገራችን ያለውን የአካባቢ ደኅንነት መብት የሕግ ማዕቀፍ እና የአካባቢ ጥበቃ ህጎችን መጣስ የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
የአካባቢ ደኅንነት መብትና የሕግ ማዕቀፍ
የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ አንፃር በሀገራችን ከተዘጋጁት የሕግ ማዕቀፎች መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት፣ በ1987 ዓ.ም የወጣው የአከባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መቋቋሚያ አዋጅ (በ1995 ዓ.ም የተሻሻለው)፣ የአከባቢ ተጽኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/1995፣ የአከባቢ ብክለት አዋጅ ቁጥር 300/1995 እና የ1997 የአከባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ይጠቀሳሉ፡፡
በ1995 በወጣው የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ለአካባቢ ደኅንነት እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን በአንቀጽ 44(1) ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው እንዲሁም በአንቀጽ 92 መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአከባቢን ደኅንነት ያገናዘበ እንዲሆን እና የሕዝብን የአከባቢ ደኅንነት የሚመለከት ፖሊሲ እና ፕሮግራም በሚነደፍበት እና ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የሚዘጋጅ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት በህገ መንግሰስቱ ተቀምጧል፡፡
ሌላው የአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ የወጣ ሕግ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/995 ሲሆን አዋጁ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የልማት ንድፈ ሀሳብ ሲዘጋጅ፣ ቦታው ሲመረጥ፣ ሲገነባ ወይም ሲተገበር የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በመተንበይ እና አስቀድሞ በማረም በውል የታሰበበትን ልማት ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑን ይደነግጋል፡፡
በአዋጁ ላይ እንደተቀመጠው ተዕፅኖ ማለት በአካባቢ ወይም በንኡሳን ክፍሎች ላይ በሚፈጠረው ለውጥ ምክንያት ማንኛውንም በሰው ጤና ወይም ደኅንነት፣ በእጽዋት፣ በእንስሳት፣ በአፈር፣ በአየር፣ በአየር ንብረት፣ በውሃ፣ በተፈጥሮዊ ወይም በባህላዊ ቅርስ፣ በሌላ ቁሳዊ ቁም አካል ወይም በአጠቃላይ ሲታይ በአካባቢያዊ፣ በመሀበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ወይም በበሀላዊ ገጽታዎች ላይ ሚከሰት ተከታይ ለውጥ ነው፡፡ እንዲሁም በካይ ማለት ፈሳሽ፣ ጠጣር ወይም ጋዝ ሆኖ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ያረፈበትን የአከባቢ ክፍል ጥራት በመለወጥ ጠቀሜታ የመስጠት አቅሙን የሚያጎድል፣ በሰው ጤና ወይም በሌሎች ሕያውያን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወይም ሊያደርስ የሚችል መርዝን፣ በሽታን፣ ክርፋትን፣ ጨረርን፣ ድምጽን፣ ንዝረትን፣ ሙቀትን ወይም ሌላ ክስተትን የሚያመነጭ ማንኛውም ነገር ነው፡፡
በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጁ መሠረት ማንኛውም ሰው የአካባቢ ግምገማ ተጽኖ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወይም ከሚመለከተው የክልል አካባቢ ጥበቃ መስረያ ቤት ይሁንታ ሳያገኝ መከናወን እንደሌለበት፣ የአካባቢ ግምገማ ተጽኖ ጥናት በፕሮጀክቱ ባለቤት ወጪ መከናወን እንዳለበት እና ባለስልጣኑም ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 8(2) ስር የአከባቢ ግምገማ ተጽኖ ጥናት ሊያካትት የሚገባውን ነገሮች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን የፕሮጀክቱን ባህሪ፣ በጥቅም ላይ የሚያውለውን ቴክኖሎጂ እና አጠቃቀም፣ ፕሮጀክቱ ሲተገበር እንዲሁም ቋሚ ሥራው ሲከናወን ወደ አካባቢው የሚለቀቀውን የበካይ ይዘት እና መጠን፣ የሥራው እንቅስቃሴ የሚጠይቀውን የኃይል ፍጆታ እና ምንጭ፣ ሊከተል ስለሚችል ክልል ተሻጋሪ የአካባቢ ተጽኖ መረጃ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይከተላሉ ተብለው የተተመኑ አውንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽኖዎች ባህሪያትና የሚቆዩበትን ጊዜ፣ አሉታዊ ተጽዕኖን ለማስወገድ፣ ለመቀነስ ወይም ለማቃለል የታቀዱ እርምጃዎች፣ የአካባቢ አያያዝ ችግርን ለማቃለል የተነደፉ እቅዶች፣ የአደጋ መከላከያ ዝግጁነት እና ፕሮጀክቱ በሚተገበርበት ወቅት የውስጥ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራዎች የሚከሄዱበትን መንገዶች ማስቀመጥ እንደለበት ተደንግጓል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ህጎችን ጥሰትና የሕግ ተጠያቂነት
በ1996 የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 521 እንደሚደነግገው ማንኛውም ሰው የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲደረግበት በሕግ የታዘዘውን ማንኛውንም ፕሮጀክት ከተገቢው አካል ፍቃድ ሳያገኝ ተግባራዊ ያደረገ እንደሆነ ወይም ይህንኑ በተመለከተ ሀሰተኛ መግለጫ ያቀረበ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡
እንዲሁም በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ መሠረት ማንኛውም የፕሮጅክት ባለቤት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሳያደርግ እና የባለስልጣኑን ይሁኝታ ሳያገኝ ተግባራዊ ያደረገ እንደሆነ ወይም በጥናቱ ሀሰተኛ መግለጫ ያቀረበ እንደሆነ ከብር 50,000 በማያንስ እና ከብር 100,000 በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ መሠረት ፍቃድ ሲሰጠው የተጣለበትን ግዴታ ካልተወጣ ወይም ተፈላጊ ዝርዝሮችን በመዝገቡ ሳያሰፍር ከቀረ ከብር 10,000 (አስር ሺ) በማያንስ እና ከብር 20,000 (ሀያ ሺ) በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ተቀምጧል፡፡ እንዲሁም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት ጥፋት ሲፈጽም ድርጅቱ እንዲከፍለው ከተፈረደበት መቀጮ በተጨማሪ የድርጅቱ የሥራ መሪ ከብር 5,000 (አምስት ሺ) በማያንስ እና ከብር 10,000 (አስር ሺ) በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይህን አዋጅ ወይም በሥሩ የሚወጣውን ደንብ ወይም መመሪያ በመጣስ ጥፋተኝነቱ የተረጋገጠበት ሰው ከሚወሰንበት ማንኛውም ቅጣት በተጨማሪ ያደረሰውን ጉዳት በሙሉ እንዲያስተካክል ወይም እንዲተካ ፍርድ ቤቱ ማዘዝ እንደሚችል አዋጁ አስቀምጧል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ አካባቢን ከሚጎዱና ከሚበክሉ ድርጊቶች የመጠበቅና ተፈፅሞ ሲገኝ የመከላከል ወይም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ የመስጠት ኃላፊነት ከሁሉም ዜጎች፣ ድርጅቶችና ከመንግሥት አካላት ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃንና ልማትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ህጎች ሲወጡ የህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን እና ከአካባቢ ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆን ማድረግ ንፁ እና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር ያግዛል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ