የአካባቢ ደህንነት መብትና የሀገራችን የህግ ማዕቀፍ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

አካባቢ ማለት በመሬት፤ በአይር፤ በአይር ሁኔታ እና በአይር ንብረት፤ በውሃ፤ በህያውያን፤ በድምጽ፤ በሽታ፤ በጣም፤ በመሃበራዊ ጉዳዮች እና በስነውበት ሳይወሰን በተፈጥሮዊ ሁኔታ ወይም በሰው አማካኝነት ተሻሽለው ወይም ተለውጠው የሚገኙ ነገሮች በሙሉና ያሉበት ቦታ፤ እንዲሁም መጠናቸውን ወይም ሁኔታቸውን ወይም ዳግም የሰው ወይም የሌሎችን ሕያዋን ሁኔታን የሚነኩ ተስተጋብሮቻቸው ድምር መሆኑን የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/995 ይደነግጋል፡፡

የአካባቢ ደኅንነት መብት የዜጎችን ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ንፁህና ለጤና ተስማሚ የሆነ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች ሊበከል ስለሚችል በአካባቢያችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ብክለት በመከላከል ንጹህ፣ ጽዱ እና ለኑሮ አማቺ የሆነ አካባቢን ለመፍጠርና ለመጪው ትውልድም ለማስረከብ አካባቢን ከሚያበላሹ ነገሮች መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ የቆዩ ሲሆን ሀገራችንም የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ የተለየዩ የሕግ ማዕቀፎችና ሌሎች እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፡፡

የአካባቢ ደኅንነት መብትና የሕግ ማዕቀፍ

የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ አንፃር በሀገራችን ከተዘጋጁት የሕግ ማዕቀፎች መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት፣ በ1987 ዓ.ም የወጣው የአከባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መቋቋሚያ አዋጅ (በ1995 ዓ.ም የተሻሻለው)፣ የአከባቢ ተጽኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/1995፣ የአከባቢ ብክለት አዋጅ ቁጥር 300/1995፣ የ1997 የአከባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ይጠቀሳሉ፡፡

በ1995 በወጣው የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ለአካባቢ ደኅንነት እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን በአንቀጽ 44 (1) ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው እንዲሁም በአንቀጽ 92 መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአከባቢውን ደኅንነት ያገናዘበ እንዲሆን እና የሕዝብን የአከባቢ ደኅንነት የሚመለከት ፖሊሲ እና ፕሮግራም በሚነደፍበት እና ስራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት በህገ መንግሰስቱ ተቀምጧል፡፡

ሌላው የአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ የወጣ ሕግ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/995 ሲሆን አዋጁ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ የልማት ንድፈ ሀሳብ ሲዘጋጅ፤ ቦታው ሲመረጥ፤ ሲገነባ ወይም ሲተገበር የሚያስከትለውን ተጽኖ በመተንበይ እና አስቀድሞ በማረም በውል የታሰበበትን ልማት ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

በአዋጁ ላይ እንደተቀመጠው ተዕፅኖ ማለት በአካባቢ ወይም በንኡሳን ክፍሎች ላይ በሚፈጠረው ለውጥ ምክንያት ማንኛውንም በሰው ጤና ወይም ደኅንነት፤ በእጽዋት፤ በእንስሳት፤ በአፈር፤ በአይር፤ በአይር ንብረት፤ በውሃ፤ በተፈጥሮዊ ወይም በባህላዊ ቅርስ፤ በሌላ ቁሳዊ ቁም አካል፤ ወይም በአጠቃላይ ሲታይ በአካባቢያዊ፤ በመሀበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊ ወይም በበሃላዊ ገጽታዎች ላይ ሚከሰት ተከታይ ለውጥ ነው፡፡ እንዲሁም በካይ ማለት ፈሳሽ፤ ጠጣር ወይም ጋዝ ሆኖ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ያረፈበትን የአከባቢ ክፍል ጥራት በመለወጥ ጠቀሜታ የመስጠት አቅሙን የሚያጎድል፣ በሰው ጤና ወይም በሌሎች ሕያውያን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወይም ሊያደርስ የሚችል መርዝን፤ በሽታን፤ ክርፋትን፤ ጨረርን፤ ድምጽን፣ ንዝረትን፤ ሙቀትን፤ ወይም ሌላ ክስተትን የሚያመነጭ ማንኛውም ነገር ነው፡፡

በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጁ መሠረት ማንኛውም ሰው የአካባቢ ግምገማ ተጽኖ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወይም ከሚመለከተው የክልል አካባቢ ጥበቃ መስረያ ቤት ይሁንታ ሳያገኝ መከናወን እንደሌለበት፣ የአካባቢ ግምገማ ተጽኖ ጥናት በፕሮጀክቱ ባለቤት ወጪ መከናወን እንዳለበት እና ባለስልጣኑም ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 8 (2) ስር የአከባቢ ግምገማ ተጽኖ ጥናት ሊያካትት የሚገባውን ነገሮች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን የፕሮጀክቱን ባህሪ፤ በጥቅም ላይ የሚያውለውን ቴክኖሎጂ እና አጠቃቀም፣ ፕሮጀክቱ ሲተገበር እንዲሁም ቋሚ ስራው ሲከናወን ወደ አካባቢው የሚለቀቀውን የበካይ ይዘት እና መጠን፣ የስራው እንቅስቃሴ የሚጠይቀውን የኃይል ፍጆታ እና ምንጭ፣ ሊከተል ስለሚችል ክልል ተሻጋሪ የአካባቢ ተጽኖ መረጃ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይከተላሉ ተብለው የተተመኑ አውንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽኖዎች በሃሪያትና የሚቆዩበትን ጊዜ፣ አሉታዊ ተጽኖን ለማስወገድ፤ ለመቀነስ ወይም ለማቃለል የታቀዱ እርምጃዎች፣ የአካባቢ አያያዝ ችግርን ለማቃለል የተነደፉ እቅዶች፤ የአደጋ መከላከያ ዝግጁነት እና ፕሮጀክቱ በሚተገበርበት ወቅት የውስጥ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎች የሚከሄዱበትን መንገዶች ማስቀመጥ እንደለበት ተደንግጓል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ግጎችን ጥሰትና የሕግ ተጠያቂነት

በ1996 የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 521 እንደሚደነግገው ማንኛውም ሰው የአካባቢ ተጽኖ ግምገማ እንዲደረግበት በሕግ የታዘዘውን ማንኛውንም ፕሮጀክት ከተገቢው አካል ፍቃድ ሳያገኝ ተግባራዊ ያደረገ እንደሆነ ወይም ይህንኑ በተመለከተ ሀሰተኛ መግለጫ ያቀረበ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡

እንዲሁም በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ አዋጅ መሠረት ማንኛውም የፕሮጅክት ባለቤት የአካባቢ ተጽኖ ግምገማ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት የአካባቢ ተጽኖ ግምገማ ሳያደርግ እና የባለስልጣኑን ይሁኝታ ሳያገኝ ተግባራዊ ያደረገ እንደሆነ ወይም በጥናቱ ሀሰተኛ መግለጫ ያቀረበ እንደሆነ ከ50000 ብር በማያንስ እና ከ100000 ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ መሠረት ፍቃድ ሲሰጠው የተጣለበትን ግዴታ ካልተወጣ ወይም ተፈላጊ ዝርዝሮችን በመዝገቡ ሳያሰፍር ከቀረ ከ10000 (አስር ሺ) ብር በማያንስ እና ከ20000 (ሀያ ሺ) ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ተቀምጧል፡፡ እንዲሁም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት ጥፋት ሲፈጽም ድርጅቱ እንዲከፍለው ከተፈረደበት መቀጮ በተጨማሪ የድርጅቱ የስራ መሪ ከ5000 (አምስት ሺ) ብር በማያንስ እና ከ10000 (አስር ሺ) ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይህን አዋጅ ወይም በሥሩ የሚወጣውን ደንብ ወይም መመሪያ በመጣስ ጥፋተኝነቱ የተረጋገጠበት ሰው ከሚወሰንበት ማንኛውም ቅጣት በተጨማሪ ያደረሰውን ጉዳት በሙሉ እንዲያስተካክል ወይም እንዲተካ ፍርድ ቤቱ ማዘዝ እንደሚችል አዋጁ አስቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ አካባቢን ከሚጎዱና ከሚበክሉ ድርጊቶች የመጠበቅና ተፈፅሞ ሲገኝ የመከላከል ወይም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ የመስጠት ኃላፊነት ከሁሉም ዜጎች፣ ድርጅቶችና ከመንግሥት አካላት ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃንና ልማትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ህጎች ሲወጡ የህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንዲሆን እና ከአካባቢ ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆን ማድረግ ንፁ እና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር ያግዛል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት