የሐራጅ ሽያጭ ሥነ ሥርዓት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የፍርድ ባለእዳ የሆነ ሰው በፍርዱ መሠረት ሳይፈፀም ሲቀር እንደ ፍርዱ እንዲፈፅም በአፈፃፀም ሥነ ሥርዓት የሚገደድ ሲሆን አፈፃፀም ፍርድ ቤት እራሱ የሰጠውን ፍርድ ወደ ተግባር የሚለውጥበት ሥርዓት ነው፡፡ አፈፃፀም ስለፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመከተል ፍርድን በተግባር መተርጎም እንደመሆኑ መጠን የማስፈፀሚያ ሥርዓቱ በጥቅሉ በፍትሐብሐር ሥነ-ሥርዓት ሕጉን መሠረት ይፈፀማል፡፡ በፍርድ አፈፃፀም ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ያሉ ሲሆን እነሱም ንብረት ማስከበር፣ በተከበረ ወይም በተያዘ ንብረት ላይ ሦስተኛ ወገኖች የሚያቀርቡት መቃወሚያ አና የሐራጅ ሽያጭ ሥነ-ሥርዓት ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ የሐራጅ ሽያጭ ሥነ-ሥርዓትን የምንመለከት ይሆናል፡፡

የሐራጅ ሽያጭ ሥነ ሥርዓት ምንነት

ሐራጅ “እንዲሸጥ የተወሰነ ንብረት በጨረታ ወይም ገበያ ላይ በተገኘው ዋጋ የሚሸጥበት መንገድ ነው በማለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ጥናትና ምርምር የአማርኛ መዝገበ ቃላት(1993) ትርጉም ሰጥቶታል፡፡

የሐራጅ ሽያጭ ሥነ ሥርዓትን ስንመለከት አንድ ጊዜ ንብረቱ በፍርድ ቤቱ ታግዶና በታገደው ንብረት ላይ ተቃወሞ ቀርቦ ምርመራ ከተደረገበት ከተወሰነ በኋላ ንብረቱ በሀራጅ እንዲሸጥ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ይህም የሐራጅ ሽያጭ ሥርዓት አፈፃፀም የሚጀምረው ለሕዝብ ማስታወቂያ በማውጣት ይሆናል፡፡ በቀጥታ ወይም በተለዋዋጭ ገንዘብ እንዲከፈል የተሰጠ ማናቸውም ፍርድ ወይም ውሣኔ የሚፈፀመው የባለዕዳውን ንብረት በማስከበርና በማሸጥ ሲሆን፤ ማናቸውም ሀብት ወይም ንብረት የሚሸጠውም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 422/3/፣ 427 እና 439 የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው የሐራጅ ሽያጭ በማድረግ ነው፡፡

ለፍርድ ማስፈፀሚያ ተብሎ የሚሸጠውም ንብረት በቁጥር 394/2/ እና 422/1/ እንደተደነገገው ከሚፈለገው የዕዳ መጠን ጋር በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡

ለፍርድ አፈፃፀም ንብረትን የመሸጥ ሥነ-ሥርዓት

የመሸጥ ሥነ ሥርዓቱ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር ከ422 እስከ 449 በተደነገገው መሠረት ይፈፀማል፡፡ ከቁጥር 422 እስከ 431 የተደነገጉት በሁሉም የሽያጭ ዓይነቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ፣ ከቁጥር 432 እስከ 438 ያሉት በተለይ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን ብቻ የሚመለከቱ እና ከቁጥር 439 እስከ 449 ያሉት በተለይ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ማንኛውም ንብረት በአፈፃፀም የሚሸጠው በሐራጅ ሽያጭ ነው፡፡ ሆኖም በፍርድ ባለመብቱና በፍርድ ባለዕዳው ፈቃድ ንብረቱ በስምምነት እንዲሸጥ ፍርድ ቤቱ ለማዘዝ ይችላል፡፡ ንብረቱ በሐራጅ እንዲሸጠጥ ትእዛዝ (ውሳኔ) ከተሰጠ የሽያጩ ማስታወቂያ ለሕዝብ መገለፅ ይኖርበታል፡፡

የሐራጅ ሽያጭ ሥነ ሥርዓቱ በማን ይፈፀማል?

የታገደ (የተከበረ) ንብረት የሚሸጠው የሽያጩን ሥርዓት እንዲያስፈፅም ፍርድ ቤቱ በተለይ ባዘዘው ሰው ወይም በፍርድ ቤቱ ሠራተኛ አማካኝነት ነው፡፡ ፍርድን ለማስፈፀም ማናቸውንም ሀብት ወይም ንብረት እንዲሸጥ የታዘዘ ሰው በሕጉ አነጋገር ሐራጅ ባይ ተብሎ ይጠራል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 422(2))፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በፍትሐብሔር ችሎቶች በሐራጅ እንዲሸጡ ውሳኔ የሚያሳርፍባቸው የፍርድ ባለዕዳ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ሀብትና ንብረቶችን ፍርድ ለማስፈጸም የሐራጅ ሽያጭ የሚያከናውን መሆኑ ይታወቃል፡፡

የሐራጅ ሽያጭ ሥነ ሥርዓት ሂደት

የሐራጅ ሽያጭ ሥርዓት አፈፃፀም የሚጀመረው ለሕዝብ ማስታወቂያ በማውጣት ይሆናል፡፡ ማስታወቂያውም ንብረቱ በሚገኝበት አቅራቢያ ወይም ግልጽ ሆኖ ሊታወቅና ሊሰማ በሚችልበት ዘዴና በማናቸውም ልማዳዊ ዓይነት በአደባባይ በመንገር ወይም በመለጠፍ ለፈፀም ይችላል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 425(1) እና 414(2))፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማስታወቂያው በጋዜጣ መውጣት አለበት (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 425(2)፡፡ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 423 መሠረት የሐራጅ ማስታወቂያው

  • የሚሸጠውን ንብረት አይነትና የዋጋ ግምት
  • ከንብረቱ ላይ የሚጠየቅ የዋስትና መያዣ ወይም ሌላ መብት መኖር አለመኖሩና ካለም መጠኑን
  • ለመሸጡ ምክንያት የሆነውን በፍርድ የተወሰነ የገንዘብ መጠን
  • ንብረቱ የሚሸጥበትን ሁኔታ፣ ገደብ፣ የሽያጭ ገንዘብና የሚከፈልበትን ጊዜ
  • ሌሎች ገዢው ከመግዛቱ በፊት ሊያውቃቸው ይገባል ብሎ ፍርድ ቤት የሚገምታቸውን ዝርዝር መረጃዎች

አሟልቶ መያዝ አለበት፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 426 መሠረት የፍርድ ባለዕዳው ከዚህ አስቀድሞ እንዲሸጥ ካልተስማማ በስተቀር ማናቸውም የሚንቀሳቀስ ንብረት አንዲሸጥ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን አንስቶ 15 ቀን፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን ደግሞ 30 ቀን ድረስ ሳይቆይ በሐራጅ ሊሸጥ አይችልም፡፡ ይህም ቀን መቆጠር የሚጀምረው ማስታወቂያው ከተለጠፈ ወይም በጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ይሆናል፡፡ የታገደው ዕቃ ቶሎ የሚበላሽ ከሆነ ከላይ የተጠቀሰውን ጊዜ መጠበቅ ሳያስፈልግ ንብረቱ ወዲያውኑ ሊሸጥ ይችላል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 426፣ 406(2))፡፡ በመጀመሪያው ማስታወቂያ ላይ በተገለፀው የዋጋ ግምት ንብረቱን የሚገዛ ገዥ ካልተገኘ ሁለተኛ ጨረታ እንዲደረግ ይታዘዛል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 428)፡፡ የሐራጅ ማስታወቂያ ከመውጣቱ በፊት የፍርድ ባለዕዳው የሚፈለግበትን ዕዳ በሙሉ ከከፈለ የሐራጁ ሽያጭ ይቆማል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 427)፡፡

የሐራጅ ሽያጭ ስለሚፀናበትና ስለሚሰረዝበት ሁኔታ

ሽያጩን እንዲፈርስ የሚጠይቅ ሰው በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ማመልከቻ አቅርቦ እንዲፈርስ ወይም እንዲሰረዝ ካላደረገ ሽያጩ የፀና ይሆናል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 447)፡፡ የሚንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ ሲሸጥ የሽያጭ ሥርዓት በትክክል አለመፈፀሙ ሽያጩን አያፈርሰውም፡፡ ሆኖም ጉዳት የደረሰበት ወገን ከጉዳት አድራሹ ካሳ እንዲከፍለው መጠየቅ ይችላል (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 435) ፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ ሲሸጥ በአሻሻጡ ሥርዓት ላይ ግዙፍ የሆነ ጉድለት የተፈፀመ ከሆነ ግን የፍርድ ባለ ገንዘቡ ወይም መብቱ የሚገባው ሌላ ሰው ሽያጩ እንዲፈረስ ወይም እንዲታገድ መጠየቅ ይችላል፡፡ ሽያጩ የሚፈርሰው ከሥርዓት ውጪ ስለተፈፀመ ብቻ ሳይሆን ግዙፍ የሆነ ጉድለት ወይም የማታለልና የማጭበርበር ሥራ ተፈፅሞ ሲገኝና ይህም በአመልካቹ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ያደረሰበት መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው (የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 445)፡፡ በፍርድ ምክንያት ንብረት እንዲታላለፍ የተሰጠውን ትእዛዝ የመቃወም ወይም የእምቢተኝነት ደርጊት ሲፈፀም ፍርድ ቤቱ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 450 እስከ 455 በተደነገገው መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡

ማጠቃለያ

ሐራጅ በፍርድ ባለእዳ ላይ የተሰጠን ውሳኔ በፍርድ ባለእዳው ንብረት ላይ ለማስፈፀም ንብረት የሚከበርበት እና የሚሸጥበት ሂደት ሲሆን የሚፈፀምበት የራሱ ሥነ ሥርአት ያለው በመሆኑ በሂደቱ የሚሳተፉ አካላት ሥነ ሥርአቱን በአግባቡ ሊረዱ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ