መግቢያ
ህገ መንግሥት የአንድን አገር አጠቃላይ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መሠረታዊ መርሆዎችን የሚይዝ ሰነድ ሲሆን የሚሻሻልበትን ሁኔታ በተመለከተ በራሱ በህገ መንግስቱ ውስጥ መደንገግ የተለመደ ነው፡፡ በአገራችንም በ1987 ዓ.ም የወጣው ህገ መንግሥት በሥራ ላይ ያለው ሲሆን ስለሚሻሻልበትም ሁኔታ በዝርዝር ደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ሂደትን በተመለከተ ሌሎች አገራት ያላቸውን ተሞክሮ እንዲሁም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ሊሻሻል የሚችልበትን ሥነ ሥረዓት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
ህገ መንግሥት ለምን ይሻሻላል?
አሁን ባለንበት ዘመን የአለማችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ እና የማኅበራዊ ሁኔታዎች በፍጥነት የሚቀያዩሩ በመሆኑ ህገ መንግሥትም ከዚሁ ለውጥ ተፅዕኖ ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ህገ መንግሥት እንደአገሩ ሕግና እንደ አስፈላጊነቱ ህጋዊ ሂደቶችን ተከትሎ እየተሻሻለ በጊዜ ሂደት የሚገጥሙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ለውጦችን ያገናዘበ መሆኑ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ህገ መንግሥት የአንድ ሀገር ሕዝብ የሚመራበት የጋራ ስምምነት ሰነድ እንደመሆኑ የሚሻሻልበት ሂደት ሌሎች ህጎች ከሚሻሻሉበት ሂደት የተለየ እና ጥብቅ ሂደቶችን የሚያካትት መሆን አለበት፡፡
ህገ መንግሥትን እንደሌሎች ህጎች በቀላል ሂደት እና በየጊዜው ማሻሻል የሚያስከትለው ችግር
ህገ መንግሥትን በጊዜ ሂደት ለሚገጥም ችግሮች እና ሁኔታዎች ጥብቅ የሆነ ሥነ ሥረዓትን ተከትሎ ማሻሻል አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን እንደ ሌሎች ህጎች በቀላሉ ማሻሻል ችግሮች ሊያስከትል ይችላል፡፡ይኸውም፡-
- በቀላሉ የሚሻሻል ህገ መንግሥት ዜጎች ድርጊታቸውን እና ውጤታቸውን ሊገምቱ እንዳይችሉ ያሚያረግና በአጠቃላይ በአንድ አገር አለመረጋጋትን፣ በነገሮች እርገጠኛ አለመሆንን እና በፖለቲካ ሥረዓቱ ላይ እምነት ማጣትን ይፈጥራል፡፡
- በቀላሉ የሚሻሻል ሕግ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ መርሆዎች እና ተቋማት በጊዜያዊ ሀሳቦች እና አመለካከቶች ምክንያት አደጋ ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል፡፡
- በቀላሉ የሚሻሻል ህገ መንግሥት መሻሻልያ ለጊዜአዊ የፖለቲካ ጥቅም ያለአግባብ መገልገያነት እና እንደ መሳሪያ መጠቀሚያነት ተጋላጭ ሊሆን ይችላል፡፡
- በቀላሉ፣ በየጊዜው እና በቸልተኝነት የሚሻሻል ህገ መንግሥት በጊዜ ሂደት ተፈፃሚነቱን እና ቅቡልነቱን እንዲያጣ ይሆናል፡፡
ህገ መንግሥት ማሻሻል በተመለከተ ጥቅም ላይ የሚውል ሥነ ሥርአቶች
በአብዛኝው የአለማችን አገራት ህገ መንግሥት ማሻሻልን በተመለከተ ከሌሎች ህጎች በተለየ ጥብቅ እና የተለያዩ ውስብስብ ሥነ ሥረዓትን ይከተላሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ በህገ መንግስቱ ማሻሻያ ሀሳብ ላይ እና የማሻሻያ ሀሳብን ለማፅደቅ በተለያዩ ምክር ቤቶች ከፍተኛ ድምፅ ማግኘት፣ የተለያዩ ምክክሮችን ማድርግ፣ አቆይቶ ረጅም ጊዜ ወስዶ ማየት፣ ህዝበ ውሳኔ ማድረግ የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
በአጠቃላይ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አገራት ህገ መንግሥትን ማሻሻልን በተመለከት የተለያዩ ሥነ ሥረዓቶችን እና ገደቦችን ያስቀምጣሉ፡፡ ለአብነትም ሥነ ሥረዓታዊ ገደቦች /Procedural Constraints/ እና በህገ መንግስቱ የተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ በግልፅ ገደቦች ማስቀመጥ/Express Substantive Constraints/ ይጠቀሳሉ::
ሥነ ሥርዓታዊ ገደቦች /Procedural Constraints/
የህገ መንግሥትን ማሻሻልን በተመለከተ በቀጥታ በህገ መንግሥት በድንጋጌ ውስጥ የህገ መንግስቱ ማሻሻያ ሃሳብ በማን እና እንዴት እንደሚቀርብ፣ ክርክሮች እና ምክክሮች እንዴት መካሄድ እንዳለባቸው፣ የማሻሻያውን ሀሳብ ስለሚፀድቅበትና ስለሚፀናበት ሂደት በአጠቃላይ ህገ መንግስቱ ስለሚሻሻልበት ሥነ ሥረዓት በህገ መንግሥት ውስጥ በዝርዝር የሚቀመጥበት ሂደት ነው፡፡
በህገ መንግስቱ የተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ በግልፅ ገደቦች በማስቀመጥ /Express Substantive Constraints/
በህገ መንግስቱ አጠቃላይ ህገ መንግስቱ ስለሚሻሻልበት ሥነ ሥረዓት ከሚያትትበት ድንጋጌ በተጨማሪ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ማሻሻል እንደማይቻል በተለየ ስለጉዳዩ በሚያካትቱ አንቀፆች ውስጥ በግልፅ በማካተት የሚደነግግበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ግልፅ ገደብ እንደየ አገራቱ እድገት፣ የህብረተሰብ ብዝሀነት፣ ስብጥር፣ ባህሪ፣ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሁኔታ እና ታሪክ ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን በአብዝኛው የአገሪቱን ህገ መንግስታዊ መዋቅር፣ መሠረታዊ መብቶችን እና ነፃነቶችን፣ የሰዎችን ክብር፣ የሕግ የበላይነት፣ የአገር ድንበር ሉአላዊነትን፣ የሥልጣን ክፍፍልን እና ህገ መንግሥትን ስለ ማሻሻል የሚደነግጉ የህገ መንግሥት ድንጋጌዎች ማሻሻል እንደ ማይቻል በግልፅ የሚከለክሉበት ሁኔታ ነው፡፡
ህገ መንግሥት ማሻሻል ላይ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ
አሜሪካ
አሜሪካ በአጠቃላይ 27 ጊዜ የህገ መንግሥት ማሻሻያ ያደረገች ሲሆን ህገ መንግስቱን ለማሻሻል የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤቱ (ኮንግረስ) እና በሕግ መወሰኛ ምክርቤት (ሴኔት) የሁለት ሶስተኛ ድምፅ ድጋፍ ሲያገኝ ወይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ ህገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲጠይቁ ነው፡፡ በአሜሪካ የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ የሚፀድቀው የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳቡን በሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ወይም ክልሎች በሚያደርጉት ጉባኤ ሶስት አራተኛ ድምፅ ሲያፀድቁት ነው፡፡ ነገር ግን የአሜሪካ ህገ መንግሥት የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች በሕግ መወሰኛው ምክርቤት ውስጥ እኩል ውክልና ሚሰጣቸውን የሕግ ድንጋጌ ያለ ክልሎቹ ሙሉ ስምምነት ማሻሻል እንደማይቻል በግልፅ ደንግጎ ይገኛል፡፡
ጀርመን
የጀርመን ህገ መንግሥት ሊሻሻል የሚችለው የህገ መንግስቱ ማሻሻያ ሀሳብ በጀርመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (Bundestag) እና የሕግ መወሰኛ ምክርቤት (Bundesrat) በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ድጋፍ ሲያገኝ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የጀርመን ህገ መንግሥት የመንግስቱን አወቃቀር፣ የሕግ የበላይነትን፣ የሰውን ክብር፣ ዲሞክራሲን፣ መሠረታዊ የሰበአዊ መብቶችን እና ነፃነቶችን እና የመንግሥት መዋቅርን የሚመለከቱ ሕግችን ማሻሻል እንደማይቻል በግልፅ ይደነግጋል፡፡ እነዚህን ህጎች በፍፁም ማሻሻል የማይቻል አይነኬ ህጎች (eternity clause) ይባላሉ፡፡
ደቡብ አፍሪካ
የደቡብ አፍሪካ ህገ መንግሥትም እንደ አሜረካ ህገ መንግሥት የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤቱ (ኮንግረስ) እና በሕግ መወሰኛ ምክርቤት (ሴኔት) የሁለት ሶስተኛ ድምፅ ድጋፍ ሲያገኝ ወይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ ህገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲጠይቁ እና የማሻሻያ ሃሳቡ የሚፀድቀው የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳቡን በሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ወይም በክልሎች በሚያደርጉት ጉባኤ በሶስት አራተኛ ድምፅ ሲያፀድቁት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ህገ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ መብቶችን መሻሻልን በተመለከተ ግልፅ የሆነ ክልከላ ባያስቀምጥም ነገር ግን ለማሻሻል ጥብቅ የሆነ ሥነ ሥረዓት እና ከፍተኛ ድምፅ እና ድጋፍን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ይደነግጋል፡፡
ህንድ
በህንድ ሕግ መንግሥትን ለማሻሻል ቀላል መንገድ የምትከተል ሲሆን ይህም ህገ መንግሥትን የማሻሻል ሀሳብ ከሁለቱ ምክር ቤቶች ወስጥ በአንዱ እንዲሻሻል የማሻሻያ ሀሳብ ሲቀርብ እና የቀረበው የማሻሻያ ሀሳብ ከሁለት ሶስተኛ ያላነሰ የምክር ቤቶች አባላት በተገኙበት ስብሳባ ሁለቱም ምክር ቤቶች በተናጠል በሚያደርጉት ጉባኤ የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳቡን በአብላጫ ድምፅ ሲያፀድቁት ሊሻሻል እደሚችል ይደነግጋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ ስለ ሚቀርብበት ሁኔታ
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 104 ህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ ስለ ማመንጨት በሚለው ድንጋጌው ሥር የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ በሶስት መንግድ ሊቀርብ እንደሚችል የሚያስቀምጥ ሲሆን ይህም፡-
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ከደገፈው
- በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ደምፅ ከደገፈ ወይም
- ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ በአንድ ሶስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የደገፉ ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብ እና የሕግ መንግስቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች እንደሚቀርብ ይደነግጋል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ስለ ሚሻሻልበት ሥነ ሥረዓት
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 105 ህገ መንግስቱን ስለ ሚሻሻልበት ሁኔታ የሚደነግግ ሲሆን ይህም በሁለት መንገድ እንደሚሻሻል ያስቀምጣል፡፡ ይህም፡-
1. በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 105/1 መሠረት በህገ መንግስቱ በምእራፍ 3 የተዘረዘሩት መብቶች እና ነፃነቶች በሙሉ፣ ስለ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ አቀራረብ የሚያትተው ድንጋጌ አንቀጽ 104 እና ህገ መንግስቱ ስለ ሚሻሻልበት ሥነ ሥረዓት የሚደነግገው አንቀጽ 105 የሚሻሻሉት
- ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት እና
- የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በየፊናቸው የቀረበውን የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያፀድቁት ብቻ ነው፡፡
2. በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 105(1) ሥር ከተዘረዘሩት ሁኔታዎች ውጪ ያሉት የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁት እና
- ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ክልሎች ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁት ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡
ማጠቃለያ
የኢፌድሪ ህገ መንግሥት የሚሻሻልበትን ሂደት በራሱ የደነገገ ሲሆን ህገ መንግስቱ መሻሻል የሚችለው ከላይ የተጠቀሱት ህጋዊ ሂደቶችን ተከትሎ ብቻ እንደሆነ እና ከተደነገገው ሂደት ውጪ ህገ መንግስቱ ሊሻሻል እንደማይችል ከእነዚሁ የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ