ቀለብ የመስጠት ግዴታ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የሰው ልጅ በህይወት ሲኖር ኑሮውን ለመግፋት በርካታ ነገሮች የሚያስፈልጉት እንደመሆኑ ሁሉም እንደአቅሙ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት የራሱን እና የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ገቢ ለማግኘት ጥረት ማድረጉ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት እና ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያስችል ገቢ ማመንጨት የማይችሉበት ሁኔታ መኖሩ የነባራዊው አለም እውነታ ነው፡፡ በዚህ መልኩ መሥራትና የእራሳቸውን ገቢ በማንጨት ኑሯቸውን መግፋት የማይችሉ ሰዎች ፈታኝ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ታሳቢ በማድረግ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቀለብ የመስጠት ግዴታን እንደመፍትሄ አካቷል። በዚህ አጭር ጽሁፍ የቀለብን ምንነት፣ ቀለብ የማግኘት መብትን እና የመስጠት ግዴታን ከተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንፃር በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

የቀለብ ምንነት

በዘልማድ ባለው የቃል አጠቃቀም “ቀለብ” የሚለው ቃል በአብዛኛው ከምግብ ጋር በተገናኘ ጥቅም ላይ ሲውል ይስተዋላል፡፡ ሆኖም የቤተሰብ ህጉ ቀለብን የደነገገበት እሳቤ ከዚህ ሰፋ ያለ ነው፡፡ የቤተሰብ ህጉ ስለ ቀለብ ሲደነግግ የቀለብ ተቀባዩን ሁኔታና የአካባቢውን ልማድ መሠረት በማድረግ ለምግብ፣ ለመኖሪያ፣ ለልብስ፣ ለጤና መጠበቂያ እና እንደሁኔታው ለትምህርት የሚያስፈልገውን እንደሚያካትት ከአንቀጽ 197 ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ቀለብ የሚለው ቃል ምግብን ብቻ በመግለፅ የተወሰነ ሳይሆን እንደቀለብ ተቀባዩ ሁኔታ መሠረታዊ ፍላጎትን ያካተተ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ቀለብ የመስጠት ግዴታ በዋናነት የሚፈጸመው የቀለቡን ገንዘብ ለተቀባዩ በመስጠት ሲሆን መጠኑም ቀለብ ተቀባዩ ያለበትን ችግር እና የቀለብ ሰጪውን አቅም በማገናዘብ የሚወሰን ይሆናል፡፡

ቀለብ የሚጠየቅበት ሁኔታ

ቀለብ አንድ ሰው ስለፈለገ ብቻ የሚጠይቀው አይደለም፡፡ ይልቁንም ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚኖረው ቀለብ ተቀባዩ ሰርቶ ለኑሮ አስፈላጊ የሆነ ገቢ ለማግኘት አቅም የሌለውና በችግር ላይ የወደቀ ሲሆን ብቻ እንደሆነ የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 201 ደንግጓል፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታ

ቀለብ የመስጠት ግዴታ በቀጥታ በወላጆችና በተወላጆች እንዲሁም በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ሲሆን በእህትና ወንድማማቾች መካከልም ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዳለ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ቀጥታ የጋብቻ ዝምድና የሚባለው ባል ከሚስቱ ወላጆችና ተወላጆች ወይም ሚስት ከባሏ ወላጆችና ተወላጆች ጋር ያላቸውን የጋብቻ ዝምድና ሲሆን ጋብቻው ከሞት ውጪ በሆነ ምክንያት ሲፈርስ ግን ይህ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ቀሪ ይሆናል፡፡ እነዚህ ዘመዶች ሁሉም በአንድ ጊዜ ለቀለብ ተቀባዩ ቀለብ መስጠት አይጠበቅባቸውም፡፡ ይልቁንም ቀለብ የመስጠት ግዴታው በህጉ አንቀጽ 210 ሥር በተቀመጠው ቅድም ተከተል የሚፈፀም ነው፡፡ በዚህ መሠረት፡-

  • 1ኛ የቀለብ ተቀባዩ ባል ወይም ሚስት
  • 2ኛ የቀለብ ተቀባዩ ተወላጆች እንደየደረጃቸው
  • 3ኛ የቀለብ ተቀባዩ ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች እንደየደራጃቸው
  • 4ኛ የቀለብ ተቀባዩ ወንድሞችና እህቶች
  • 5ኛ የቀለብ ተቀባዩ የጋብቻ ተወላጆች እንደየደረጃቸው
  • 6ኛ የቀለብ ተቀባዩ የጋብቻ ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች እንደየደረጃቸው

ባለው ቅደም ተከተል የሚፈፀም ይሆናል፡፡ በህጉ በተደነገገው ቅደም ተከተልም ቢሆን ቀለብ ሰጪዎች ቁጥራቸው ከአንድ በላይ ሊሆን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ቀለብ ተቀባዩ አንዱን በመምረጥ ቀለብ ሊጠይቅ የሚችል ሲሆን የጋራ ቀለብ ሰጪዎችም መካከላቸው አንዱ ለቀለብ ተቀባዩ ቀለብ እንዲሰጥ የጋራ ስምምነት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ ቀለብ ተቀባዩም ይህንን ስምምነት ከተቀበለ ከባድ ምክንያት ከሌለው በስተቀር ከቀሪዎቹ ቀለብ ሰጪዎች መጠየቅ እንደማይችል በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 211 ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ከብዙ ቀለብ ሰጪዎች መካከል አንደኛው ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቀለብ ሲሰጡ የነበረ ከሆነ ሳይከፍሉ የቀሩት ድርሻቸውን እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡

ከጉዲፈቻ ጋር በተያያዘ ጉዲፈቻ አድራጊ ቤተዘመዶች ቀለብ ለመስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ካልሆኑ በስተቀር ጉዲፈቻ የተደረገ ልጅ፣ የጉዲፈቻ ተደራጊው ልጅ ባል ወይም ሚስት እንዲሁም የቀጥታ መስመር ተወላጆች ከጉዲፈቻ ተደራጊውን ልጅ የስር ወይም የቀደምት ወላጆች ቤተዘመዶች ቀለብ መጠየቅ የማይችሉ ሲሆን በተመሳሳይ የቀደምት ቤተሰቦች ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ከዘመዶቻቸው ቀለብ ማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ጉዲፈቻ የሰጡትን ልጅ ቀለብ ሊጠይቁ አይችሉም፡፡

ሌላው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ስጦታ ተቀባይ ሲሆን ስጦታ ሰጪው ሰርቶ ለማግኘት አቅም ሲያጣና ፍጹም ድህነት ላይ ሲወድቅ ስጦታ ተቀባይ ቀለብ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት የፍትሐብሔር ሕግ ስለ ስጦታ በሚደነግግበት ክፍል በቁጥር 2458 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የስጦታ ውሉ ላይ እንኳን ቀለብ የመስጠት ግዴታ ስምምነት ባይኖርም ይህ ግዴታ ቀሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ስጦታ ሰጪ ቀለብ የመቀበል መብቱን ከሌሎች ግዴታ ካለባቸው ሰዎች መውሰድ የሚችል ሲሆን ይህ በሆነ ጊዜ ቀለቡን የሰጠው ሰው የሰጠውን ቀለብ ከስጦታ ተቀባዩ ሊቀበል እንደሚችል የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2458(3) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የቀለብ ገንዘብ ሊተላለፍና ሊያዝ የማይችል ስለመሆኑ

በመርህ ደረጃ ለቀለብ የሚከፈል ገንዘብ ሊተላለፍ ወይም በምንም ሁኔታ ሊያዝ አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ ቀለብ ተቀባዩ ላለበት ችግር አሳቢ ለሚሆኑ ለእርዳታ ለተቋቋሙ ድርጅቶች እንዲሁም ለቀለብ ተቀባዩ ኑሮ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ላበደሩ ሰዎች የቀለብ ገንዘቡ ሊተላለፍ እንደሚችል የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 205 ያሳያል፡፡ ሌላው ማንም ሰው ሊያውቀውና ሊገነዘበው የሚገባው የቀለብ ገንዘብ የማይጠራቀም መሆኑን ነው፡፡ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 206 መሠረት ቀለብ ተቀባዩ ለኑሮ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ካላቀረበ በስተቀር ቀለቡን መቀበል ካለበት ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሶስት ወራት ውስጥ ቀለቡን ያልተቀበለ ወይም ያልጠየቀ እንደሆነ የተጠራቀመውን ቀለብ መጠየቅ አይችልም፡፡

ቀለብ ተቀባይ መብቱን የሚያጣበት ሁኔታ

በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 200 መሠረት ቀለብ ተቀባይ የሆነ ሰው በቀለብ ሰጪው ላይ ወይም በቀለብ ሰጪው ወደላይ እና ወደታች በሚቆጠሩ ወላጆች ወይም ተወላጆች ወይም ባል ወይም ሚስት ህይወት ወይም ንብረት ላይ የወንጀል ተግባር የፈጸመ ወይም ለመፈጸም የሞከረ እንደሆነ ቀለብ የማግኘት መብቱን የሚያጣ ይሆናል፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታን አለመወጣት የሚያስከትለው ተጠያቂነት

ከላይ እንደተገለፀው ቀለብ የመስጠት ግዴት ከሕግ የመነጨ ሲሆን ባለመብቱና ግዴታ ያለበት ወገን የቀለብ አሰጣጡን በተመለከተ በመስማማት ውል ሊፈጽሙ እንደሚችሉ በህጉ ላይ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከቀለብ አሰጣጥም ሆነ አቀባበል ጋር በተያያዘ በቤተሰብ ህጉ ላይ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች በሚቃረን መልኩ ስምምነት ሊደረግ እንደማይችል በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 214 ላይ የተደነገገ እንደመሆኑ ይህን የሚቃረን ስምምነት ቢደረግም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

በሌላ በኩል በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 658 መሠረት ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ማንኛውም ሰው ያለ በቂ ምክንያት በሕግ መሠረት ሊሰጥ የሚገባውን ቀለብ፡-

  • ለባለመብቶቹ አልሰጥም ያለ ወይም መስጠትን ያስተጓጎለ
  • የፍቺ ውሳኔ እስከሚሰጥ ጊዜ ድረስ የፍቺ ጥያቄ ላቀረበ የትዳር ጓደኛ አልሰጥም ያለ ወይም መስጠትን ያስተጓጎለ
  • በሕግ መሠረት ወይም በውል በገባው ግዴታ መሠረት ከጋብቻ ውጭ ላስረገዛት ሴት ወይም ከጋብቻ ውጭ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አብሮት ለኖረ ሰው ወይም ከጋብቻ ውጭ ለተወለደው ልጅ ሊያሟላ የሚገባውን የገንዘብ ግዴታ ያልተወጣ ከሆነ

የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሲሆን የግል አቤቱ ሲቀርብ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ ይችላል፡፡

ማጠቃለያ

ቀለብ ሰርቶ ፍላጎቱን ለማሟላት የሚያስፈልገውን ገቢ ማግኘት የማይችል ሰው ከሥጋ ወይም ከቀጥታ የጋብቻ ዘመዶቹ መሠረታዊ ፍላጎቱ እንዲሟሉለት በሕግ የተጣለ ግዴታ ሲሆን ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ማንኛውም ሰው ግዴታውን በአግባቡ የመወጣት የሕግም የሞራልም ግዴታ እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ