መግቢያ
መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገትን ከማፋጠን አኳያ ክፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት የራሱ ገቢ ያስፈልገዋል፡፡ መንግሥት ገቢ ከሚያሰባስበብበት የገቢ ምንጭ መካከል ታክስ አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው ታክስ ዋናው የመንግሥት የፋይናንስ ምንጭ በመሆን የአንድ አገር ኢኮኖሚ ልማትንና እና እድገት የጀርባ አጥንት ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሞዎች የሚገልጹት፡፡ በሀገራችን የታክስ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ የታክስ ዓይነቶች በሁለት ምድብ የተዋቀሩ ሲሆኑ እነዚህም ቀጥታ ታክሶች እና ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች ናቸው፡፡ ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች ከሚባሉት ውስጥ ተጨማሪ እሴት ታክስ አንዱ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የተጨማሪ አሴት ታክስ ምንነት፣ የታክስ ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት፣ አዳዲስ የተካተቱ ጉዳዮች እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ ግብይቶች የሚሉትን እንመለከታለን፡፡
የተጨማሪ አሴት ታክስ ምንነት
የተጨማሪ ዕሴት ታክስ መሰረቱ ሰፊ የሆነ በፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚጣል ቀጥታ ያልሆነ ታክስ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ በእቃዎች እና በአገልግሎቶች ላይ በሚደረጉ ተጨማሪ እሴቶች ላይ የሚጣል የታክስ ዓይነት ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ የፍጆታ ታክስ (consumption tax) በሚባለው ታክስ ዓይነት ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ የእቃዎች እና አገልግሎቶች ዋጋ በግብይት ሂደቶች ውስጥ በሚጨምርበት ጊዜ በእያንዳንዱ የግብይት ሂደት በተጨመረው እሴት ልክ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰላል፡፡ ይህ ታክስ በእያንዳንዱ የግብይት ሂደት ላይ በመከፈሉ በአንድ እቃ ወይም በአንድ አገልግሎት ላይ በተደጋጋሚ እንደሚጣል ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን በግብዓት ላይ የተከፈልን ታክስ በውጤት ላይ ከተሰበሰበ ታክስ በማቀናነስ ታክስ የሚሰላበት ሥርዓት በመሆኑ ተደጋጋሚ ታክስ እንዳይሰበሰብ ያደርጋል፡፡
ታክሱ ከአስመጪዎችና ጥሬ ዕቃ አምራቾች አንስቶ እስከ ችርቻሮ ድረስ በሚደረጉ የማምረትና የማከፋፈል (የማሰራጨት) ሂደቶች በሁሉም ደረጃዎች በሚፈጠረው ተጨማሪ እሴት ላይ ይሰበሰባል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበሰበው ወይም የሚቀረጠው ምርት ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ወይም የዕቃና የአገልግሎት ግብይት ሲካሄድ ነው፡፡ ይህ ታክስ በፍጆታ ላይ ወይም በተጠቃሚው ወጪ ላይ የተመሰረተ ታክስ ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጠቃሚ እቃዎችን እና አገልግሎቶችን በሚሸምትበት ወቅት ከሚከፍለው ዋጋ በተጨማሪ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፍላል፡፡ በእያንዳንዱ ግይብት ላይ የሚጨመሩ እሴቶችም ተጠቃለው በመጨረሻ ላይ በሚደረገው ግብይት ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፈልባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት የታክስ አጣጣል እና አሰባሰብ ሕግጋት ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋዮች በመባል የሚታወቁት ለዚህም ታክስ ተመዝጋቢ የሚሆኑት የእቃዎች እና የአገልግሎቶች አቅራቢዎች ናቸው፡፡ በዚሁም መሠረት ዓመታዊ ታክስ የሚከፈልበት ግብይታቸው አንድ ሚለዮን ብር እና ከዚያ በላይ የሆነ ወይም ሊሆን እንደሚችል የሚገመት ሰዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ይሆናሉ፡፡
የመጨረሻ ሸማቾች ከከፈሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ በስተቀር በግብይት ሂደት ውስጥ ይህንን ታክስ ለከፈሉ ሌሎች ሰዎች የከፈሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ይደረግላቸዋል፡፡ ስለዚህም ሸማቾች ከሚከፍሉት ታክስ ውጪ ሌላ የሚከፈል የተጨማሪ እሴት ታክስ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ የሚደለግበትን ሁኔታ ስንመለከት ነጋዴዎች የሚያቀርቡትን እቃዎች እና አገልግሎቶች በሚገዙበት ወቅት የከፈሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ እቃዎቹን እና አገልግሎቶቹን በሚሸጡበት ጊዜ ከሚሰበስቡት ታከስ ላይ የሚቀናነስ ይሆናል፡፡
የታክስ ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት
የተጨምሪ እሴት ታክስ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያለው የታክስ ዓይነት ሲሆን ይህ የታክስ ዓይነት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ተግባራዊ የሆነው በ1994 ዓ.ም (አዋጅ ቁጥር 285/1994) ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በተለያየ ወቅት እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን የማበረታት ሚና አለው፡፡ የካፒታል ዕቃዎችን ሳይጨምር በዕቃ እና አገልግሎት ፍጆታ ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የተጣለው በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ረገድ የተደረጉ ለውጦችን በተለይም የኤሌክትሮኒስ ግብይትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ከታክሱ ነፃ የመሆን መብት አተገባበርም ለውጦች ተደርገውበታል።
አዳዲስ የተካተቱ ጉዳዮች
ነባሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከወጣ 22 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ አስከ አሁን ድረስ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በርካታ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 እነዚህን ለውጦች እንዲያካትት የተደረገበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፡-
- የጉዳዮችን ምክንያታዊነት ፍሰት በተከተለ መልኩ እንዲቀረጽ እና እንዲዋቀር ተደርጓል ፡፡
- የታክስ መርሆች በግልጽ በሚያሳይ መልኩ ተደረጃቶ የተዘጋጀ አዋጅ መሆኑ፡፡
- ራሳቸውን ችለው መደንገግ ያለባቸው በተለይ እንደ ግብዓት ዓይነት ታክሶች ራሳቸውን ችለው እንዲደነገጉ ሆኗል፡፡
- ነባሩ አዋጅ 285/94ን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 79/95 ላይ የተቀመጡ በአዋጁ ላይ የሌሉ ነገሮች በደንቡ ላይ ተካተው የነበሩ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ እነዚህም ከደንቡ ወጥተው በአዋጁ ላይ መደንገግ ስለነበረባቸው እንዲመጡ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ የታክስ ማስታወቅና የታክስ መክፈል ሥርዓት፣ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣ የታክስ ደቢትና ክሬዲት አያያዝ እና መሰል ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡
- የአዋጁ ተፈፃሚነት ወሰን ሰፋ እንዲል ተደረጎ ተደንግጓል፡፡ በማንኛውም የዕቃ ግዥ ወይም አገልግሎት የተከፈለ ማንኛውም አቅርቦት ላይ፣ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ወይም የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው አገልግሎቶችን ሩቅ ሆነው አገር ውስጥ ላሉ ተጠቃሚዎች የሚያቀርቡ ስለሆነ ኢትዮጵያ በምትከተለው የዴስትነሽን (መዳረሻ) መርህ መሠረት አቅርቦቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከሆነ ድረስ ታክስ የሚመለከታቸው እንደሆነ በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
- ለተጨማሪ እሴት ታክስ የሚታየው ዋጋ፡- የመነሻ ዋጋ የሚለው ትርጉም በግልጽ መደንገጉ እንደ አንድ አዲስ ነገር የሚወሰድ ሲሆን በተጨማሪ እሴት ታክስ ዕቃ ወይም አገልግሎት ዋጋ የምንለው፡-
- ማንኛውም ሰው ለአቅረቦቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የከፈለው የገንዘብ መጠን በተለይም ዕቃ አቅርቦት በሚሆንበት ጊዜ የዕቃ አቅርቦቱ መያዣ ዕቃ ካለው የዕቃ መያዣው ተመላሽም ቢሆንም እሱን ታሳቢ ሳያደርግ የዕቃ መያዣውን ጭምር ታሳቢ ተደርጎ የሚከፈለው ዋጋ በተጨማሪ እሴት ታክስ የአቅርቦቱ ዋጋ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
- በአቅርቦቱ ምክንያት የተከፈሉ ሌሎች ማናቸውም የታክስ አይነቶች ቀረጥ፣ ኤክሳይስ ታክስ፣ ሱር ታክስ እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያዎች (ሰርቪስ ቻርጅ) የሚሏቸው ክፍያዎች ካሉ እነሱንም ሁሉ አጠቃሎ ለተጨማሪ እሴት ታክስ እንደ ዋጋ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
- ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የሚሆኑ ምርቶች በተመለከተ፡- የተጨማሪ እሴት ታክስን ነፃ የማድረግ ዓላማ ገቢ መጠኑ ዝቅተኛ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ጫና ለመቀነስ እና የውጭ ንግድን (ኤክስፖርትን) ለማበረታት ተብሎ የተለያዩ ዘርፎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሆነው ቀይተዋል፡፡ ነገር ግን የነበረው የታክስ ዓላማ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ሆኖ ብዙዎችን ከታክስ ነፃ አድርጎ ስለነበር ከዚህ ላይ ማሻሻያ ማድረጉ፡፡ በዚህም መሠረት ነፃ ተደርገው ከነበሩት ውስጥ ትክክለኛ ወይም ምክንያታዊ በቂ የሆነ ምክንያት የሌላቸው ወደ ታክሱ እንዲካተቱ አደርጓል፡፡
- ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የማድረግ (የመድሀኒት አቅርቦትን በተመለከተ) ሥልጣን ለገንዘብ ሚኒስቴር ተሰጥቶ የቆየ ሥልጣን ነበር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ የመድኃኒት እና ፈንድ አቅርቦት መሥሪያ ቤት ብቻ ሥልጣኑ ተዘዋውሯል፡፡
- ነፃ የመሆን መብት በቀጥተኛ ጥቅም ላይ በሚውሉ የመጨረሻ ምርቶች ላይ እንጂ በግባዓቶች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት እነዚህ ባማከለ መልኩ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መሆን ያለባቸው ተብለው የተዘረዘሩ ግብይቶች ምንምን እንደሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 10 እና አባሪ 2 ላይ ተደንግጓል፡፡
- የማሳወቂያ እና የመክፈያ ጊዜ አንድ ወር መሆኑ፡- ይህም ግብር ከፋዮች በአካል በመገኘት ሳይሆን ቴክኖሎጂ መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
- ለተጨማሪ እሴት ታክስ ለመመዝገብ ያለው መስፈርት ሲሆን በግዴታ የሚመዘገቡት ዓመታዊ የሽያጭ መጠን (threshold) ሁለት ሚሊዮን ብር የሆነ ሲሆን በፈቃደኝነት መመዝገብ የሚችሉበት መስፈርት ደግሞ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን (threshold) አንድ ሚሊዮን በሚል አዋጁ አስቀምጧል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በታች ያሉት የሽያጭ ታክስን (ቲኦቲን) ሰብስበው ለሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ ገቢ እንዲያደርጉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
- መሠረታዊ ድንጋጌዎችና አስተዳደር ድንጋጌዎችን ለይቷል፡፡ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ላይ የደነገገ ሲሆን የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ አስተዳደር በተመለከተ ተፈፃሚነት እንዲኖረው መደረጉ (አዋጅ ቁጥር 1341 /2016 አንቀጽ 57) ፡፡
- በኤሌክትሮኒክስ አማካኝነት የአገልግሎት አቅርቦት መከናወን በአዋጁ ሽፋን ማግኘቱ፡- በኤሌክትሮኒስ ዘዴ ግብይት በስፋት እየተካሄደ ነው፡፡ በድኅረ ገጽ፣ የኢንተርኔት ፖርታል፣ ጌት ወይ፣ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ግብይት የሚፈፀምበት መደብር፣ የገበያ ቦታ፣ የማከፋፈያ መድረክ ወይም ሌላ ተመሳሳይ መንገድ አቅራቢው ሩቅ ሆኖ በሩቅ የሚሰጡ አገልግሎቶች ወይም በኤለክትሮኒስ ዘዴ የሚታገዙ ዕቃዎችን በሌላሰው አማካኝነት ለ3ኛ ወገን የሚተላለፉበት ዘዴ በመሆኑ ይኸ ግብይት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለ ስለሆነ ይህ በአዋጁ ተካቷል፡፡ ምክንቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ግብይቶችን የሚፈጽሙ አካላት አሉ፡፡ እነዚህን ግብይቶች የሚያስፈጽሙ ሌሎች አገበያዮች አሉ፡፡ ምርቱን የሚያቀርቡ ለምሳሌ፡- አማዞን፣ ጎግል ፕሌይ፣ አፕል ስቶር እና የመሳሰሉት እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ግብይት ሊያካሂዱ ስለሚችሉ ታክስ መመዘገብ አለባቸው ( አንቀጽ 2 እና 25)፡፡
ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ ግብይቶች
የሚከተሉት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የተደረጉ አቅርቦቶች ናቸው፡፡
- በመኖሪያ ቤትነት ለሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ያገለገለ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ፣
- ከሁለት ወራት በታች ለሆነ ጊዜ የተከራየን ቤት ሳይጨምር የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣
- ፈቃድ በተሰጠው ባንክ ወይም የፋይናንስ ተቋም ወይም በሌላ ማናቸውም ሰው የሚሰጥ የፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት (ብድር፣ ክሬዲት ወይም የክሬዲት ዋስትና አገልግሎት መስጠት ወይም መነገድ፤ ዕዳ መሰብሰብን እና ተሰብሳቢ ሒሳብ መሸጥን ሳይጨምር ገንዘብ፣ ተቀማጭ ሒሳብን፤ ቁጠባንና ሌሎች ተመሳሳይ ሒሳቦችን፣ ክፍያዎችን፣ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባራትን (የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አግልግሎትን ሳይጨምር)፣ ዕዳን፣ ቼክን ወይም የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶችን የሚመለከቱ ተግባራት፤ የአክስዮን ድርሻ፣ ቦንድ እና ሌሎች የግዴታ ምስክር ወረቀቶች መገበያትና ከእነዚህ ጋር የተያያዘ ማናቸውም ምርጫ ወይም ዋስትና፤ የኢንቨስትመንት ፈንድ ማስተዳደር፤ የጡረታ ፈንድ፣ ፕሮቪደንት ፈንድ፣ የመድን ፈንድ ማስተላለፍ)፣
- አቅራቢው የትምህርት ፕሮግራም ለሚከታተሉ ተማሪዎች የሚያቀርባቸውን ዋጋቸው ለፕሮግራሙ የሚከፈለው ዋጋ ውስጥ የተካተተ የመማሪያ መፃሕፍት፣ ቁሳቁሶች ወይም መሣሪየዎችን ጨምሮ የትምህርት ፕሮግራሞች አቅርቦት (ዕውቅና የተሰጠው፣ ፕሮግራሙ ዲግሪ ወይም ተመሳሳይ የብቃት ማስረጃ የሚያስገኝ ከሆነ)፣
- ፈቃድ በተሰጠው አገልግሎት ሰጪ የሚከናወን የሕፃናት ማቆያ አገልግሎት፣
- የሕክምና አገልግሎት፣
- በሕክምና የሚታዘዙ መድኃኒቶች አቀርቦት፣
- የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት፣
- ቅዱሳት መፃሕፍትን ማቅረብን ጨምሮ በእምነት ተቋማት የሚሰጡ ከእምነቱ ወይም ከሃይማኖቱ ሥርዓት ጋር በቀጥታ የተያያዙ አገልግሎቶች፣
- የሕክምና መገልገያ፣ የህክምና መሣሪያ፣ የወባ አጎበር አቅርቦት፣
- ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች የሚቀርቡ በእርዳታ የሚሰጡ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች
- ለግብርና አገልግሎት ብቻ የሚውል የምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የጸረ ተባይ፣ የጸረ አረም፣ የአፈርን አሲዳማነት ለመከላከል የሚውል ካልሲየም ሃይደሮኦክሳይድ (ውህድ ኖራ) ወይም የፈንገስ መከላከያ ኬሚካሎች፣
- ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር የሚያስገቡት ወይም ከሀገር ውስጥ የሚገዙት ዕቃ (በሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ በተደነገገው መሠረት )፣
- የኤሌክትሪክ ኃይል (ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ ከሚወሰን ወርሀዊ ፍጆታ ያልበለጠ) እና የታሸገ ውሃን ሳይጨምር የውሃ አቅርቦት፣
- 60% እና ከዚያ በላይ ሠራተኞቹ አካል ጉዳተኛ የሆነ ሰው የሚያቀርባቸው ማናቸውም አቅርቦቶች፣
- ሚኒስቴሩ በሚያቀርበው ሀሳብ መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታክሱ ነፃ የሚደረጉ ዕቃዎች፣
- አምቡላንስ እና የእሳት አዳጋ ተሽከርካሪዎች እና መሣሪያዎች አቅርቦት፡፡ ለዚህም ማብራረያ አባሪ 2 ን ይመለከቷል፡፡
- በተጨማሪ ከታክሱ ነፃ የሆነ ወደ ሀገር የሚገባ ዕቃ በአዋጁ አንቀጽ 11 በተደነገገው መሠረት ሲሆን ከአዋጁ ጋር በተያያዘው አባሪ 3 የተዘረዘሩት ወደ ሀገር የሚገቡ ዕቃዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ተደርገዋል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ታክስ መክፈል ለሀገር ዕድገት እና ለዜጎች ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በሀገራችን ካሉት የታክስ ዓይነቶች ተጨማሪ እሴት ታክስ አንዱ ሲሆን ይህን ታክስ ለመንግሥት መክፈል ግዴታ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊያውቅ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ይህን አውቆ በወቅቱ አለመክፈል ቅጣቶችን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ የሚጠበቅበትን በወቅቱ መክፈል አለበት፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ