የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓትን ህግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

መንግስታዊ አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ ማናቸውም የመንግሥት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት በተቀመጡ መሠረታዊ መርሆዎች ተመላክቷል፡፡ በዚህ መርህ የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያወጠጧቸው መመሪያዎች እና የሚሰጧቸው ውሳኔዎች በሕግ የሚመሩ መሆን አለባቸው፡፡ በሀገራችን እነዚህ መመሪያዎች የሚወጡበት እና ውሳኔዎች የሚሰጡበት ሂደት በአስተዳደር ሥነ ሥርአት ሕግ የሚመራ ይሆናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለ አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ምንነት፣ መርሆዎች፣ መመሪያ የማዉጣት ሥልጣን፣ የመመሪያ አመዘጋገብ ሥርዓትን እንዲሁም በተለያየ አካል የሚሰጡ አስተዳደራዊ ዉሳኔዎችና ሊከተሉ ስለሚገባው ሥነ ስርዓት እንዳስሳለን፡፡

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓትን ሕግ ምንነት

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ከሥነ ሥርአት ህጎች (procedural law) የሚመደብ ሲሆን የአስተዳደር ተቋማት የሚያወጧቸው መመሪያዎች እና የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የሚመሩበትን እንዲሁም ቅሬታዎች የሚፈቱበትን ሂደት የሚደነግግ ሕግ ነው፡፡ የአስተዳደር ተቋም ማለት አስፈፃሚ አካል ሆኖ በሕግ የተደራጀ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲሆን ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆኑ የከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን እንደሚጨምር በፌደራል አስተዳደር ሥነ ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 2(1) ሥር ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

የአስተዳደር ተቋማት መመሪያ የማውጣት ሥልጣንና ሂደት

መመሪያ ማለት የሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት በአስተዳደር ተቋም የሚወጣ እና በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል የሕግ ሰነድ ሲሆን በሥራ ላይ ያለ መመሪያን የሚያሻሽል ወይም የሚሽር የሕግ ሰነድንም እንደሚጨምር ከአዋጁ አንቀጽ 2(2) መረዳት ይቻላል፡፡ ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ከማውጣቱ በፊት መመሪያ ለማውጣት ሥልጣን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይገባዋል (አንቀጽ 8)፡፡ የአስተዳደር ተቋሙ መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ያለው መሆኑ ሲረጋገጥ ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ማዉጣት አለበት፡፡ ይህም እናት ህጉ መመሪያ እንዲያወጣ በአስገዳጅ ሁኔታ በደነገገ ጊዜ በ3 ወራት ውስጥ አስገዳጅ ባልሆነ ሁኔታ በተደነገገ ጊዜ ደግሞ በተገቢው ጊዜ ውስጥ መመሪያውን ማውጣት አለበት፡፡ አንድ የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣው የሚገባዉን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ሳያወጣ ቢቀር መመሪያውን እንዲያወጣ ማንኛውም ሰው በጽሑፍ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ የአስተዳደር ተቋም በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ መመሪያውን የማውጣት ሂደት መጀመር ወይም መመሪያውን ማውጣት የማይችል ከሆነ ምክንያቱን በመግለፅ ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ አለበት፡፡

መመሪያ የሚያወጣ ተቋም በቅድሚያ ስለሚያወጣው ረቂቅ መመሪያ ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ፣ በተቋሙ ድህር ገፅ እና በሌሎች መገናኛ ብዙሀን ዝርዝር መረጃ የያዘ ማስታወቂያ ማውጣት ይገባዋል (አንቀጽ 8)፡፡ በተጨማሪም የመመሪያውን ረቂቅ ለሚመለከታቸው የአስተዳደር ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአስተያየት መላክ አለበት፡፡ ተቋሙ ለአስተያየት መስጫ የሚወስነው ጊዜ ካበቃ በኋላ አስተያየት ለመስጠት በቂ ጊዜ የተመደበለት የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ግብአት ማሰባሰብ ይጠበቅበታል፡፡

በተጨማሪም የሚወጣው መመሪያ ርእሰ ጉዳይ፣ የመመሪያውን አወጣጥ መርሃ ግብር፣ የረቂቅ መመሪያው ዝግጅት ሚገኝበትን ደረጃ፣ የታተሙ ማስታወቂያዎች ካሉ፣ አስተያየት ስለሚቀርብበት ጊዜ፣ የተሰበሰቡ አስተያየቶችንና በአስተያየቶቹ ላይ የተወሰዱ አቋሞችን በዝርዝር በመዝገብ አደራጅቶ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ይህን ሂደት መመልከት የፈለገ ማንኛዉም ሰው የተደራጀዉን ሰነድ መመልከት ወይም አስፈላጊውን ወጪ ሸፍኖ ኮፒ መውሰድ ይችላል፡፡

በመጨረሻም ረቂቅ መመሪያውን ከማፅደቁ በፊት ለአስተያየት ለፍትሕ ሚኒስቴር መላክ ያለበት ሲሆን ሚኒስቴሩ በ15 ቀናት ውስጥ ያለውን አስተያየት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡

ሚኒስቴሩ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ አስተያየት ካልላከ አስተያየት እንደሌለው ተቆጥሮ የማፅደቁ ሂደት ይቀጥላል፡፡ መመሪያ ከፀደቀም በኋላ ከነማብራሪያ ፅሁፉ ለፍትሕ ሚኒስቴር ተልኮ መመዝገብ አለበት፡፡ ይህም መመሪያውን ለላከው አስተዳደር ተቋም እንዲያውቀው መደረግ ያለበት ሲሆን ከዚህ ቀን ጀምሮ በተቋሙ ድህረ ገፅ ላይ በመጫን፣ አሳትሞ ለሚመለከታቸው አካላት በመላክ፣ ቅጂውን ማግኘት የሚፈልግ ሰው መመሪያ ባለበት መመልከት እንዲችል ወይም ወጪውን ሸፍኖ ኮፒ ማግኘት እንዲችል በማመቻቸት ለሕዝብ ክፍት እና ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ አለበት፡፡

በሌላ በኩል ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በሥራ ላይ የነበረ መመሪያን ይህ አዋጅ በወጣ ከ90 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለፌደራል የፍትሕ ሚኒስቴር በመላክ እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ ጥሏል፡፡ በዚህ አግባብ ያልተመዘገበ እና በድህረ ገፅ ላይ ያልተጫነ ማናቸውም መመሪያ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡

መመሪያ ለሕዝብ ግልፅ ማድረግ የማይፈቀድባቸው ሁኔታዎች

አዋጁ አንቀጽ 11 ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ሲያወጣ የተጠቀሰውን ሂደት የማይከተልባቸው ልዩ ሁኔታዎችን ደንግጓል፡፡ ይኸውም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በመኖሩ በህጉ የተቀመጡ ግዴታዎቹ ውስጥ ለማለፍ ጊዜ የማይፈቅድ ሲሆን፣ ስለመመሪያው ቅድመ ማስታወቂያ ማውጣቱ የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ሲገኝ እንዲሁም ቅድመ ማስታወቂያ ማውጣቱ የመመሪያውን ተፈፃሚነት ፋይዳ ቢስ የሚያደርግ ሆነ ሲገኝ ናቸው፡፡ መሰል ሁኔታዎች ሲኖሩ ተቋሙ ምክንያቱን የያዘ ዝርዝር መግለጫ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡

አስተዳደራዊ ጥያቄዎችና ውሳኔዎቹ የሚመሩበት መርሆች

አስተዳደራዊ ውሳኔ ማለት መመሪያ ማውጣትን ሳይጨምር የአስተዳደር ተቋም በዕለት ተዕለት ተግባሩ በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ሚሰጠው የአስተዳደር ውሳኔ ነው፡፡ የአስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚወስን ሰው የሚከተሉትን መርሆች መከተል ይኖርበታል፡፡ እነሱም ውሳኔ ለመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው መሆን፣ ውሳኔ ሲሰጥ በሕግ የተሰጠ ሥልጣን ወሰንን አለማለፍ፣ የግል እና የሕዝብ ጥቅምን ማመዛዘን፣ ሙያዊ ትጋትና ሥነ ምግባርን በመከተል ውሳኔ መስጠት፣ በአግባቡ ማዳመጥ፣ በቅን ልቦና መወሰን፣ ለውሳኔው በቂ ምክንያት መስጠት፣ ከተገልጋዩ ጋር የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው ከሆነ ወይም በማናቸውም ሁኔታ የጥቅም ግጭት ካለ እራስን ከዉሳኔ ማግለል፣ የተገልጋዮችን እኩልነት ማክበር፣ በተገቢው ጊዜ መወሰን፣ ተገማች መሆን ወይም በፍሬ ነገር ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፍ እና በውሳኔ አሰጣጡ ግልፅነትን የተከተለ ሂደት መከተል ናቸው፡፡

ለአስተዳደራዊ ውሳኔ የሚቀርብ ጥያቄ ጉዳዩ በሚመለከተው ሰው ወይም በወኪሉ እንዲሁም በሚመለከተው የአስተዳደር ተቋም አነሳሽነት ሊጀመር ይችላል (አንቀጽ 20)፡፡ የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄ በፅሑፍ ሆኖ እንደሁኔታው በአካል፣ በተመዘገበ ፖስታ ወይም በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ሊቀርብ ይችላል፡፡ አቤቱታ በፅሑፍ ሲቀርብ ቀን፣ የአቤቱታ አቅራቢው ወይም ወኪሉ ስም፣ ፊርማ እና አድራሻ፣ የሚፈፅመው ተቋም ስም፣ የአቤቱታ አቅራቢው መብት ወይም ጥቅም፣ ተቋሙ ሊፈፅመው የሚገባ አስተዳደራዊ ተግባር እና የሚቀርቡ ምክንያቶች ማካተት ያለበት ሲሆን ተያያዥ ማስረጃዎች ተያይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

አቤቱታ የቀረበለት ተቋም አቤቱታውን የተቀበለ መሆኑን መዝግቦ የማረጋገጫ ፅሑፍ መስጠት አለበት፡፡ ውሳኔውን የሚሰጠዉ ሰው ሙያዊ ትጋትና ሥነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ የፍሬ ነገሩን እና ማስረጃ በሚገባ ማዳመጥ፣ መመርመር፣ የሕዝብን አስተያየት ማዳመጥ እንዲሁም የጥቅም ግጭትን ካለ ራስን ማግለል ይኖርበታል፡፡ የሚሰጠው ዉሳኔ የተገልጋይን የግል ጥቅም እና በአስተዳደር ተቋሙ ዓላማ የተመለከተውን የሕዝብ ጥቅም ማመዛዘን አለበት /አንቀጽ 25/፡፡

የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጥበት ሥነ ሥርዓት

በአዋጁ አንቀጽ 36 እና 37 መሠረት ማንኛውም አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ጉዳዩ በሚገባ መሰማት ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ በሚሰማበት ጊዜ ባለጉዳዩ በክርክሮች ሂደት ሁሉ ተገኝቶ ምስክርነት የመስጠት፣ ምስክሮችን እና ሌሎች ማስረጃዎችን የማቅረብ፣ የማሰማት እንዲሁም ተቃራኒ ወገን የሚያቀርበውን ማስረጃ መመርመርና የማስተባበል መብት አለው፡፡ የአስተዳደር ተቋሙ ማስረጃ ለማግኝት ከፈለገ በክርክሩ ተካፋይ ከሆነ ወገን ወይም ሌሎች ማናቸውንም አስፈላጊ ማስረጃዎችን ለማግኘት ሕጋዊ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላል፡፡

ውሳኔ

በአስተዳደሩ የተሰጠው ውሳኔ ከነምክንያቱ ለተገልጋዩ በፅሑፍ መሠጠት አለበት፡፡ ውሳኔውም በፅሑፍ ሆኖ የውሳኔ ቀንና ቁጥር፣ የተቋሙን ስም፣ በክርክሩ ተካፋይ የሆኑ ወገኖችን አድራሻ፣ አከራካሪ ፍሬ ነገር፣ የማስረጃዎች ትንተና፣ የፍሬ ነገር እና የሕግ ትንታኔ እና በጉዳዩ ላይ ተሰጠውን ውሳኔ መያዝ ይኖርበታል፡፡ በጉዳይ ለተሰጣቸው ውሳኔ ቅሬታ ካላቸው ለሚመለከታው አካል በሕግ የተቀመጠዉ ጊዜ ሣያልፍ በሌላ የፍትሕ መድረክ መብታቸውን ለማረጋጋጥ ይረዳል፡፡ በተሰጠዉ ዉሳኔ የማይመለስ ጉዳት የሚደርስ ሆኖ ከተገኘ ወሳኔው እንዲታገድለት ውሳኔውን ለሰጠው ተቋም አቤቱታ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ አቤቱታው ተቀባይነት ካገኘ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ወይም የውሳኔውን ማናቸውም ክፍል ሊያግደው ይችላል (አንቀጽ 41)፡፡

ቅሬታ የሚፈታበት ሥነ ሥርዓት

ማንም ሰው በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ የማቅረብ ህገ መንግሰታዊ መብት አለው፡፡ ቅሬታ የሚቀርበው በተቋሙ ለተቋቋመው የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ይሆናል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 45 መሠረት ቅሬታ የቀረበበት ውሳኔ ተመርምሮ እስኪወሰን ድረስ ዉሳኔው አይፈጸምም፡፡ ሆኖም የውሳኔው ሳይፈፀም መቆየት በሕዝብ ላይ የማይመለስ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ የአስተዳደር ተቋሙ የበላይ ኃላፊ ዉሳኔው እንዲፈፀም ሊያዝ ይችላል፡፡ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል ቅሬታውን በሚገባ መመርመር እና የውሳኔ ሀሳብ ለአስተዳደር ተቋሙ የበላይ ኃላፊ ወይም እሱ ለወከለው የሥራ ኃላፊ ማቅረብ አለበት፡፡ የበላይ ኃላፊ ወይም እሱ የወከለው የሥራ ኃላፊ በቅሬታ ማስተናገጃ አካል የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል (አንቀጽ 46)፡፡ ይህ ውሳኔ ወዲያውኑ በፅሑፍ ለቅሬታ አቅራቢው መስጠት አለበት፡፡ በፅሑፍ የሚሰጥበት ዋና ዓላማ የክለሳ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ስሚያግዝ ነው፡፡

በፍርድ ቤት የሚሰጥ የክለሳ ውሳኔ

ከላይ በተመለከተው አስተዳደራዊ ውሳኔ መሠረት ቅሬታ ያደረበት ማንም ሰው ለፍርድ ቤት ለክለሳ ማቅረብ ይችላል፡፡ በአንቀጽ 49 መሠረት ጉዳዩን የሚመከለተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ቅሬታውም የአስተዳደር መመሪያውን በተመለከተ ወይም በተሰጠው ውሳኔን የተመለከተ ይሆናል፡፡ የአስተዳደር ውሳኔን በተመለከተ የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጠው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን መመሪያን የተመለከተ ቅሬታ ሲሆን ደግሞ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊቀርብበት ይችላል (አንቀጽ 49 (1 እና 2)፡፡

የአስተዳደር መመሪያ በፍርድ ቤት የሚከለሰው በሶስት ምክንያቶች ሲሆን ይህም

  1. በዚህ አዋጅ የተመለከቱትን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል የወጣ መሆኑ ሲረጋገጥ
  2. ከተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጣ ሲሆን፣
  3. ከመመሪያ በላይ ከሆኑ ሌሎች ህጎች የሚቃረን ሲሆን ሲገኝ ነው፡፡

በሌላ በኩል የአስተዳደር ውሳኔ የሚከለሰው በዚህ ከላይ ተጠቀሱ አስተዳደራዊ ጥያቄዎችና ውሳኔዎቹ የሚመሩባቸውን መርሆዎች የጣሰ ሲሆን ነው (አንቀጽ 50 (1 እና 2)፡፡ ቅሬታው መመሪያው ከፀደቀበት ቀን በሚቆጠር በ90 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ የሚገባው ሲሆን ውሳኔውን የተመለከተ ከሆነ ዉሳኔ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡ ለውሳኔ ክለሳ አግባብነት ያላቸው የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑ ሲሆን ፍርድ ቤት ዉሳኔውን ወይም መመሪያዉን ሊያፀና ወይም በሙሉ ወይም በከፊል ሊሽር ይችላል (አንቀጽ 57)፡፡

ማጠቃለያ

የአስተዳደራዊ የሥነ ሥርዓት ሕግ ዜጎች ተገቢውን አስተዳደራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ቅሬታ ሲኖራቸውም እስከ ፍርድ ቤት ቀርበው መብታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበትን ሥርዐት የዘረጋ በመሆኑ ማህበረሰቡ ይህን በመረዳት መብትና ግዴታውን በማረጋገጥ ለህጉ ተፈፃሚነት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ