የሽያጭ ውል

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

የሰዉ ልጆች በዚች ምድር ላይ ሲኖሩ የተለያዩ ህጋዊ ውጤት ያላቸውን ተግባራት ያከናዉናሉ፡፡ ከእነዚህ ህጋዊ ዉጤት ከሚያስከትሉ ተግባራት አንዱ የሽያጭ ዉል ነዉ፡፡ የሽያጭ ዉል ሰዎች በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የሕይወት መስተጋብራቸው ዉስጥ ከሚያከናዉኗቸዉ ተግባራት አንዱ ሲሆን የጠቅላላው የውል ግዴታ አንዱ ዘርፍ ነዉ፡፡

በዚህ አጭር ጽሑፍ የሽያጭ ዉልን ምንነትና አፈፃፀም፣ የሻጭና የገዥ ግዴታዎች እንዲሁም የውል አለመፈፀም የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤቶች እንመለከታለን፡፡

የሽያጭ ውል ምንነት

በፍትሐብሔር ህጋችን ቁጥር 2266 መሠረት ሽያጭ ማለት ሻጭ የሆነው አንዱ ወገን ገዥ ለሆነው ሌላ ወገን ዋጋው በገንዘብ የተወሰነውን አንድ ነገር ገዢው ሊከፍለው ግዴታ በገባበት መሠረት ሊያስረክብና ሀብትነቱን ሊያስተላልፍ የሚገደድበት ውል ነው፡፡ በህጉ ድንጋጌ መሠረት ሽያጭን ለማከናወን መሟላት ያለባቸው ፍሬ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡-

ውል መሆኑ፡- ሽያጭ በሻጭና በገዢው መካከል የሚደረግ ውል እንደመሆኑ መጠን የውልን መሰረተ ሀሳቦችና መመዘኛዎች ተከትሎ መፈፀም የሚገባው መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ ይህም ማለት ውልን ለመመስረት አስፈላጊ የሆኑትን እንደ የተዋዋዮች ነፃ ፈቃድ፣ የተዋዋዮች ችሎታ መኖር፣ የውሉ ፍሬ ነገር በእርግጠኝነት የሚቻል፣ ህጋዊና ሞራላዊ መሆን እና የውሉ ፎርም ወይም ቅርፅን በሚመለከት የውልን አካሄድ ተከትሎ መከናወን አለበት፡፡

በሁለት አካላት መካከል ስለመከናወኑ፡- የሽያጭ ውል የሚከናወነው በሁለት ወገኖች ማለትም በሻጭ ወገን እና በገዢ ወገን መካከል ነው፡፡

ንብረቱን የማስረከብና ስመሀብቱን የማስተላለፍ ግዴታ፡- የንብረቱ ባለቤት ንብረቱን ለማስረከብ ብቻ ሳይሆን ስመሀብቱንም ለማስተላለፍ ከገዥው ጋር መስማማት ይጠበቅበታል፡፡ ይህም የሽያጭ ውል ከሌሎች ውሎች የሚለይበት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በንብረት ላይ የሚደርግ መሆኑ፡- በትርጉሙ ክፍል የሽያጭ ውል በንብረት ላይ የሚደረግ መሆኑን እንደመስፈርትነት አካቶት እናገኘዋለን፡፡ ይህም ማለት የሽያጭ ውል ፍሬ ነገር ንብረት መሆን አለበት ለማለት ነው፡፡

ዋጋው በገንዘብ የተወሰነ መሆኑ፡- አንድ ውል የሽያጭ ውል ለመባል የሸያጩ ፍሬ ነገር የሆነው ንብረት ዋጋው በገንዘብ የተተመነ መሆን ይገባዋል፡፡ በገንዘብ ያልተተመነ ዋጋ ከሆነ የዕቃ ለውጥ ከመሆን አልፎ የሽያጭ ውል መስፈርትን ማሟላት አይችልምና ነው፡፡

እንደማንኛውም የውል ዓይነቶች የሽያጭ ውልም ተዋዋይ ወገኖች (ገዥና ሻጭ) በዕቃው ምንነትና ዋጋ ላይ ተነጋግረው ስምምነት ላይ ሲደርሱ የሽያጭ ውሉ ይመሰረታል፡፡ ይህም ማለት ገዥና ሻጭ በውሉ ፍሬ ነገሮች ላይ ስምምነታቸውን ሲገልፁ ውሉ እንደተፈፀመ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡

የሻጭ ግዴታዎች

ዕቃ የማስረከብ ግዴታ

የሽያጭ ውል ከተከናወነ በኋላ ሻጭ የግብይት ምክንያት የሆንውን ዕቃ/ንብረት ለገዥ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡ ዕቃውን ሲያስረክብም መጠኑንና ዓይነቱን በሚመለከት በውላቸው መሠረት መሆን ይገባዋል፡፡ ሻጩ በመጠን ያነሰ ንብረት ወይም የተለየ ዓይነት ዕቃ ካስረከበ ግዴታውን እንዳልፈፀመ ይቆጠራል፡፡ ዕቃውን የሚያስረክብበት ቦታና ጊዜም ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ስለዚህ ተዋዋይ ወገኖች ዕቃውን የሚረካከቡበትን ጊዜና ቦታ ከወሰኑ በውላቸው መሠረት መሆን የሚገባው ሲሆን ጊዜና ቦታውን ካልወሰኑ ደግሞ ጊዜውን በተመለከተ በመርህ ደረጃ የዕቃው ዋጋ ክፍያ ሲፈፀም ዕቃ የማስረከብ ግዴታውም ወዲያዉኑ መከናወን ያለበት መሆኑን በፍ/ብሔር ሕጉ በቁጥር 2278 ላይ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በሆነ ምክንያት ይህ ሳይደረግ ቢቀር ገዢው አስረክበኝ ብሎ ሲጠይቅ ሻጩ ወዲያውኑ ማስረከብ የሚገባው ሲሆን የማስረከቢያ ቦታውን በሚመለከት ግን ሽያጩ በተደረገበት ወቅት በነበረው መስሪያ ቤት ወይም መስሪያ ቤት ባይኖረው እንኳን ሻጩ አዘውትሮ በሚጠቀምበት ቤቱ መሆን እንደሚገባው የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2276 እና 2279 በቅደም ተከተል ይደነግጋሉ፡፡

ስመ-ሀብት የማስተላለፍ ግዴታ

የሽያጭ ውል ልዩ መገልጫ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ሻጩ የሽጭ ምክንያት የሆነውን ንብረት ስመ-ሀብትን የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ሲባል የባለቤትነትን መብት ያለተጨማሪ ሕጋዊ ሂደት ይዞታን በማስተላፍ ብቻ የሚያሰጡ ንብረቶች እንደ ተራ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የመሳሰሉት ንብረቶቹን በትክክለኛው ጊዜና ቦታ በማስረከብ፣ ልዩ ተንቀሳቃሽ የሆኑትን እንደ ተሽከርካሪ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ደግሞ ለገዥው ከማስረከብም በተጨማሪ የሚመለከተው አካል ጋር አስፈላጊ ሰነዶችን አሟልቶ በማቅረብ ስመ-ሀብትነቱን የማዛወር ሂደት የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡

ዋስትና የመስጠት ግዴታ

ሌላኛው የሻጭ ግዴታ ከተሸጠው ዕቃ ጋር በተገናኘ ለሚፈጠሩ ችግሮች ለገዥው ዋስትና የመስጠት ግዴታ ነው፡፡ ይህ የግዴታ ዓይነት የሚፈለገው ከዕቃው የባለቤትነት መብት ጋር ለሚፈጠሩ ችግሮች፣ ከዕቃው ጥራት እና ተስማሚነት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሻጩ ለገዢው ዋስትና የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑን በፍ/ብሔር ሕግ ቁጥር 2282፣ 2287 እና ተከታይ ድንጋጌዎች እና በየንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/06 አንቀጽ 14(5) ንባብ መረዳት እንችላለን፡፡

የገዥ ግዴታዎች

ገዥም በበኩሉ የራሱ የሆኑ ግዴታዎች አሉበት፡፡ በዋናነት የገዥ ግዴታዎች ተብለው የሚታወቁት የዕቃውን ዋጋ የመክፈልና የገዛውን ዕቃ በተገቢው ጊዜ የመውሰድ ግዴታዎች መሆናቸው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2303 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ የዕቃውን ዋጋ የመክፈል ግዴታ ሲባል የገዥው ገንዘብ የመክፈል አቅም ያለው መሆንና የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን ማዘጋጀቱን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን እንደየውሉ ዝርዝርና በአካባቢው ባህል በተለመደው መልኩ መክፍል ግዴታንም ያካትታል፡፡

ልክ እንደ የማስረከብያ ቦታና ጊዜ ክፍያ የሚፈፀምበት ቦታና ጊዜም ወሳኝ በመሆኑ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ክፍያው የሚፈፀምበት ቦታ በውላቸው ላይ የተገለፀ ከሆነ በዛው ቦታ መፈፀም የሚገባው ይሆናል፡፡ በውላቸው ላይ ከፍያ የሚፈፀመው ሻጭ ዕቃውን ለገዥው በሚያስረክብበት ወቅት ነው የሚል ሀሳብ ካለበት ደግሞ ክፍያው የሚፈፀምት ቦታ ዕቃው የሚረከብበት ቦታ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በውላቸው ውስጥ እነዚህ ዝርዝሮች ከሌሉበት ግን ክፍያው የሚፈፀምበት ቦታ በሻጩ ቤት እንደሆነ ሕጉ ይደነግጋል፡፡ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2309)

ክፍያ የሚፈፀምበትን ጊዜ በሚመለከት የእጅ በእጅ ሽያጭ በሚሆንበት ወቅት ገዥው ዋጋውን መክፈል ያለበት የገዛውን ዕቃ ሲረከብ ሲሆን ሽያጩ የዱቤ በሆነ ወቅት ደግሞ ዋጋው መከፈል ያለበት በውሉ ተገልፆ ከሆነ በውሉ መሠረት ካልተገለፀ ግን ሻጩ እንደጠየቀ ወዲያዉኑ መሆን ይገባዋል፡፡ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2311)

የውል አለመፈፀምና ውጤቶቹ

በተዋዋይ ወገኖች የውል አለመፈፀም በሚያጋጥም ጊዜ ሕጉ የውል ግዴታውን ባልተወጣው አካል ላይ ቅጣትና ኪሳራን የሚያስከትል ሲሆን የውል ግዴታውን ለፈፀመው ደግሞ ውሉ እንዲፈፀምለት ወይም ለጉዳቱ ተመጣጣኝ ካሳ የሚያገኝባቸው የተለያዩ መፍትሔዎችን /Remedies/ ያስቀምጣል፡፡

በመሆኑም እንደውሉ ያልተፈፀመለት ተዋዋይ ወገን የሚከተሉት ሦስት መፍትሔዎች ይኖሩታል፡፡ እነዚህም፡- ውልን በግድ ማስፈፀም፣ ውልን ማፍረስ እና የጉዳት ካሳ መጠየቅ ናቸው፡፡ እንደወሉ ያለተፈፀመለት ወገን ወደመፍትሔዎች ከመሄዱ በፊት ውሉን ያልፈፀመውን ሰው ሕጉ በሚፈቅደው አኳኋን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን በውላቸው ውስጥ ማስጠንቀቅያ መሰጣጣት አስፈላጊ አይደለም ተባብለው ከተስማሙ ማስታወቅያ መስጠት ሳያስፈልግ በቀጥታ ወደ መፍትሔዎቹ መግባት ይቻላል፡፡

ውልን አስገድዶ ማስፈፀም ማለት እንደውሉ ያልፈፀመውን ሰው ከፍላጎቱ ውጪ ማድረግ የሚገባውን እንዲያደርግ ማድረግ ነው፡፡ ሻጩ ዕቃውን የማስረከብ ግዴታውን ካልተወጣና ገዥው የውሉ መፈፀም ልዩ ጥቅም የሚያስገኝለት ከሆነ ገዥውን በሕግ አስገድዶ የማስፈፀም መብት እንዳለው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2329 ስር ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ገዥው ክፍያውን ሳይከፍል ቢቀርና በንግድ ልማድ መሠረት ሁለቱን ተዋዋዮች በሚያቻችል ሽያጭ ለመሆን የሚችል ካልሆነ በስተቀር ሻጩ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2333 መሠረት ገዥውን እንዲከፍለው በሕግ ማስገደድ ይችላል፡፡ ሌላው የውል አለመፈፀም መፍትሄ ውልን ማፍረስ ሲሆን በፍርድ ቤት ወይም በተዋዋይ ወገኖች በራሳቸው መደረግ ይችላል፡፡ ውልን በግድ ከማስፈፀምና ውልን ከማፍረስ በተጨማሪ ለደረሰ ጉዳት ካሳ ማስከፈልም ሌላኛው የውል አለመፈፀም መፍትሔ ነው፡፡ የጉዳት ካሳ የሚከፈለው በውል አለመፈፀም ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ወገን ውሉ ቢፈፀም ኖሮ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም እንዲያገኝ ለማስቻል በማሰብ ነው፡፡

በአጠቃላይ የሽያጭ ውል የጠቅላላ የውል ግዴታ አንድ አካል እንደመሆኑ በመሠረታዊው የውል ሕግ መርሆዎች የሚገዛ ስለሆነ ሰዎች ዕቃ ሲገዙም ሆነ ሲሸጡ ጠቅላላ የውል ሕግ መርሆዎችን እንዲሁም የሽያጭ ውልን የተመለከቱ ልዩ ድንጋጌዎችን ተከትለው ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ገዢና ሻጭ የገቡትን ግዴታ እንደውሉ መፈፀም ያለባቸው ሲሆን ግዴታው ሳይፈፀም ቢቀር ውል ያልተፈፀመለት ወገን በህጉ የተመለከቱ መፍትሄዎችን መጠቀም ይችላል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ