በፍትሐብሔር ክርክር የተከራካሪዎች በችሎት አለመቅረብ የሚያስከትለው ውጤት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

ሰዎች በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው በርካታ ተግባራትን ይከውናሉ፡፡ በዚህ መሀልም በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን አለመግባባቶች በራሳቸው መፍታት ሳይችሉ ሲቀር በተለያዩ መንገዶች ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስወገድ የመዳኘት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ጉዳዩ ይወሰዳል፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት የጉዳዩ መሰማት ከመጀመሩ በፊት በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርአት ህጉ ላይ በተቀመጠው መሠረት ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ በችሎት ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲያሰሙ በቅድሚያ ጥሪ የሚያደርግ ሲሆን ግራ ቀኙ ካልቀረቡ ጉዳዩ እንደተቀጠረበት ሁኔታ በህጉ ላይ የተቀመጡ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም በአንድ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ክርክር የጀመሩ ወገኖች በቀነ ቀጠሮ ያልቀረቡ እንደሆነ ፍርድ ቤት የሚወስደው እርምጃ ምን እንደሆነ እና ምን አይነት ውጤት እንደሚያስከትል እንመለከታለን፡፡

ከሳሽ ስለመሆን

በመርህ ደረጃ ማንኛውም ችሎታ ያለው ሰው ክስ የማቅረብ መብት ያለው ሲሆን ነገር ግን ለክሱ መነሻ የሆነው ነገር ወይም ክሱ በተመሰረተበት ጉዳይ ላይ ጥቅም ወይም መብት ያለው መሆኑን ከሳሹ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሳሽ ከተከሳሽ ላይ የሚጠይቀውን መብትና ጥቅም ማረጋገጥ ያለበት ሲሆን የሚቀርበው ጉዳይ በፍርድ ሊታይ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ በሕግ ችሎታ የሌላቸው ሰዎች እና የሕግ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ክስ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን ከላይ እንደተቀመጠው መብትና ጥቅማቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው በፍትሐብሔር ሥነ-ሥረአት ሕግ ቁጥር 33 በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ችሎታ ያለው የተፈጥሮ ሰውም ይሁን በሕግ ሰውነቱ የተረጋገጠለት ድርጅት መብትና ጥቅም አለኝ በሚለው ማንኛውም ጉዳይ ላይ ከሳሽ የመሆን መብት አለው፡፡

የከሳሽ አለመቅረብ

ከሳሽ በአንድ ጉዳይ ክስ ካቀረበ በኋላ ክርክሩ እንዲሰማ በተቀጠረበት ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነና ተከሳሽ ቀርቦ የተከሰሰበትን ጉዳይ በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ እንደሆነ ከሳሽ በሌለበትም ቢሆን ፍርድ ቤቱ በታመነው ጉዳይ ላይ የፍርድ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችል ሲሆን ተከሳሹ በቀረበው ክስ ላይ የካደ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን በመዝጋት ተከሳሽን እንደሚያሰናብት በፍ/ሥ/ሥ/ህቁ 73 በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የመዝገቡ መዘጋት የሚያስከትለው ውጤት

በአንድ ጉዳይ ላይ ክስ ቀርቦ ክርክሩ በሚሰማበት ቀን ከሳሽ ሳይቀርብ ቀርቶ መዝገቡ ከተዘጋ ከሳሽ ለመጀመሪያው ክስ መነሻ የነበረውን ነገር መሠረት በማድረግ በድጋሚ ክስ ማቅረብ እንደማይችል በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 74(1) ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከሳሹ በቀዳሚው ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረው በቂ በሆነ ምክንያት ወይም እክል ከሆነ መዝገቡ በተዘጋ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከሳሽ መዝገቡ እንደገና ተከፍቶ ጉዳዩ እንዲታይለት መጠየቅ የሚችል ሲሆን ፍርድ ቤቱ ምክንያቱ በቂ መሆኑን ከተቀበለ ከሳሽ ኪሳራና ማንኛውም ወጪ እንዲከፍል ውሳኔ በመስጠት የተዘጋው መዝገብ እንዲከፍት ትእዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 74(2) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የተከሳሽ በችሎት አለመቅረብ

አንድ ተከሳሽ ክስ በቀረበበት ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለቀረበበት ክስ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ለመስማት በቀጠረው ቀነ ቀጠሮ ከሳሽ ቀርቦ ተከሳሽ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 70 መሠረት ተከታዮችን ሥርአቶች በመከተል ውሳኔ ይሰጣል፡፡ እነዚህ ሥርአቶችም፡-

  • በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርእት ሕግ ላይ በተቀመጠው የመጥርያ አደራረስ ሥርአት መሠረት ለተከሳሽ መጥርያ የደረሰው መሆኑ ከተረጋገጠ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በሌለበት ክርክሩ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡
  • የተላከው መጥሪያ ለተከሳሽ በትክክል ያልደረሰው ከሆነ ሁለተኛ መጥሪያ እንዲላክለት ይደረጋል፡፡
  • ለተከሳሽ መጥሪያ የደረሰው መሆኑ ቢረጋገጥም መጥሪያው ለተከሳሹ የተሰጠበት ቀን ለክሱ መልስ ለማዘጋጀት አጭር ጊዜ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከተረዳ ሌላ ቀጠሮ ይሰጣል፡፡
  • ተከሳሾች ብዙ ሆነው መጥሪያው ለተወሰኑ ተከሳሾች ያልደረሳቸው በከሳሹ ቸልተኝነት ከሆነ ፍርድ ቤቱ መጥሪው ባልደረሳቸው ተከሳሾች ላይ የቀረበውን የክስ መዝገብ ሊዘጋው ይችላል፡፡

የተከሳሽ አለመቅረብ ያለው ውጤት

በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርእት ሕግ ላይ በተቀመጠው የመጥርያ አደራረስ ሥርአት በችሎት እንዲቀርብ መጥሪያ ደርሶት ተከሳሽ ሳይቀርብ ከቀረ ክርክሩ በሌለበት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ተከሳሽን ከክሱ አስወጥቶ /Ex-parte/ ጉዳዩ መታየት የሚቀጥለው ተከሳሹ ጉዳዩ ለመሰማት በተቀጠረበት ቀን ወይም የቃል ክርክር ለማድረግ በተቀጠረበት ቀን ያልቀረበ እንደሆነ ነው፡፡ ሆኖም ተከሳሽ ያልቀረበው መልስ ይዞ ለመቅረብ በተቀጠረበት ቀን ከሆነ መልሱን በጽሑፍ ከማቅረብ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥቅሞች ይቀሩበታል እንጂ በቀጣዩ ሂደት ከመሳተፍ እንደማያግደው የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 15835 አስገዳጅ የሆነ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡

በሌላ በኩል በከሳሹ ቸልተኝነት መጥሪያ ለተከሳሽ ባለመድረሱ ተከሳሽ ያልቀረበ ከሆነ መዝገቡ የሚዘጋ ይሆናል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከሳሽ ተገቢውን የዳኝነትና የተወሰነውን ኪሳራ ከፍሎ መዝገቡን እንደገና ማስከፈትና ነገሩ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚችል ከፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 71(1) መረዳት ይቻላል፡፡

ሆኖም ጉዳዩ የቀረበው በይግባኝ ከሆነ ይግባኝ ባይ መጥሪያውን ለመልስ ሰጪ በአግባቡ ባለማድረሱ መዝገብ ከተዘጋ ለይግባኝ ክርክር መነሻ የነበረውን ነገር መሠረት በማድረግ በድጋሚ ክስ ማቅረብ እንደማይችል በበፍ/ሥ/ስ/ህ.ቁ 74(1) ተደንግጓል፡፡

ተከሳሽ በሌለበት የተሰጠ ውሳኔ የሚነሳበት ሁኔታ

ተከሳሽ በተገቢ ሁኔታ መጥሪያ ደርሶት በችሎት ሳይቀርብ ቀርቶ በሌለበት ክርክሩ እንዲቀጥል ከተወሰነ በኋላ በቀጣይ ቀጠሮ በችሎት ቀርቦ ባለፈው ቀጠሮ መቅረብ ያልቻለው በቂ በሆነ ምክንያት እንደሆነ ካስረዳና ፍርድ ቤቱም የቀረበው ምክንያት በቂ መሆኑን ከተረዳ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 72 መሠረት ተከሳሹ በቀረበበት ቀን መከላከያውን አቅርቦ ወደ ክርክሩ እንዲገባ ያደርጋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ተከሳሽ በሌለበት የተሰጠን ውሳኔ ለማስነሳት የሚቻለው በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 78 መሠረት ነው፡፡ አንድ ተከሳሽ ክርክሩ ላይ ቀርቦ መልስ ወይም መከላከያ ሳያቀርብ ቀርቶ በሌለበት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደሆነ ይህ ውሳኔ መሰጠቱን ባወቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በችሎት ቀርቦ የተሰጠው ውሳኔ እንዲነሳለት የማመልከት መብት እንዳለው የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 78 ደንግጓል፡፡ ተከሳሽ መጥሪያው በትክክል ያልደረሰው መሆኑን ወይም ክርክሩን ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ቀርቦ ክርክሩን ለማሰማት ወይም መልስ ለመስጠት ያልቻለው በበቂ ምክንያት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ እንደሆነ ተከሳሹ በሌለበት እንዲታይ የተሰጠው ብይን እንደሚነሳና ክርክሩ እንደገና እንደሚሰማ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የከሳሽና ተከሳሽ (ሁለቱም) አለመቅረብ

ከሳሽም ተከሳሽም በቀነ ቀጠሮ ሳይቀርቡ የሚቀሩበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 69(2) መሠረት መዝገቡን የሚዘጋ ይሆናል፡፡

ግራ ቀኙ ባለመቅረባቸው ተዘጋው የመጀመሪያ ክስ ከሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 71(1) መሠረት ከሳሽ ተገቢውን የዳኝነትና የተወሰነውን ኪሳራ በመክፈል ጉዳዩን ማንቀሳቀስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከሳሹ በቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረው በቂ በሆነ ምክንያት ከሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 71(2) መሠረት የዳኝነትና ኪሳራ ሳይከፍል መዝገቡ እንደገና ተከፍቶ መታየት እንዲቀጥል ሊፈቀድለት ይችላል፡፡

ሆኖም በግራ ቀኙ አለመቅረብ የተዘጋው በይግባኝ ቀረበ ጉዳይ ከሆነ ከሳሹ ለይግባኝ ክርክር መነሻ የሆነውን ነገር መሠረት በማድረግ አዲሰ ክስ ማቅረብ እንደማይችል ከፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 74(1) መረዳት ይቻላል፡፡

በፍትሐብሔር ክርክር ሂደት ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ የፍርድ ቤት ቀነ ቀጠሮ በማክብ ጉዳያቸውን መከታተል የሚገባቸው ሲሆን ጉዳያቸውን በአግባቡ በማይከታተሉት ላይ ህጉ እርምጃ እንዲወሰድ የደነገገ በመሆኑ የፍርድ ቤት ቀጠሮ በማክበር እራስን ከእንግልት መጠበቅ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ