መግቢያ
ህጎች የተለያዩ መመዘኛዎችን መሠረት በማድረግ ሊከፋፈሉ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሠረት “የሲቪል ሎው (civil law)” እና “የኮመን ሎው (common law)”፣ “ፐብሊክ ሎው (public law)” እና “የግል ሕግ (private law)”፣ “የወንጀል ሕግ” እና “የፍትሐብሔር ሕግ”፣ “የሥነ ሥርዓት ሕግ (procedural law)” እና “መሠረታዊ ሕግ (substantive law) እና የመሳሰሉትን መስፈርቶች በመጠቀም ህጎችን ማከፋፈል ይቻላል፡፡ የሀገራት ህጎች በሁለት ዋና ዋና የሕግ ስርዓቶች ማለትም የኮመን ሎው እና የሲቪል ሎው በሚል ይታወቃሉ፡፡ የሲቨል ሎው የሕግ ስርዓት ተከታይ አገራት ፍትሐብሔርን የሚመለከት ዐብይ ሕግ በአንድ ጥራዝ (codified) ታውጀው እና የወንጀል የሚመለከት ዐብይ ሕግ በአንድ ጥራዝ (code) ታውጀው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በአገራችን አጠራር የፍትሐብሔር ሕግ እና የወንጀል ሕግ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ስለሆነም ይህን ስርዓት የሚከተሉ ሀገሮች ዋና የሕግ ምንጭ በሕግ አውጪ አካል ታውጀው የሚጠረዙ ህጎች ናቸው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የኮመን ሎው ስርዓትን የሚከተሉ ሀገሮች ዋና የሕግ ምንጫቸው በሕግ አውጪ አካል የሚወጡ ህጎች ሳይሆኑ በፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ ቀደም ብለው የተሰጡ አስገዳጅ ውሳኔዎች (precedent) ናቸው፡፡ እንዲሁም ያልተፃፉ ህጎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡
በሀገራችንም የተለያዩ የሕግ ምንጮች ያሉ ሲሆን የህጎች ተዋረድ ወይም የሕግ የበላይነት ደረጃ (hierarchy of laws) በሕግ ስርዓት ውስጥ ጉልህ ቦታ ካላቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በዚህ የንቃተ ህገ ጽሑፍ የኢትዮጵያ የሕግ ምንጮችን እና የህጎቹን ተዋረድ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሕግ ምንጮች (sources of Ethiopian laws)
በአገራችን ህጎች በፌደራል እና በክልል ደረጃ ወጥተው ስራ ላይ ይውላሉ፡፡ እነዚህም ህጎች በፌደራል እና በክልሎች የተለያዩ ምንጮች አሏቸው፡፡
የፌደራል የሕግ ምንጮች
ህገ መንግሥት (constitution)
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 9 ህገ መንግሥት የሀገሪቱ የበላይ ሕግ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ማንኛውም ሕግ ለምሳሌ አዋጅ፣ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ይህ ማለት ህገ መንግሥት የማንኛውም ህጎች መነሻ እና ምንጭ እንዲሁም ህጋዊነታቸውን (validation) የሚያገኙበት መሠረት ነው፡፡
ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች (international treaties)
ሀገራት ዓለም ዓቀፍ ስምምነት ሲፈርሙ ስምምነቱን እንደ አንድ ዓለም ዓቀፍ ሕግ እንተቀበሉ ማስረጃ ነው፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 (4) እንደሚደነግገው ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ስራ ላይ ለመዋል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቅ እና በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትመው መውጣት አለባቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ሆነው ተግባራዊ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ኮዶች (codes)
በሀገራችን በ1960ዎቹ አምስት ኮዶች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ እነዚህም የፍትሐብሔር ሕግ፣ የንግድ ሕግ፣ የባህር ሕግ በ1960፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ በ1961 እና የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ በ1965 ናቸው፡፡ እነዚህም ህጎች በነጋሪት ጋዜጣ በአዋጅ መልክ ታውጀው ስራ ላይ ውለዋል፡፡ ከዚህም በኃላ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ፣ የወንጀል ሕግ እና አዲሱ የንግድ ሕግ በኮድ መልክ ስራ ላይ የዋሉ የአገራችን የሕግ ምንጮች ናቸው፡፡
አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያ (proclamations, regulations & directives)
አዋጆች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ደንቦች በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና መመሪያዎች ደግሞ በፌደራል ሚኒስትሮች መስሪያ ቤቶች ወይም በሚስትሮች ምክር ቤት መመሪያ እንዲያወጡ በደንብ ውክልና በተሰጣቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ይወጣሉ፡፡ በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ሥልጣን በህገ መንግስቱ ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህም የሕግ ክፍሎች ወይም አይነቶች የአገራችን የሕግ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉ ሲሆኑ በስራ ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በሚነስትሮች ምክር ቤት ከታወጁበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ የሚውሉ ወይም በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡
አስገዳጅ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች (precedent)
ይህ የሕግ ምንጭ አይነት ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አስገዳጅ ወይም ሕግ የሚሆንበት ስርዓት ነው፡፡ በአገራችን ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ እንደ ሕግ እንደሚያገለግሉ እና አስገዳጅ እንደሆነ የሚገልፀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10/2 ስር እንደተደነገገው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ ባለ የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት ይኖረዋል ይላል፡፡ ይህ ማለት እነዚህ ውሳኔዎች የሕግ ምንጭ ሆነው ስራ ላይ ይውላሉ ማለት ነው፡፡
ልማዳዊ ህጎች (customary laws)
ልማዳዊ ህጎች በኢትዮጵያ ህጎች ውስጥ በተለያየ ጊዜ እንደምንጭ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ የፍትሐብሔር ህጉን ያረቀቁት ፕሮፌሰር ሬኒ ዳቪድ በረቂቁ ውስጥ የኦርቶዶክስን ልማዳዊ ሕግ ‘ፍትሀ ነገስትን‘ እንደምንጭ እንደተጠቀሙበት ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 34/5 ስር እንደተደነገገው የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሀይማኖቶች ወይም በባሕሎች ሕጎች መሠረት መዳኘት እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ባህላዊ ወይም ልማዳዊ ህጎች እንደ አንድ የሕግ ምንጭ ያገለግላሉ ማለት ነው፡፡
የክልል ሕግ ምንጮች
የክልል ህገ መንግሥት(state constitutions)
በኢፌድሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 52/2 ስር እንደተደነገገው ክልሎች የራሳቸው ህጎች ማውጣት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ክልሎች የራሳቸው ህገ መንግሥት ከፌደራል ህገ መንግሥት ጋር በሚጣጣም መልኩ አውጥተዋል እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡ የክልል ህገ መንግሥት በክልሎቹ ውስጥ የበላይ ሕግ ነው፡፡
የክልል አዋጆች (state proclamations)
የፌደራል ህገ መንግሥት ክልሎች ለአስተዳደር በሚያመች መልኩ የክልሎቹን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት አዋጅ ማወጅ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሠረት ለምሳሌ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና የደ/ብ/ብ/ህ ክልል የራሳቸው የቤተሰብ ሕግ አውጀዋል፡፡
የክልል ደንቦች እና መመሪያዎች (state regulations & directives)
የፌደራል ህገ መንግሥት የክልል አስፈፃሚ ምክር ቤቶች በክልል ወሰን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንደሚችሉ እንዲሁም ደንብ እና መመሪያዎችን ማውጣት እንደሚችሉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡
የህጎች ተዋረድ (hierarchy of laws)
የህጎች ተዋረድ (hierarchy of laws) የህጎች የበላይነት ደረጃን ወይም የትኛው ሕግ ከየትኛው ሕግ የበላይ ሕግ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በአገራችን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9/1 ስር እንደተደነገገው ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ ድርጊት እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት በሀገሪቱ ውስጥ የህጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ህገ መንግስቱ ነው ማለት ነው፡፡
የፌደራል ህገ መንግሥት በፌደራልም ይሁን በክልል ደረጃ የህጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው፡፡ በመቀጠል የአገሪቱ የበላይ የሕግ አውጪ አካል ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ህጎች ማለትም አዋጆች ይከተላሉ፡፡ የዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን የሕግ ተዋረድ በተመለከተ ወጥ የሆነ መግባባት ባይኖርም በህገ መንግስቱ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የአገረቱ ሕግ አካል ይሆናሉ ስለሚል ከአዋጅ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ የሚል ሀሳብ አለ፡፡ በሕግ ተዋረድ በመቀጠል የሚመጡት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጡት ደንቦች እና በሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የሚወጡት መመሪያዎች በቅደም ተከተል ናቸው፡፡በሌላ በኩል በተመሳሳይ ተዋረድ (hierarchy) ላይ ባሉ ህጎች መካከል መቃረን ሲኖር ተፈፃሚ የሚሆነው በጊዜ ዘግይቶ የወጣው ሕግ (latest prevails) ነው፡፡ ይህ ማለት ዘግይቶ የወጣው ቀድሞ ከወጣው ይልቅ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ልዩ ሕግ (special law) ከጠቅላላ ሕግ ይልቅ ቅድሚያ ተቀባይነት (special law prevails over general law) ይኖረዋል ማለት ነው፡፡