የሽያጭ ውል በኢትዮጵያ ሕግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ላይ ሲኖሩ የተለያዩ ህጋዊ ውጤት ያላቸውን ድርጊቶች ያከናውናሉ፡፡ ከነዚህም አንዱ ውል ሲሆን የሽያጭ የውል ደግሞ የውል አንዱ ዘርፍ ነው፡፡ የሽያጭ ውል በሻጭና በገዢ መካከል የሚፈፀም ስምምነት ሲሆን ሻጭና ገዢ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ የሚያካትት ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የሽያጭ ውል ምንነት፣ የሽያጭ ውል አመሰራረት እንዲሁም የሻጭና የገዢን ግዴታዎች እንመለከታለን፡፡

የሽያጭ ውል ምንነት

የሽያጭ ውል የጠቅላላው የውል ግዴታ አንድ አካል እንደመሆኑ የሽያጭ ውል ምንነትን ከማየታችን በፊት ስለ ውል ምንነት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መሀል የሚደረግ ስምምነት እንደሆነ በፍትሐብሔር ሕግ በቁጥር 1675 ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሰረተ ሀሳቦች በሚለው መፅሀፋቸው ውስጥ “ውል አንድን ግዴታ ወይም ከዚሁ ግዴታ ጋር የተያያዙ ሌሎች በርከት ያሉ ግዴታዎችን የሚያቋቁም ተግባርን የሚያመለክት አነጋገር ነው” በማለት ተርጉመውታል፡፡ “በዚህ ግዴታ ባለገንዘብ የሆነው ወገን አንድ ነገር እንዲፈጸምለት የመጠየቅ መብት የሚኖረው ሲሆን ባለዕዳው ደግሞ አንድን ነገር የመፈጸም ግዴታ ይጠበቅበታል” በማለት አብራርተው ገልፀውታል፡፡

ወደ ሽያጭ ውል ስንመጣ “ሽያጭ” ማለት ሻጭ የሆነው አንዱ ወገን ገዢ ለሆነው ሌላው ወገን ዋጋው በገንዘብ የተወሰነ አንድ ነገር ገዢው ሊከፍለው ግዴታ በገባበት መሠረት ሊያስረክብና ባለሀብትነቱን ሊያስተላለፍ የሚገደድበት ውል እንደሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2266 ላይ ተመልክቷል፡፡

የፀና ውል እንዲኖር መሟላት ያለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች

በገዢና በሻጭ መካከል የሚደረገው ውል በሕግ ተቀባይነት እንዲኖረው ከዚህ የሚከተሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ማሟላት ይኖርበታል፡፡ እነዚህም የተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ችሎታ፣ የተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ እንከን በሌለበት አኳኋን የተገለጸ መሆኑ፣ ተዋዋዮች የሚዋዋሉበት ጉዳይ ወይም ፍሬ ነገር ፀንቶ ባለ ሕግ ያልተከለከለ፣ ለመልካም ሥነ-ምግባር ተቃራኒ ነው ተብሎ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያልተወሰደ፣ አፈፃፀሙ በተዋዋዮች አቅም ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና በእርግጠኛነትም የተገለፀ እንዲሁም ሕጉ ውሉ የሚደረግበትን ፎርም በደነገገ ጊዜ የውሉ አቀራረጽ በተጠየቀው ፎርም የተዘጋጀ መሆኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መስፈርቶች የአንዱ አለመሟላት በሻጭና በገዢ መካከል የተደረገውን ውል ውጤት አልባ ሊያደርገው የሚችል ስለሆነ ሻጭና ገዢ በጥንቃቄ ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የሽያጭ ውል አመሰራረት

እንደማንኛውም የውል ዓይነቶች የሽያጭ ውልም ተዋዋይ ወገኖች (ገዢና ሻጭ) በዕቃው ምንነትና ዋጋ ላይ ተነጋግረው ስምምነት ላይ ሲደርሱ የሽያጭ ውሉ ይመሰረታል፡፡ ይህም ማለት ገዢና ሻጭ በውሉ ፍሬ ነገሮች ላይ ስምምነታቸውን ሲገልፁ ውሉ እንደተፈፀመ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ አቀራረብና አቀባበል (Offer and Acceptance) የሚባሉት የውል ሕግ መሠረታዊ አነጋገሮች ከተሟሉም ሽያጩ መፈፀሙን ያሳያል፡፡ ይህን አገላለፅ ወደ ሽያጭ ውል ስናመጣው አቀራረብ (Offer) የሚባለው ሻጭ ንብረቱን ለመሸጥ (የዋጋና ሌሎች ዝርዝሮችን አካቶ) ወደ ገበያ ሲያወጣ ማለት ሲሆን አቀባበል (Acceptance) የሚባለው ደግሞ ገዢ ንብረቱን ለመግዛት ፍላጎት ማሳየቱ እና ለመግዛት መወሰኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ አቀራረብ የሚያደርገው የንብረቱ ሻጭ ብቻ ሳይሆን ገዢውም ዕቃውን ለመግዛት ፍላጎት ያለው መሆኑን ገልፆ ለባለንብረቱ ጥያቄ ቢያቀርብለት አቀራረብ (Offer) አደረገ ማለት ሲሆን ሻጩም ይኼን ተቀብሎ ለመሸጥ ሲስማማ አቀባበል (Acceptance) አደረገ ማለት እንችላለን፡፡

የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1681 መሠረት አንድ የሆነ ዓይነት ውል ውስጥ ለመግባት የሚፈልግ ሰው (ለምሳሌ፡- ለመግዛት ወይም ለመሸጥ) ለቀረበለት የውል ጥያቄ ፈቃዱን በቃል፣ በጽሑፍ ወይም በተለመዱ ጠቅላላ ምልክቶች ወይም ለውሉ መነሻ ከሆነው ምክንያት የተነሣ ግዴታ ለመግባት መፍቀዱን በማያጠራጥር አሠራር ለማስታወቅ የሚቻል ሲሆን ጥያቄ አቅራቢው ለውሉ አቀባበል የተለየ አሠራር ለመወሰን ይችላል፡፡

የሻጭ ግዴታዎች

ሻጭ የሚከተሉት ሶስት መሠረታዊ ግዴታዎች አሉበት፡-

  • ዕቃ የማስረከብ ግዴታ
  • በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2273(1)፣ 2274 እና በተከታዮቹ መሠረት ሻጭ በውሉና በተጨማሪው ውስጥ የተመለከተውን ነገር ለገዢው በውሉ ልክ መስጠት ወይም ማስረከብ አለበት፡፡
  • የእቃውን ባለሀብትነትን የማስተላለፍ ግዴታ
  • የሽያጭ ውል ዋና ዓላማ የሚሸጠውን ዕቃ ባለሀብትነት ከሻጭ ወደ ገዥ ለማዛወር በመሆኑ በፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 2273(2) እና 2281 መሠረት ሻጭ የሸጠውን እቃ ባለሀብትነትን ለገዢ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡
  • ዋስትና የመስጠት ግዴታ

የሻጩን መድህንነት አስመልክቶ ሻጭ ባለሀብትነቱን ለገዢው ለማስተላለፍ አስፈላጊ የሆኑትን ተግባሮች ለመፈፀም ግዴታ እንዳለበት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2281 እና 2282 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም ሻጩ የሸጠውን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ይለቀቅልኝ የሚል ጠያቂ ቢመጣ ሻጩ መመለስ አለበት፡፡ ሆኖም ገዢው በገዛው ነገር ላይ ይለቀቅልኝ ባይ መኖሩን በውሉ ጊዜ አውቆ እንደሆነ ግን ሻጩ መጪውን ለመመለስ ቃሉን ሰጥቶ ካልተገኘ በቀር መድህንነት እንደማይኖርበት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2283(1) ተደንጓል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ገዢ ዕቃው የኔ ነው ባይ ሊነሳበት እንደሚችል ተረድቶ የሚመጣውን እቀበላለሁ ወይም እኔው እራሴ የኔ ነው ባዩን ሞግቼ እመልሳለሁ ብሎ ወዶና ፈቅዶ ከገባበት ሻጩ የኔ ነው ባዩን የመመለስ ግዴታ እንደማኖርበት ነው፡፡ ነገር ግን ገዢው ይለቀቅልኝ ባይ ወይም የኔ ነው ባይ ሊነሳበት እንደሚችል እያወቀ ወዶ ቢገባበትም ሻጭ ይለቀቅልኝ ባይ መኖሩን አውቀህ ብትገባም ይለቀቅልኝ ባዩን ለመመለስ እኔው ራሴ መድህን ነኝ የሚል የውል ግዴታ ገብቶ ከሆነ ግን ሻጭ በመድህንነት ከመጠየቅ አይድንም፡፡ በተጨማሪም ገዢው ይለቀቅልኝ ባይ መኖሩን የሽያጩ ውል በሚደረግበት ጊዜ ቢያውቅም ይለቀቅልኝ ባይነቱ ሊፈጠር የቻለው ሻጩ በሰጠው የዋስትና መያዣ ምክንያት ከሆነ ሻጩ ይለቀቅልኝ ባይ መኖሩን አውቀህ ስለገዛህ መድህንነት የለብኝም ሊል እንደማይችል በህጉ ቁጥር 2283(2) ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የገዢ ግዴታዎች

ገዢም በበኩሉ የራሱ የሆኑ ግዴታዎች አሉበት፡፡ በዋናነት የገዥ ግዴታዎች ተብለው የሚታወቁት የዕቃውን ዋጋ የመክፈል፣ የገዛውን ነገር የመረከብ እና በውሉ የገባቸው ሌሎች ግዴታዎች እንደሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2303 እና ተከታዮቹ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

የዕቃውን ዋጋ የመክፈል ግዴታ ሲባል የገዥው ገንዘብ የመክፈል አቅም ያለው መሆንና የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን ማዘጋጀቱን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን እንደየውሉ ዝርዝርና የአካባቢው ባህል በተለመደው መልኩ መክፍል ግዴታንም ያካትታል፡፡ ክፍያ የሚፈፀምበት ቦታና ጊዜም ወሳኝ በመሆኑ ክፍያው በውላቸው ላይ የተገለፀ ከሆነ በዛው ቦታ መፈፀም የሚገባው ይሆናል፡፡ በውላቸው ላይ ከፍያ የሚፈፀመው ሻጭ ዕቃውን ለገዥው በሚያስረክብበት ወቅት ነው የሚል ሀሳብ ካለበት ደግሞ ክፍያው የሚፈፀምት ቦታ ዕቃው የሚረከብበት ቦታ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በውላቸው ውሰጥ እነዚህ ዝርዝሮች ከሌሉበት ግን ክፍያው የሚፈፀምበት ቦታ በሻጩ አድረሻ እንደሆነ በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2309 ተደንግጓል፡፡ ሽያጩ የዱቤ በሆነ ጊዜ ደግሞ ዋጋው መከፈል ያለበት በውሉ ተገልፆ ከሆነ በውሉ መሠረት ካልተገለፀ ግን ገዢው የገዛውን ነገር ከተረከበ በኋላ ሻጩ እንደጠየቀ ወዲያውኑ መሆን እንዳለበት በህጉ አንቀጽ 2311 ተደንግጓል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የሽያጭ ውል መሠረታዊ ሀሳቦች ከላይ የተገለፁት ሲሆኑ የሸያጭ ውል በእለት ተእለት ኑሯችን የምንተገብረው ህጋዊ ውጤት የሚያስከትል ድርጊት እንደመሆኑ በህጉ ዙሪያ ያለንን እውቀት በማዳበር እና ህጉ ተከትሎ በመንቀሳቀስ እራሳችንን ከአላስፈላጊ እንግልት መታደግ ይጠበቅብናል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ