በአሁኑ ወቅት የግንባታው ዘርፍ ለቡዙ ዜጎች የስራ እድልን በመፍጠር ለአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይሁንና አብዛኛው የሕንጻ ግንባታዎች በሕንጻ ህጉ መሠረት በግንባታ ወቅት ማደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ባለማድረጋቸው የተነሳ በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፈተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ጤንነትና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የሕንፃ ግንባታ ወይም የሕንፃ ግንባታ ማሻሻያና የአገልግሎት ለውጥን በተመለከተ በሀገሪቱ በአጠቃላይ ተፈፃሚ የሚሆን ዝቅተኛውን ደረጃ ለመወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አገራችንም የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 እና እሱን ለማስፈጸም የወጣ የሚንስትሮች ምክር ቤት የሕንጻ ደንብ 243/2003 ወጥቶ በስራ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ጽሁፍ በህጉ ላይ ስለተደነገገው እና በግንባታ ወቅት መደረግ ስለሚገባ ጥንቃቄ እና ይህንኑ ጥንቃቄ ያለማድረግ ስለሚያስከትለው ሀላፈነት በአጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የግንባታ ምንነት እና የሕንፃ አይነቶች በአገራችን ሕግ
የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 በአንቀጽ 2 ስር ለተለያዩ ቃላቶች ትርጓሜን የሚሰጥ ሲሆን ይህም፡-
“ግንባታ” ማለት አዲስ ሕንፃ መገንባት ወይም ነባር ሕንፃን ማሻሻል ወይም አገልግሎቱን መለወጥ ነው በማለት ትሩገጓሜ የሰተው ሲሆን፣
“ሕንፃ” ማለት ለመኖሪያ፣ ለቢሮ፣ ለፋብሪካ ወይም ለማናቸውም ሌላ አገልግሎት የሚውል ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ግንባታ ነው፤ በማለት ይገልጸዋል፡፡
የሕንፃ አይነቶች
የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ በአጠቃላይ በአገራችን የሚገኘውን የሕንጻ አይነቶችን በሶስት የሚመድብ ሲሆን ይህም፡-
1ኛ ምድብ ‘ሀ’ ሕንፃ
ማለት በሁለት የኮንክሪት ወይም የብረት ወይም ሌሎች ስትራክቸራል ውቅሮች መካከል ያለው ርቀት 7 ሜትር ወይም ከዚያ በታች የሆነ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ወይም ማናቸውም ከሁለት ፎቅ በታች የሆነ የግል መኖሪያ ቤት ነው፡፡
2ኛ ምድብ ‘ለ’ ሕንፃ
ማለት በሁለት የኮንክሪት ወይም የብረት ወይም ሌሎች ስትራክቸራል ውቅሮች መካከል ያለው ርቀት ከ7 ሜትር በላይ የሆነ ወይም ባለሁለት ፎቅና ከሁለት ፎቅ በላይ የሆነና በምድብ ‘ሐ’ የማይሸፈን ሕንፃ ወይም በምድብ ‘ሀ’ የተመደበ እንደሪል ስቴት ያለ የቤቶች ልማት ነው፡፡
3ኛ ምድብ ‘ሐ’ ሕንፃ
ማለት የሕዝብ መገልገያ ወይም ተቋም ነክ ሕንፃ፣ የፋብሪካ ወይም የወርክሾፕ ሕንፃ ወይም ከመሬት እስከ መጨረሻው ወለል ከፍታው ከ12 ሜትር በላይ የሆነ ማናቸውም ሕንፃ ነው፡፡
በግንባታ ወቅት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች
የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 እና ይህን ለማስፈጸም በወጣው የሚንስትሮች ምክር ቤት የሕንጻ ደንብ ቁጥር 243/2003 መሠረት በግንባታ ወቅት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች በመዘርዘር የሚያስቀምጡ ሲሆኑ ይህም፡-
- ማንኛውም ግንባታ በግንባታው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን፣ የግንባታው ሠራተኞችን፣ የሌሎች ግንባታዎችን ወይም ንብረቶችን ደኅንነት በማያሰጋ መንገድ ዲዛይን መደረግና መገንባት አለበት፡፡
- ማንኛውም የሕንፃ ባለቤት አዲስ የሕንፃ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው ቀደም ብሎ የተሠሩ ሕንፃዎችን እና የመሠረተ ልማት አውታሮችን አገልግሎት የሚያውኩ፣ የአካባቢውን ወይም አዋሳኙን ደኅንነትና ጤንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ እና የትራፊክ ፍሰትን የሚያስተጓጉሉ ሁኔታዎችን ማስወገድና ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡
- ከግንባታ ጋር የተያያዘ ቁፋሮ የማንኛውንም ንብረት ወይም አገልግሎት ደኅንነት ጉዳት ላይ የሚጥል ሲሆን የግንባታ ቦታው ባለቤት የንብረቱን ወይም የአገልግሎቱን ደኅንነት ለመጠበቅ በቂ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ለሚሠሩ ግንባታዎች የሕንፃው ባለቤት የሚከተላቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በጽሁፍ እንደአስፈላጊነቱም በዲዛይንና በዝርዝር ትንታኔ በማስደገፍ ለሕንፃ ሹሙ በማቅረብ ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡
- አጎራባቹ የቴክኒክ ዕውቀት ካለው በራሱ፣ ከሌለው ደግሞ በሚወክለው ባለሙያ ገንቢው የሚያደርገው የቅድሚያ ጥንቃቄ ዝግጅት ንብረቱን ከአደጋ መከላከል መቻሉ እንዲገለጽለት መጠየቅ እና በግንባታም ወቅት ከግንባታው ባለቤት ጋር በመነጋገር መከታተል ይችላል፡፡
- የተቆፈረው ጉድጓድ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ወይም በጉድጓዱ ውስጥ መሠረት በሚገነባበት ጊዜ ባለቤቱ ወይም ቁፋሮውን ያካሄደው ሰው ጉድጓዱን ለደኅንነት በማያሰጋ ሁኔታ መጠበቅ አለበት፡፡
- ከግንባታ ጋር የተያያዘ ቁፋሮ የማንኛውንም ንብረት ወይም አገልግሎት ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል መሆኑ ሲገመት የግንባታ ቦታው ባለቤት በቅድሚያ የመከላከያ ዘዴዎችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለከተማው አስተዳደር ወይም ለተሰየመው አካል በማቅረብ የጽሑፍ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡
- ማንኛውም አዲስ የሚገነባ ህንፃ መሠረት ጭነት በነባር መሠረቶች፣ የአገልግሎት መስመሮች ወይም ሌሎች ሥራዎች ላይ ችግር የሚፈጥር መሆን እንደሌለበት በህጉ ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በግንባታ ወቅት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችን አለማድረግ ሚያስከትልው ኃላፊነት
በግንባታ ወቅት መደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ባለማድርግ የሚደርስን ጉዳት በተመለከተ የፍትሐብሄር ተጠያቂነት እንዳለ ሆነ በሕንጻ አዋጅ እና ደንቡ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ የግንባታ ሥራ ፈቃድን በሚሰጡ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ይህንኑ እንዲያከናውኑ ኃላፊነት በተሰጣቸው ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች፣ በተመዘገቡ ባለሙያዎች ወይም ሥራ ተቋራጮች፣ አንዲሁም በግንባታ ባለቤቶች ለሚፈፀሙ ጥፋቶች እንደ ሁኔታው አስተዳደራዊ መቀጮ እና የወንጀል ተጠያቂነት እንዳለባቸው በህጉ ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
አስተዳደራዊ መቀጮ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕንጻ ደንብ ቁጥር 243/2003 ላይ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ኃላፊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አዋጁን ወይም ይህንን ደንብ በሚተላለፍ የግንባታ ባለቤት ላይ የከተማው አስተዳደር ወይም የተሰየመው አካል እንደ ሕንፃው ደረጃ የገንዘብ መቀጮን ይጥላል፡፡ ለአብነትም በግንባታ ወቅት መወሰድ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ሳይወስድ በምድብ ለ ሕንጻ ስር የሚመደብ ሕንጻ መገንባት በ3000 (ሶስት ሺ) ብር የገንዘብ መቀጮ ያሚያስቀጣ ሲሆን የሚሰራው ሕንጻ ምድብ ሐ ሕንጻ ሲሆን ቅጣቱ በ5000 (አምስት ሺ) ብር የገንዘብ መቀጮ ይሆናል በማለት ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ሌላው የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 አንቀጽ 56 መሠረት በአዋጁ ላይ በተመለከቱት የሕግ መጣስ ተግባሮች ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ የተመዘገበ ባለሙያ ወይም ሥራ ተቋራጭ በፍርድ ከተወሰነበት የእሥራት ቅጣት በተጨማሪ ጥፋተኛው ከአምስት ዓመት ጀምሮ ጥፋተኛ በተባለበት አንቀጽ እስከ ተመለከተው ከፍተኛ የእሥራት ዘመን ድረስ የሙያ ወይም የሥራ ፈቃዱ ይታገዳል በማለት አስቀምጧል፡፡
የወንጀል ተጠያቂነት
የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 መሠረት የአዋጁን ድንጋጌዎች በመተላለፍ የግንባታ ሥራ ፈቃድን በሚሰጡ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ይህንኑ እንዲያከናውኑ ኃላፊነት በተሰጣቸው ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች፣ በተመዘገቡ ባለሙያዎች ወይም ሥራ ተቋራጮች፣ እንዲሁም በግንባታ ባለቤቶች የሚፈፀሙ ጥፋቶች እንደሁኔታው ከ6 ወር ጀምሮ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ500 (አምስት መቶ) ብር እስከ 50000 (ሀምሳ ሺ) ብር የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም በ1996 የወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 501 የሕንጻ ስራ ደንቦችን መጣስ በሚል ርዕስ ስር ማንም ሰው ማንኛውንም አይነት የሕንጻ ስራ ወይም የሕንጻ ማፍረስ ስራ ሲቆጣጠር፣ ሲመራ ወይም ሲፈጽም በሕግ የተደነገገውን ወይም በሕንጻ ስራ ሙያ ወይም ልምድ የሚሰራባቸውን የጥንቃቄ ደንቦችን አስቦ በመጣስ የሕዝብን ደኅንነት ወይም የሰዎችን ሕይወት፣ ጤንነት ወይም አካል ወይም የሌላውን ሰው ንብረት አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ ከ3 ወር በማያንስ ቀላል እስራት እና በመቀጮ የሚቀጣ ሲሆን ወንጀሉ የተፈጸመው በቸልተኝነት እንደ ሆነ ከ1 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና በመቀጮ እንደሚያስቀጣ ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ማንኛውም የሕንፃ ግንባታ ሥራ በሚከናወንበት ወቅት ጉዳት እንዳያደርስ የግንባታ ሥፍራውን ተቀባይነት ባላቸው ቁሶች መከለል፣ በቁፋሮ ወቅት ከመሬት በታች ሊኖሩ የሚችሉ የመሠረተ ልማት መሥመሮች እንዳይጎዱ፣ በአካባቢው የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል፣ ተቀጣጣይነት ያላቸውን የግንባታ ቁሳቁሶች በአያያዝ ጉድለት ለእሳት አደጋ እንዳይጋለጡ በማድረግ፣ በግንባታ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ሠራተኞችና ጐብኚዎች የደኅንነት መጠበቂያዎችን በማሟላት፣ ለግንባታ የሚውሉ የኬሚካል ውጤቶች በአጠቃቀም ወቅት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እና ብናኝ ጭስና አንጸባራቂ ጨረር የመሳሰሉ አዋኪ ነገሮች አካባቢውን እንዳይረብሹ ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት በህጉ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይክቶሬት የተዘጋጀ