የዐቃቤያነ ሕግ የሞያ ሥነ-ምግባር (ክፍል ሁለት)

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ዐቃቤ ሕግነት የሕግ ባለሞያዎች ከሚሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ መንግሥትን ወክሎ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የሚከሰሱ ሰዎችን ለዳኝነት አካል አቅርቦ ለፍትሕ የሚተጋ የመንግሥት ጠበቃ ነው። ዐቃቤ ሕግ የሚለው ቃል “ዐቃቤ” እና” ሕግ” ከሚሉት ቃላት የተገነባ ነው፡፡ “ሕግ” ማለት የኅብረተሠብ ሰላምና ኑሮ ጸጥታ ለመጠብቅ ከአንድ መንግሥት የወጣ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን “ዐቃቤ” የሚለው የአማረኛ ቃል “ዐቃቢ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ነው። ዕውቁ የአማርኛና የግዕዝ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በ1948 “መፅሐፈ ሰዋሰው፣ወገስ ወመዝገበ ቃላት ሀዲስ” ባሳተሙት መፅሀፋቸው ዐቃቢ ማለት ጠባቂ፣ ተመልካች፣ ተከላካይ ማለት ነው። በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ማለት መንግሥት የሚያወጣውን ሕግ በሥርዓት የሚይዝ፤ የሚጠብቅ፤ የሚያስከብር ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ዐቃቤ ሕግ ሕግ ጠባቂና አስከባሪ የመንግሥት አካል ነው።

በዚህ ሂደት ወንጀል የተፈፀመባቸው የግል ተበዳዮች መንግሥት በሚያቆምላቸው የሕግ ባለሞያ በመወከል ለደረሰባቸው በደል ፍትሕ እንዲያገኙ ይደረጋል። ዐቃቤ ሕግ ሞያዊ ችሎታውን በመጠቀም ወንጀሎች ሲፈፀሙ ከፖሊስ ወይም የወንጀል ምርመራ ለማካሄድ ሥልጣን ከተሰጣቸው አካላት የሚቀርቡለትን የወንጀል ጉዳዮች በጥንቃቄ እየተመለከተ ክስ ሊመሠረት ይገባዋል ብሎ በሚያምንባቸው ጉዳዮች ላይ ክስ ለፍርድ ቤት ያቀርባል።

ክስ በማይመሠረትባቸው ጉዳች ላይ አስፈላጊ ሲሆን ምርመራ እንደ ገና እንዲጣራ ፤ ተጨማሪ ምርመራ አያስፈልጋቸውም ባላቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ ክስ የመዝጋት ውሳኔ ይሰጣል። ዐቃቤ ሕግ ወንጀል የፈፀመ ሰው ከሕግ ተጠያቂነት እንዳያመልጥ ለማድረግ ያለበትን ግዴታ ያህል አንድ ንፁህ ሰው ባልሠራው ሥራ እንዳይቀጣ የማድረግ የሕግና የሞራል ኃላፊነት አለበት። በመሆኑም የዐቃቤ ሕግ ግዴታ ሕግን ማስከበር እና ፍትሕን ማስፈን ይሆናል ማለት ነው።

በተጨማሪም የዐቃቤያነ ሕግ ተግባር እና ኃላፊነት አጠቃላይ የህጎችንና የደንቦችን አንድ ወጥ አፈፃፀም ማረጋገጥን፣ ከወንጀል ውጪም ቢሆን የመንግሥት አካላት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ መሆናቸውን መከታተልን፣ ከፍተኛ በሆኑ ሀገራዊ የፍትሐ ብሄር ክርክሮች መንግሥትን እየወከሉ መሳተፍ፣ የሕዝብ ጥቅምን በሚመለከቱ በሌሎች የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ጣልቃ መግባትን እንዲሁም በሕግ ጉዳዮች የመንግሥት አማካሪ ሆኖ መሥራትን ያካትታል።

ዐቃቤያነ ሕግ የተጣለባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት እና ግዴታ ሲወጡ በሕግ አግባብ ስራቸውን ከመሥራት በተጨማሪ የዐቃቤ ሕግ ሞያዊ ሥነ-ምግባርን ማክበር እና መልካም ሥነ- ምግባር በተሞላባት ሁኔታ ስራቸውን መከወን ይገባቸዋል። የወንጀል መዝገብን መርመሮ ውሳኔ የመስጠት ሂደት በሕግ እና በማስረጃ ላይ ብቻ መመስረት ያለበት ሲሆን ከዐቃቤ ሕግ የግል እምነት፣ ከመድሏዊ አሠራር ውጪ መሆን ይኖርበታል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን አንዱ የሥነ- ምግባር ጥሰት ይሆናል ማለት ነው።

በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግነት ከፍተኛ ኃላፊነት ከሚጠይቁ ሞያዎች አንዱ በመሆኑ ከሥነ-ምግባር አንፃር ሞያተኞች ሊከተሏቸው የሚገቡ የሥነ-ምግባር ግዴታዎች በተለያዩ ደንቦች እና መመሪያዎች ሰፍረው ይገኛሉ። በዚህ አጭር የንቃተ-ሕግ ጽሑፍ ክልሎች የራሳቸው የሥነ-ምግባር ደንብ ሊኖራቸው የሚችል መሆኑ እንዳለ ሆኖ የዐቃቤያነ ሕግ ሥነ-ምግባር ምን መሆን እንዳለበት በዋናነት የፌደራል ዐቃቤያነ ሕግ መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 443/2011ን፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤያነ ሕግ አለባበስ ሥርዓት እና ገጽታ መመሪያ ቁጥር 42/2017ን በመዳሰስ እናቀርባለን።

የዐቃቤያነ ሕግ የሞያ ሥነ-ምግባር በአጠቃላይ

የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጡራን ከሚለየአቸው ነገሮች አንዱ ህይወቱን ለመምራት በሚያደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሥነ-ሥርዓትን እና ደንብን መከተል ነው። እነዚህ ሥነ-ሥርዓት እና ደንቦች ደግሞ በአብዝሃኛው ሰው ቅቡልነት ካገኙ የግብረ-ገብነት ሥነ-ምግባር ደንቦች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ጠበቆች መፅሄት ላይ ዐቃቤ ሕግንነት፣ ሙያውና ሥነ-ምግባሩ በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እንዳሰፈሩት በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች እንደሚገልፁት በሕግ እና በሥነ-ምግባር ደንብ መከከል ያለው ልዩነት ሕግ ሰው ሁሉ ቢስማማበትም ባይስማማበትም ሊያከብረው የሚገባ ደንብ ሲሆን የሥነ-ምግባር ደንብ ግን እያንዳንዱ ሰው በጎ ነገር መሆኑን አምኖ በራሱ ፈቃድ ማክበር ያለበት የህይወት መመሪያ ነው በማለት ይገልፁታል። በመሆኑም መልካም ሥነ-ምግባር ሕግን ሙሉ ያደርገዋል ይላሉ።

የዐቃቤ ሕግነት ሥራ ሙያዊ ብቃትን፣ የአሠራር ነጻነትን፣ ሚዛናዊነትንና በተገልጋዩ ማኅበረሰብ ተዓማኒነትን ማግኘትን ይጨምራል። ዐቃቤ ሕግ በግል ሥነ-ምግባሩ ከሥራ ባልደረቦቹ፣ ከተገልጋዮች እንዲሁም ከተጠርጣሪዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን መልካም ሥነ-ምግባርን መላበስ፣ ባለጉዳዮችን ከማጉላላትና ፀያፍ ቃላትን ከመጠቀም መቆጠብ፣ በተገልጋዮች መካከል ተገቢ ያልሆነ ልዩነት ከመፍጠር መጠበቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግነት ከሚከተሉት የሥነ-ምግባር ነጥቦች አንፃር ከፍተኛ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት እንዳለበት ፕሮፌሰር ጥላሁን ያስቀምጣሉ። እነዚህም፡-

  • ክስ ለማቅረብ ስለሚደረግ ውሳኔ፡- ክስ ለማቅረብ የሚሰጥ ውሳኔ ሊመሠረት የሚገባው በህጉና በማስረጃው ብቻ እንጂ በዐቃቤ ህጉ የግል እምነት ወይም በሌሎች ከጉዳዩ ጋር የቀረበ ተዛምዶ በሌላቸው ፍሬ ነገሮች ላይ ሊሆን አይገባም።
  • ስጦታ ወይም መማለጃ ስለመቀበል፡- ዐቃቤ ሕግ ራሱ ጠይቆም ይሁን በሌላ መልክ ከስራው ጋር በተያያዘ ግንኙነት ካለው ከማንኛውም ወገን ስጦታ ወይም መማለጃ መቀበል የለበትም።
  • የጥቅም ግጭት፡- ዐቃቤ ሕግ የያዘው ጉዳይ ከግል ጥቅሙ ጋር እንደሚጋጭ ወይም ወደፊት ሊጋጭ እንደሚችል ካወቀ ይህንኑ ለበላይ ሀላፊ በማሳወቅ ከጉዳዩ እራሱን ማግለል ይኖርበታል።
  • በፍርድ ሂደት የሚታዩ የሥነ-ምግባር ጉድለቶች፡- ጉዳዩ በፍርድ ቤት በሚታይበት ጊዜ የችሎቱን ክብርና ሞገስ ሳያጓድል፣ የተከሳሹን፣ የምስክሮችንና የሌሎች በክርክሩ ሂደት የሚሳተፉ ሰዎችን ስሜት ሳይነካ ስራውን እንዲያከናውን የሚጠበቅበት ሲሆን ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ መረጃ ለፍርድ ቤት በመስጠት በተከሳሹ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ማድረግ የለበትም።
  • ተከሳሹን የሚመለከት ነገር አሟልቶ ስለመግለጽ፡-የዐቃቤ ሕግ ተቀዳሚ ዓላማ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ ስለሆነ መረጃው ለተከሳሹ ቢጠቀምም ባይጠቀምም፣ የክሱን ውጤት ቢቀይረውም ባይቀይረውም ተከሳሹን የሚመለከቱ ነገሮቸን አሟልቶ መግለፅ ይኖርበታል።
  • የሥራ ምስጢር ስለመጠበቅ፡-ለስራው አፈፃፀም እስፈላጊ መሆኑ እስካልታመነበት ድረስ ዐቃቤ ሕግ በያዘው ጉዳይ ላይ የሚያውቀውን መረጃ ምስጢርነት መጠበቅ አለበት። ይኸው የሚጠቀምባቸውን ሰነዶች በጥንቃቄ ማስቀመጥ፣ በሥራው ምክንያት የሚያውቃቸውን መረጃዎች ለራሱ ጥቅም ያለመዋል፣ በመሥሪያ ቤቱ ታምኖበት ፈቃድ ሳያገኝ የክስ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያለመስጠት ኃላፊነት አለበት።
  • በመስሪያ ቤቱ ንብረት በአግባቡ መገልገል።- ዐቃቤ ሕግ የተቋሙን ንብረት መገልገል ያለበት ኃላፊነት በተሞላበት ስሜት ከስራው ጋር ለተያያዙና ለተፈቀዱለት ዓላማዎች ማስፈፀሚያ ብቻ መሆን ይኖርበታል።
  • በሌላ ሥፍራ ተቀጥሮ መሥራት፡- ዐቃቤ ሕግ በሌላ ስራ ተቀጥሮ ለማስራት ለበላይ ሀላፊው ቀድሞ ማሳወቅ እና የትርፍ ስራ መሥራት በመስሪያ ቤቱ ደንብና ፖሊሲ ያለውን እንድምታ አብሮ ማየት አለበት።
  • የወደፊት የሥራ ሁኔታን ስለማመቻቸት፡- አንድ ዐቃቤ ሕግ ያለበትን ኃላፊነት መጠቀሚያ በማድረግ ወደፊት ሊገባበት ላሰበው የሥራ መስክ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አይገባውም። ሥራ ከለቀቀ በኋላም ቢሆን ዐቃቤ ሕግ በነበረበት ጊዜ ሥራውን አስመልክቶ በሚያውቀው መረጃ ያለአግባብ መጠቀም አይኖርበትም።
  • የማይገቡ ተግባሮችን ስለመግለፅ፡- የማይገባ ተግባር ወይም የሙስና ድርጊት በሌላ ዐቃቤ ሕግ ወይም በመስሪያ ቤቱ ሌሎች ሠራተኞች መፈፀሙን አንድ ዐቃቤ ሕግ ካወቀ ይህንኑ ተግባር በተቻለ ፍጥነት ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

የዐቃቤያነ ሕግ የሞያ ሥነ-ምግባር በፌደራል ዐቃቤያነ ሕግ መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 443/2011

ደንቡ በክፍል ሶስት ስለ ዐቃቤያነ ሕግ ነጻነት በሚደነግገው ክፍል ዐቃቤያነ ሕግ ከማናቸውም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ እና ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ እንደማይመሩ ይገልፃል። እንዲሁም በሕግና በተዘረጋ ሥርዓት መሠረት ካልሆነ በስተቀር ከዐቃቤ ሕግነት ሥራቸው እንደማይነሱ ይደነግጋል። ሞያዊ ነጻነት ዐቃቤያነ ሕግ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ከሚረዱ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን ከዐቃቤያን ሕግ ሥነ-ምግባር ጋር የተያያዙ የዐቃቤያነ ሕግ ግዴታዎች በደንቡ ክፍል አምስት ስር በዝርዝር ሰፍረው ይገኛሉ። እነዚህም፡-

  • ታማኝነት፡-ዐቃብያነ ሕግ በሥራ ነጻነታቸው የተጣለባቸውን እምነት መጠበቅ ያለባቸው ሲሆን ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ መላ ጉልበቱን፣ ሀሳቡንና ችሎታውን በታማኝነት ለመንግሥትና ለሕዝብ አገልግሎት ጥቅም ማዋል አለበት ( አንቀጽ 69)፡፡
  • የዐቃቤ ሕግ ጠባይ ፡- ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ የሕዝብን አክብሮትና እምነት እንዲያገኝ በመሥሪያ ቤቱም ሆነ ከመሥሪያ ቤቱ ውጭ በማናቸውም ጊዜ መልካም ጠባይና ሥነ-ምግባር እንዲኖረው የሚያስፈልግ ሲሆን በማንኛውም ጊዜ የሙያውን ክብር ለማስጠበቅ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ መገኘት ይኖርበታል።
  • ታዛዥነት፡-ዐቃቤ ሕግ ከቅርብ ሃላፊ ወይም ከበላይ ኃላፊው የሚሠጠው ትእዛዝ በግልጽ ከሕግ ውጭ ካልሆነ በቀር እንደትዕዛዙ መፈጸም ያለበት ሲሆን በማናቸውም አኳኋን የቅርብ ሃላፊ ወይም የበላይ ሃላፊ ለሚሠጠው ትእዛዝ ሕጋዊነት ተጠያቂ ነው፡፡
  • ገለልተኝነት፡-ዐቃብያነ ሕግ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ወይም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሳተፍ ወይም በሥራቸው ላይ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን መግለጽ ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ማሳየት የተከለከለ ሲሆን በማናቸውም ሁኔታ በሥራቸው ላይ የግል እምነታቸውን ወይም ኃይማኖታቸውን የሚያንጸባርቅ ተግባር መፈጸም የለባቸውም፡፡
  • ዐቃቤ ሕግ ከሕዝብ ጋር ስላለው ግንኙነት፡- ዐቃቤ ሕግ ያለፍራቻ፣ ያለአድሎ ወይም ያለምንም ጥላቻ በተለይም ከግለሰባዊና ከወገናዊ ጥቅም ወይም ከሕዝባዊና ከመገናኛ ብዙሃን ግፊት ተፅዕኖ ሳያድርበት የሕዝብ ጥቅም ብቻ በማስቀደም ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሰዎችን ሰብዓዊ መብትና ክብር ማክበር፣ መጠበቅና መደገፍ አለበት።
  • ምስጢር መጠበቅ፡- መረጃው ተራ ወይም በሕዝብ ዘንድ የታወቀ ካልሆነ ወይም መደበኛ ሥራውን በሕጋዊ መንገድ ለመፈጸም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በሥራው አጋጣሚ ወይም ምክንያት ወይም በሌላ አኳኋን ያገኘውን መረጃ ለማናቸውም ሰው መግለጽ የለበትም፡፡ በሕግ ሥልጣን በተሠጠው አካል ወይም ኃላፊ በአግባቡ ካልታዘዘ በስተቀር በአሠራር ምስጢር የተባሉትን መረጃዎች፣ ቃለ-ጉባኤዎች፣ የሥራ ዕቅዶችና እነዚህን የመሳሰለትን ምስጢራዊ ጉዳዮች ሁሉ በሥራም ላይ ሆነ ከሥራ ውጭ ለሌላ ማናቸውም ሰው መግለጽ የለበትም።
  • ገንዘብ መበደር፡- ዐቃቤ ሕግ አዘውትሮ ገንዘብ መበደር የተከለከለ ሲሆን በስራው ምክንያት ከሚያጋጥመው ባለጉዳይ ገንዘብ ለመበደር መሞከር ወይም መበደር ፍፁም ክልክል ነው።
  • ስጦታዎች፡- ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ ከሥራው ጋር በተያያዘ ለሠጠው ወይም ወደፊት ስለሚሠጠው አገልግሎት ከማንኛውም ሰው ማናቸውም ዓይነት ዋጋ ያለውም ሆነ የሌለው ስጦታ መጠየቅ ወይም መቀበል የለበትም፡፡
  • በመንግሥት ሥራና በግል ጉዳዮች ወይም ጥቅሞች መካከል ስለሚፈጠር ግጭት፡-ማናቸውም ዐቃቤ ሕግ የራሱ፣ የዘመዶቹ ወይም የወዳጆቹ የግል ጉዳይ ወይም ጥቅም ከሥራው ወይም በሥራው ምክንያት ከያዘው የሕዝብ ወይም የግለሰብ ጉዳይ ጋር የሚጋጭ ሆኖ ሲገኝ ይህንኑ ለቅርብ ኃላፊው ወዲያውኑ በማሳወቅ ጉዳዩ በሌላ ዐቃቤ ሕግ እንዲታይ ማመልከት አለበት፡፡
  • በመሥሪያ ቤቱ መገልገያዎች ስለመጠቀም፡-ዐቃቤያነ ሕግ ሥራቸውን በሚገባ ለመፈጸም ያህል ብቻ በመሥሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ መገልገያዎች መጠቀም ይችላሉ፡፡
  • ለሌላ ስለመሥራት፡- ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ በአግባቡ ሲታዘዝ ከሦስት ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ ለሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት ወይም ዓለም ዓቀፍ ድርጅት መሥራት አለበት። ለመሥሪያ ቤቱ የሚያበረክተውን አገልግሎት የሚያጓድል ወይም ለተሠጠው ሥራና ኃላፊነት ተቃራኒ የሆነ ወይም ከሥራውና ከሀላፊነቱ ወይም ከሙያ ሥነ-ምግባር ጋር የማይጣጣም ማናቸውንም የውጭ ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ ዐቃቤ ሕግ ከሥራ ሰዓት ውጭ ለፈጠራ፣ ለኪነ ጥበብ፣ ለጥናትና ምርምር፣ የሕግ ረቂቆችን ለማዘጋጀት፣ ለሳይንሳዊና ለትምህርታዊ ሥራ ካልሆነ በስተቀር የውጭ ሥራ ለመሥራት በቅድሚያ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉን ፈቃድ ማግኘት አለበት ( አንቀጽ 80)።
  • ስለ አለባበስ፡- ዐቃቤ ሕግ በሥራ ላይ እያለ በሕግ የሚደነገገውን የአለባበስ ሥርዓት ማክበር እንዳለበት በደንቡ 81 ስር የተደነገገ ሲሆን ለዚህ ደንብ አፈፃፀም ይረዳ ዘንድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤያነ ሕግ አለባበስ ሥርዓት እና ገጽታ መመሪያ ቁጥር 42/2017 ፀድቋል። በመቀጠል በመመረያ የተካተቱ አንኳር ጉዳዮችን እንመለከታለን።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤያነ ሕግ አለባበስ ሥርዓት እና ገጽታ መመሪያ ቁጥር 42/2017

አለባበስ የሰዎች ሥነ-ምግባር ከሚንፀባረቅባቸው መገለጫዎች አንዱ ነው። በመመሪያው በተሰጠው ትርጉም መሠረት አለባበስ ማለት በሰውነት ላይ ለተመልካች በሚታይ መልኩ የሚደረግ ማንኛውም ነገር ሲሆን በተለይም ልብስ፣ ጫማና ጌጣጌጥ አደራረግን ያካትታል። ገፅታ ማለት ደግሞ የአለባበስ፣ የፀጉር አቆራረጥ እንዲሁም በሰውነት ላይ የሚደረግ ማንኛውም ነገር ወይም የንፅህና አጠባበቅ ሁኔታ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ሊኖር የሚችል እይታ ነው።

ከመመሪያው መረዳት እንደሚቻለው የአለባበስ እና ገፅታ ሥርዓቱ ተፈጻሚ የሚሆነው በዐቃቤያነ ሕግ የሥራ ቦታ ሲሆን በመመሪያው እንደተሰጠው ትርጉም የሥራ ቦታ ማለት ዐቃቤ ሕግ መደበኛ ሥራውን የሚያከናውንበት ቦታ ሆኖ ቢሮን፣ ችሎት፣ ፖሊስ ጣቢያ ወይም ሌሎች ዐቃቤ ሕግ በትምህርት እና ሥልጠና ወይም በሥራ ምክንያት የሚሳተፍባቸውን ቦታዎች ያካትታል። ታዲያ ወንድ እና ሴት ዐቃቤያነ ሕግ በእነዚህ ቦታዎች ምን አይነት ልብስ መልበስ አለባቸው ገፅታቸውስ ምን መምሰል አለበት የሚለው ዝርዝር ጉዳይ በመመሪያው ተቀምጧል። በዚሁ መሠረት ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ የግል ንፅህናውን የጠበቀ፣ የሚጠቀምበት የሰውነት መዋቢያ እና ጌጣጌጥ የስራ አካባቢውን የማይረብሽ፣ የሚለብሰው ልብስ ሙያውን እና የተቋሙን ክብር የማያስነቅፍ ንጹህ፣ ያልተቀደደ፣ የተተኮሰና በልክ የተሰፋ መሆን አለበት።

እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ ለሥራው የተሰጠውን ካባ ንፅህና በመጠበቅ በአግባቡ መያዝና መልበስ ያለበት ሲሆን የችሎት አለባበስ ሥርዓትን የማክበር ግዴታ አለበት። ይህ በእንዲህ እያለ በሳምንት አንድ ቀን አርብ እለት ማንኛውም ዐቃቤ ሕግ መደበኛ የሆነ የሙያውንና የመስሪያ ቤቱን ክብር የማያስነቅፍ አለባበስ መልበስ ይችላል። በመቀጠል የወንድ እና የሴት ዐቃቤያነ ሕግ አለባበስ እና ገፅታን በተመለከተ በመመሪያው የሰፈሩ ዝርዝር ፕሮቶኮሎችን እንመለከታለን።

የወንድ ዐቃቤ ሕግ አለባበስ ሥርዓት እና ገፅታ

ወንድ ዐቃቤ ሕግ በስራው ቦታና ሠዓት ከጨርቅ የተዘጋጀ ኮት፣ ሱሪና ሸሚዝ በቆዳ ጫማ ወይም ከሙሉ ልብስ ጋር የሚለበስ ጫማ መልበስ አለበት። ኮት መልበስ ካልቻለ ሸሚዝ፣ ሸሚዝ በከረባት፣ ሸሚዝ በሰደሪያ ወይም ሹራብ መልበስ አለበት፤ ይሁንና በክረምት ወቅት የተቋሙን እና የሙያን ክብር የማይጥስ አለባበስ በተጨማሪነት መልበስ ይችላል። በሌላ በኩል በሌላ ሕግ በግልፅ በረሃማና ሞቃታማ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የሚሠራ ከሆነ ጨርቅ ሱሪና ሸሚዝ ለአካባቢው ከሚስማማ ጫማ ጋር መልበስ ይችላል። ፀጉሩን በንፅህና መያዝ፣ በአጭሩ እና በአግባቡ መስተካከል ያለበት ሲሆን ጥፍሩ በአጭሩ የተቆረጠ እና ንፁህ መሆን አለበት። በመሆኑም በሀይማኖት ወይም በሀዘን ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ፂሙን ከቢሮው እና ከመደበኛ አለባበስ ጋራ የተጣጣመ እንዲሆን መቆረጥና መስተካከል አለበት።

የሴት ዐቃቤ ሕግ አለባበስ እና ገፅታ

ሴት ዐቃቤ ሕግ በስራው ቦታና ሠዓት የጨርቅ ኮት ወይም ሹራብ ወይም ሸሚዝ ወይም ሸሚዝ በሰደሪያ ወይም ቆዳ በኮት አይነት የተዘጋጀ ከጨርቅ ሱሪ ወይም ከጉልበት በታች የሆነ የጨርቅ ቀሚስ በቆዳ እና መሰል ጫማ መልበስ አለባት። ይሁንና በክረምት ወቅት የተቋሙን እና የሙያን ክብር የማይጥስ አለባበስ በተጨማሪነት መልበስ ይቻላል። ይህ እንዳለ ሆኖ ነፍሰ ጡር የሆነች ዐቃቤ ሕግ የሚመቻትን ማንኛውንም ልብስ መልበስ ትችላለች። ፀጉሯ በአግባቡ የተያዘ እና ንፅህናው የተጠበቀ መሆን እንዳለበት መመሪያው ያስቀምጣል።

በተጨማሪም መመሪያው ለዐቃቤያነ ሕግ የተከለከሉ አለባበስ ሥርዓት እና ገፅታ ዝርዝር ክልከላዎችን በአንቀጽ 9 ስር ያሰፈረ ሲሆን ለአብነት ያክል ወንድ ዐቃቤ ሕግ በስራ ቦታ እና ሰዓት የፊትና የጆሮ ጌጣጌጥ ማድረግ፣ ፀጉር ከተፈጠሯዊ ቀለሙ ውጪ መቀባት፣ ማንጨባረር፣ ሹሩባ መሰራት እንዲሁም ድሬድ ማድረግ፤ ሱሪ ዝቅ አድርጎ መታጠቅ፣ የተቀዳደደ ወይም የሰውነት ቅርፅን የሚያሳዩ አልባሳትን መልበስ፣ በሚታይ ቦታ የሰውነት ክፍል ላይ ንቅሳት ወይም ታቶ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ለሴት ዐቃቤ ሕግም እንዲሁ የተቀዳደደ ወይም አግባብ ባለሆነ ሁኔታ የሰውነት አካልን አጋልጦ የሚያሳይ ከጉልበት በላይ የሆነ ቀሚስ መልበስ፣ ያልተለመደ ደማቅ የፀጉር ቀለም መቀባት፣ በማንኛውም ሁኔታ የሌላውን ሰው ክብር የሚነካ ወይም የፖለቲካ መግለጫ ህትመት ያለበት ልብስ ወይም ጌጣጌጣ ማድረግ የተከለከለ ነው።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ሥነ-ምግባር በሰው ልጆች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲደረግ ወይም እንዳይደረግ በማኅበረሰብ፣ በሞያ እንዲሁም በሀይማኖት የሚጠበቅ ባህሪ ሲሆን በተለይ ከሞያ አንፃር ባለሞያዎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ፣ በተገልጋዩ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያስችል የህይወት መመሪያ ነው። ዐቃቤያነ ሕግ እንደ ሕግ ባለሞያ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ሲወጡ መልካም ሥነ-ምግባርን መላበስ እና በሥነ-ምግባር ደንቡ እና መመሪው የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ማክበር ይኖርባቸዋል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ