በአዲሱ የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ የተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

መንግሥት የዜጎቹን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈን እና የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን መንግሥት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ ለዚህም አመች ይሆን ዘንድ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን በመወሰንና ተቆጣጣሪ ኤጀንሲውን በማቋቋም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህን አስመልክቶም የተለያዩ አዋጆች፣ ደንብ እና መመሪያዎች ወጥተው ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የግዥ ሥርዓትን ለመወሰን እና ተቆጣጣሪ ኤጀንሲውን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 430/1997፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 184/2002 እና የፌዴራል መንግሥት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ እና ማሻሻያዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 ለብዙ ጊዜያት ሲያገለግል ቆይቶ በፌደራል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 በሚለው ተተክቷል፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ የመንግሥት ግዥ ምንነት፣ የመንግሥት ግዥ አስፈላጊነት እና ዓላማ፣ የመንግሰት ግዥ አፈፃፀም መርሆች፣ የግዥና የንብረት ሕጉን መሻሻል (መተካት) ያስፈለገበት ምክንያት እና አዳዲስ የተካተቱ ጉዳዮች የሚሉትን የምንመለከት ይሆናል፡፡

የግዥና የንብረት ሕጉን መሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት

የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ በሀገራችን የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ሲሆን እንደ ወቅቱ እና እንደየ ጊዜው ሁኔታ ማሻሻያ እየተደረበት ሲያገልግል ቆይቷል፡፡ በሥራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 በይዘት እና አፈፃፀም ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ከአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1333/2016 መግቢያ መረዳት እንችላለን፡፡ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅን የተፈፃሚነት ወሰን እና መርሆችን በማስፋት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማድረግ እና የመንግሥት ግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደር ሥርዓቱን ግልጽነት በማሻሻል እና ተደራሽነቱን በማስፋት በመንግሥት ግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚከሰት የሕግ ጥሰት የሚያስከትለውን አስተዳደራዊ ተጠያቂነት (አንቀጽ 86) ግልፅ ለማድረግ ማሻሻያ ተደርገውበታል፡፡

የመንግሰት ግዥ ምንነት

የመንግሥት ግዥ የሚለውን ከማየታችን በፊት ግዥ ምን እንደሆነ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንቀጽ 2 ላይ በሰጠው ትርጉም መሠረት “ግዥ ማለት ዕቃዎችን፣ የምክር አገልግሎቶችን እና የግንባታ ዘርፍ ሥራዎች በመግዛት፣ በኪራይ፣ በሊዝ ስምምነት ወይም በማናቸውም ሌላ ተመሳሳይ ውል ማግኘት ነው፡፡”

የመንግሥት ግዥ ፡-

  • መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ለማስፈጸም በመዋቅሩ ማለትም፣ በመንግስታዊ አካል አማካኝነት የሚያከናውነው የዕቃዎች፣ የአገልግሎቶችና የሥራ (የግንባታ ዘርፍ ስራዎች) ግዥን ያጠቃልላል፡፡
  • እንደ ተባበሩት መንግስታት ድረጅት (ተ.መ.ድ) የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ አተረጓጎም የመንግሥት ግዢ የሚለው ሀረግ፣ የዕቃ፣ የአገልግሎት ወይም የግንባታ ዘርፍ ስራዎችን የመግዛት ሂደትን የሚያጠቃልል ሆኖ ግዢውን የሚፈጽመው አካል ህዝባዊ ድርጅት ወይም ማህበር ሊሆን ሲችል፣ ለግዢው ጥቅም ላይ የሚውለው ገንዘብ ግን የመንግሥት ሲሆን ነው፤ የሚል ትርጉም ተሰጥቶት ይገኛል፡፡
  • በሁለቱ የትርጉም ክፍሎች መካከል ያለው ልዩነት የገዢው ማንነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመንግሥት ገንዘብ የሚደረግ ማንኛውም የዕቃ፣ የአገልግሎት፣ የግንባታ ዘርፍ ሥራ ወይም ከእነዚህ መገልገያ እቃዎችና አገልግሎቶች ጋር ግንኙነት (ተያያዢነት) ያላቸውን ነገሮች በግዥ፣ በኪራይ ወይም በቅጥር ስምምነት መያዝ፣ ወይም ማግኘትን ያጠቃልላል፡፡
  • በአዲሱ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 2 (12) ላይ የመንግሥት ግዥ ለሚለው ቃል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የመንግሥት ገንዘብን በመጠቀም የሚያከናውኑት ግዥ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡

የመንግሥት ግዥ አስፈላጊነት እና ዓላማ

ማንኛውም በሕግ የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም፡-

  • ለአገልግሎት መስጫ የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች፣ አገልግሎቶችና ሌሎች ሥራዎች በትክክለኛው ጊዜ፣ በጥራትና በብቃት፤ እንዲሁም በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት ካልቻለ ተግባሩን ሊያከናውን አይችልም፡፡ በተጨማሪም ውጤታማ አገልግሎት የመስጠት ውስንነት ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ይህን ለማስተካከል አስፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡
  • ተፈላጊ ንብረቶችን፣ አገልግሎቶችን ወይም ስራዎችን ትክክለኛ በሆነ ጥራት፣ ብዛት፣ ዓይነት፣ ዋጋ፤ ትክክለኛ ከሆነ አቅራቢ በማግኘት በወቅቱ ለአገልግሎት ማዋል የሚል ዓላማ አለው፡፡

የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም መርሆች

በአዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንቀጽ 4 እንደተደነገገው የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም ተግባር የሚከተሉትን መርሆች መሠረት ማድረግ ይኖርበታል፡-

  • በግዥ አፈፃፀም ረገድ የመንግሥት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም ማስገኘት፣ (ቁጠባን፣ የአፈፃፀም ብቃትን እና ውጤታማነትን ማረጋገጥ)፣
  • በአዋጁ በተፈቀደው ልዩ አስተያየት ካልሆነ በስተቀር በዜግነት ወይም ከመወዳደሪያ መስፈርቶች ጋር ባልተያያዙ ሌሎች ምክንያቶች በዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል አድልዎ አለማድረግ፣
  • ማናቸውም የግዥ አፈጻጸምና የንብረት አወጋገድ ውሳኔ የሚሰጥበት መስፈርት እና እያንዳንዱ የግዥና የንብረት አወጋገድ ሂደት ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ግልጽ እና ፍትሐዊ መሆን፣
  • ማንኛውም የመንግሥት ግዥ በሚፈጸምበት እና ንብረት በሚወገድበት ወቅት በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የማያስከትል እና መልሶ መጠቀምን የሚያበረታታ መሆኑን ማረጋገጥ፣
  • የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ ሂደቶች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የተፈጸሙ መሆኑን ማረጋገጥ፣
  • የግዥ አፈጻጸምና የንብረት አስተዳደር ተግባራትን በታማኝነት መፈጸም፣
  • በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ላይ የተሰጡ ውሣኔዎች እና የተወሰዱ እርምጃዎች ተጠያቂነት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣
  • የቴክኖሎጂ ፈጠራን ማበረታታት፡፡

እነዚህ መርሆች የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሉ በመሆናቸው የግዥ እና የንብረት አስተደደር ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ይረዳሉ፡፡

አዳዲስ የተካተቱ ጉዳዮች

ነባሩ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ከወጣ 15 ዓመት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 1333/2016 እነዚህን ለውጦች ታሳቢ ባደረገ መልኩ የወጣ ሲሆን፡-

  1. ነባሩ አዋጅም ሆነ ከዚያ በፊት ያሉ ሕጎች የተፈፃሚነት ወሰናቸው በመንግሥት ግዥና ንብረት ላይ ብቻ ነበረ፡፡ አዲሱ አዋጅ ግን የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅን የተፈፃሚነት ወሰን በማስፋት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ሆኗል ፣
  2. የፌደራል መንግሥት ከአንድ ወይም ከአንድ በላይ ከሆኑ የሌሎች ሀገር መንግሥታት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ካደረገው ወይም ከሚያደርገው ስምምነት ወይም ከስምምነቱ ከመነጨ ግዴታ ጋር የማይጣጣም ከሆነ በስምምነቱ የተመለከተው ግዴታ ተፈፃሚ እንዲሆን መደረጉ፣
  3. የመንግሥት ግዥ አፈፃጸም እና የንብረት አስተዳደር መርሆች በዓይነት ሰፋ ብለው መቅረባቸው፣
  4. የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚበረታታ መሆኑ፣
  5. በአዋጁ አንቀጽ 9 መሠረት የፌደራል መንግሥት የግዥና ንብረት ባለሥልጣን መቋቋሙ፣
  6. የግዥ እና የንብረት አስተዳደር ሰነዶች መያዝ ያለበት መሆኑ፣
  7. በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በተወዳዳሪዎች፣ ተጫራቾች ወይም አቅራቢዎች መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲሆኑ መደረጋቸው፣
  8. ዘመናዊ የግዥ እና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱ ወዘተ…የሚሉት ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

የመንግሥትና የሕዝብን መብትና ጥቅም ለማክበርና ለማስከበር እንዲሁም ራስን ከኃላፊነት እና ከተጠያቂነት ለመጠበቅ ሲባል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሥራን በግልጽነት፣ በታማኝነት፣ በታታሪነት፣ በሐቀኝነት እና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም በጥንቃቄ መተግበር (መሥራት) ይገባል፡፡ በተጨማሪም በአዲሱ አዋጅ የተካተቱ የግዥ ዘዴዎች፣ ሥልቶች፣ እና የጨረታ ሥነ-ሥርዓት እና የውል አስተዳደር ድንጋጌዎችና የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ