መግቢያ
ሰዎች ሰው ሆነ በመፈጠራቸው የተለያዩ መብቶች ያሏቸው ሲሆን እነዚህ መብቶች ለሁሉም በእኩልነት ሊከበሩ ይገባል፡፡ ሆኖም ሴቶች በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው አለም በሚባል ደረጃ ለዘመናት መድሎ ሲደረግባቸው የነበረ ስለመሆኑ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ለምሳሌ የመምረጥና የመመረጥ መብት መነፈግ፣ የመሥራት መብት መነፈግ፣ ደፍረው ወደ ሥራ የሚገቡትን በሥራ ቦታ አድሎ መፈፀም ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ ሲገጥማቸው የነበሩ ችግሮች ነበሩ፡፡ በሀገራችንም ቢሆን ያለእድሜ ጋብቻ፣ የመማር እድል መነፈግ፣ በቤተሰብ አስተዳደር ውስጥ የመወሰን እድል መነፈግ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ወዘተ ለዘመናት የዘለቀ ሲሆን አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ለማለት አይቻልም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታትም በርካታ ሴቶች በተለያዩ ሀገራት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በአለም ደረጃ የነበረው ጥረትና ውጤት ለማሰብ በየአመቱ ማርች 8 በሀገራችንም ጭምር ይከበራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የማርች 8 ከሴቶች መብት ጋር ያለውን ግንኙነት እና በአለምና በሀገራችን ለሴቶች በሕግ የተሰጡ ጥበቃዎችን የምንመለከት ይሆናል፡፡
ማርች 8 ከሴቶች መብት ጋር ያለው ግንኙነት
የሴቶች መብት ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የደረሰው በረጅም አመታት ጥረት ሲሆን ማርች 8 ወይም ሴቶች ቀን የሚከበረው ሴቶች በባህላዊ፣ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለመብታቸው መከበር ያደረጉትን ጥረት እና ስኬት ለማሰብ ነው፡፡ ቀደም ሲል የሴቶች ቀን ጉዳይ ይነሳ የነበረው በሶሻሊስት ርዕዮተ አለም ተከታዮች እና ፓርቲዎች ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1909 ጀምሮ የሴቶች መብት አቀንቃኞች የተለያዩ ስብሰባዎችን ያደርጉ የነበረ ሲሆን በመላው አውሮፓም ሴቶች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም ጾታን መሠረት ያደረጉ መድሎዎች እንዲቆሙ ይጠይቁ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደቶች ግን የሴቶች ቀን የሚከበርበት እለት ከሀገር ሀገር ይለያይ የነበረ ቢሆንም በአብዛኛው በየካቲት (February) መጨረሻ እና በመጋቢት (March) መጀመሪያ ይከበር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ 1914 የሴቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ማርች 8 የተከበረ ሲሆን እ.ኤ.አ ማርች 8 1917 ደግሞ በሩሲያ ሴት የጨርቃ ጨርቅ ሰራተኞች ያነሱት አመፅ በመላው ሀገሪቱ የአብዮት መነሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 ሩሲያ ማርች 8 የሴቶች ቀን ሆኖ ሥራ የማይሰራበት ቀን እንዲሆን ከተደረገ በኋላ በሶሻሊስት ሀገራት የሚከበር ለመሆን የበቃ ቢሆንም እስከ እ.ኤ.አ1967 በዋናነት የኮሚኒስቶች በአል ሆኖ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1967 በኋላ ግን ቀኑ በአውሮፓ ለዓለም ዓቀፍ የሴቶች መብት መከበር ለሚደረገው ትግል መነሳሻ ሆነ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ሂደት ያለፈውን ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶች ዓመት ተብሎ ከተሰየመው እ.ኤ.አ 1975 ጀምሮ ማክበር የጀመረ ሲሆን እ.ኤ.አ 1977 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ (General Assembly) አባል ሀገራቱ ማርች 8ን የሴቶች መብት ቀን አድረገው እንዲያውጁ ጋብዟል፡፡ በዚህም መሠረት ማርች 8 ሴቶች በየጊዜው ለመብታቸው ያረጉት ረጅም ተጋድሎ መታሰቢያ ሆኖ እስካሁንም እየተከበረ ይገኛል፡፡
የሴቶች መብት በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች
የሴቶች መብት ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የሴቶች መብት በነባሮቹ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ውስጥ ጭምር የተካተተ ከመሆኑም በተጨማሪ ሴቶችን በልዩነት የተመለከተ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት እስከማድረግ ደርሷል፡፡ በመሆኑም ሴቶች የማኅበረሰብ አካል እንደመሆናቸው መብቶቻቸው ለሁሉም የሕግ ጥበቃ በሚያደርጉ የሰብአሰዊ መብት ሰነዶች እንዲሁም ሴቶችን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ በተደነገጉ ስምምነቶች ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ እንደሚከተለው እንመልከታቸው፡፡
በሰብዓዊ መብት ታሪክ ቀደምት የሚባለው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አብዛኛው ድንጋጌዎች የሚጀምሩት “Everyone” በሚል ሲሆን ወደ አማርኛው ስንመልሰው “እያንዳንዱ ሰው” እንደማለት ነው፡፡ ይህም ሁሉንም ሰው የሚያካትት አገላለፅ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች ሁሉንም ባካተተ መልኩ ከተደነገጉ ደግሞ ሴቶችንም ጭምር የሚያካትቱ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ለአብነት የሴቶች የረጅም ጊዜ ችግሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማየት ያህል በአንቀጽ 7 ሁሉም ሰው ያለምንም ልዩነት እኩል የሕግ ጥበቃ እንዳለው የደነገገ በመሆኑ አባል ሀገራት ለወንዶች እንደሚያደርጉት ሁሉ ለሴቶችም እኩል የሕግ ጥበቃ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአንቀጽ 17 እያንዳንዱ ሰው ንብረት የማፍራት መብት እንዳለው የደነገገ እንደመሆኑ ሴቶች ለዘመናት ሲቸገሩበት የነበረውን በተለይ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የማፍራት ክልክላ የሚያስወግድ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንቀጽ 16 እድሜያቸው የደረሰ ወንዶችና ሴቶች በዘር፣ በዜግነት፣ በሀይማኖት ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው ትዳር መመስረት እና ቤተሰብ የመመስረት መብት እንዳላቸው እንዲሁም ጋብቻው ሲመሠረት፣ በጋብቻው ዘመን እንዲሁም በፍቺ ወቅት እኩል መብት እንዳላቸው የሕግ ከለላ ሰጥቷል፡፡
ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR) በአንቀጽ 3 የስምምነቱ አባል ሀገራት ወንዶችና ሴቶች በስምምነቱ የተቀመጡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች በእኩልነት መጠቀም የሚችሉበትን ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በአንቀጽ 26 ሁሉም ሰው በዘር፣ በእድሜ፣ በቆዳ ቀለም፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በማኅበራዊ መሠረት ወዘተ ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሕግ ጥበቃ እንዳላቸው ከለላ ሰጥቷል፡፡ ከቤተሰብ ጋር በተያዘም በአንቀጽ 23 ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ሙሉ ፈቃድ መፈፀም እንዳለበትና ወንዶችና ሴቶች ጋብቻው ሲፈፀም እንዲሁም በፍቺ ወቅት እኩል መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡
የትምህርት፣ የባህል እና ማኅበራዊ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ስምምነት (ICESCR) በተመሳሳይ በአንቀጽ 3 የስምምነቱ አባል ሀገራት ወንዶችና ሴቶች በትምህርት፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በእኩልነት መጠቀም የሚችሉበትን ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ከቤተሰብ መመስረት ጋር በተያያዘ በአንቀጽ 10 በተጋቢዎች ሙሉ ፈቃድ መመስረት እንዳለበት እና አባል ሀገራትም የማኅበረሰብ ተፈጥሮአዊ መነሻ ለሆነው ቤተሰብ ጥበቃ ማድረግ እንዳለባቸው ግዴታ ጥሏል፡፡ በልዩ ሁኔታም ወላድ ሴቶች ከመውለዳቸው በፊት እና ከወለዱ በኋላ ምክንያታዊ የሆነ እረፍት ከክፍያ ጋር ወይም ከጥቅማ ጥቅሞች ጋር እንዲሰጣቸው የሚያስገድድ ድንጋጌ አካቷል፡፡ ሌላው በአለም ዙሪያ የሴቶች የመብት ጥያቄ የሆነውን የሥራ ሁኔታ በተመለከተ በአንቀጽ 7 ሴቶች በተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ ወንድ ሰራተኞች ተመሳሳይ የሆነ የሥራ ሁኔታ አንዲኖራቸው እና ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ክፍያ ማግኘት መብት እንዳላቸው ጥበቃ አድርጓል፡፡
ሴቶችን ከማንኛውም አድሎ ለመጠበቅ የተደረገው ስምምነት (CEDAW) ስሙ እንደሚያመለክተው በትምህርት፣ በፖለቲካ፣ በጤና እንዲሁም በሌሎች ማኅበራዊ ዘርፎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ መድሎዎችን የማስቀረት ኃላፊነት በአባል ሀገራት ላይ ኃላፊነት የሚጥል ስምምነት ነው፡፡
የሴቶች መብት በኢትዮጵያ ሕግ
በሀገራችን ለረጅም ዘመናት በሴቶች ላይ ሲደርስ የነበረውን አድሎ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ አዳዲስ ህጎች ከመደንገግ በተጨማሪ በነባሮቹ ህጎች ላይ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል፡፡ በሀገራችን ለሴቶች ያለውን የሕግ ጥበቃ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ሀገራችን ከላይ የጠቀስናቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች አባል ሀገር ናት፡፡ በዚህም በሥምምነቱ የተካተቱ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለባት፡፡ ይህን በተመለከተ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 13(2) በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተገለፁ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ሀገራችን ከተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደሚተረጎሙ የደነገገ እንደመሆኑ ከላይ የጠቀስናቸው መሠረታዊ መብትን የተመለከቱ ስምምነቶች የሀገራችን ሕግ አካል ተደርገው የሚፈፀሙ ይሆናል፡፡
ከዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በተጨማሪ በሀገራችን የህጎች ሁሉ የበላይ ሕግ የሆነው ህገ መንግሥት ለሴቶች እንደማንኛውም ዜጋ እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ለሴቶች ሊደረጉ የሚገባቸው የሕግ ጥበቃዎችን ደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 25 መሠረት ዜጎች በዘር፣ በብሄር፣ በጾታ፣ በቀለም፣ በሀይማኖት ወዘተ ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሕግ ጥበቃ እንዳላቸው የደነገገ በመሆኑ ሴቶች በማንኛውም ረገድ አድሎ እንዳይደርስባቸው ጥበቃ እንዲያገኙ መሠረት ጥሏል፡፡ በተጨማሪም ሴቶች
- በብሔራዊ ልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና ፕሮጀክት ዝግጅት፣ በተለይም የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ፕሮጀክቶች ሀሳባቸውን እንዲሰጡ መጠየቅ እንዳለባቸው
- መሬትን ጨምሮ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀም እና የማስተላለፍ እንዲሁም ውርስን በተመለከትም እኩል የመታየት መብት እንዳላቸው
- ከጎጂ ባህላዊ ተፅዕኖዎች የመላቀቅ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ እና መንግሥትም የህ ማስከበር እንዳለበት
- በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው
- ከቅጥር፣ ከሥራ እድገት፣ በክፍያ እና ጡረታን በማስተላለፍ ረገድ እኩል መብት እንዳላቸው
- በእርግዝና እና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የቤተሰብ ምጣኔ፣ መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት እንዳላቸው
- የወሊድ ፈቃድ ወይም የዕርግዝና ፈቃድ ከደሞዝ ጋር የማግኘት መብት እንዳላቸው
የሕግ ጥበቃ ከመስጠቱ በተጨማሪ ሴቶች በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረም እና ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች (affirmative action) ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የሕግ ጥበቃ አስቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ቀድሞ በፍትሐብሔር ህጉ ተካቶ የነበረውንና ወንጆችን የቤተሰብ መሪ የሚደርገው የቤተሰብ ሕግ በማሻሻል ሴቶች ጋብቻ ሲመሠረት፣ በጋብቻው ዘመን እንዲሁም በፍቺ ወቅት ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ በዚህም ሴቶች በልጆች አስተዳደግ፣ በንብረት አስተዳደር እና መሰል ቤተሰባዊ ጉዳዮች ከባሎቻቸው እኩል መብት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
ሌላው ሴቶች እክል ይገጥማቸው ከነበሩት ዘርፎች ውስጥ ይጠቀስ የነበረው ከሥራ ጋር በተያያዘ የነበረ ሲሆን የፌደራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 እንዲሁም የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዲታዩ ከማድረጋቸውም በላይ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርጓል፡፡ ይኸውም አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በአንቀጽ 87 እና 88 ሴቶች
- በጾታቸው ምክንያት ማንኛውም አይነት ልዩነት እንዳይደረግባቸው
- በቅጥር፣ በደረጃ እድገት፣ በማንኛውም የጥቅማ ጥቅም ውድድር ከወንዶች ጋር እኩል ከሆኑ ቅድሚያ የማግኘት
- ለሴቶች ከባድ ወይም ለጤናቸው ጎጂ ተብለው ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚዘረዝራቸው ሥራዎች ላይ አለመሰማራት
- ነፍሰጡር ሴት ከምሽቱ 4 ሰዓት እሰከ ንጋቱ 12 ሰዓት እንዲሁም በትርፍ ሰዓት ያለመሥራት፣ የምትሰራው ሥራ ለእራሷም ሆነ ለፅንሱ ጤንነት አደገኛ መሆኑን ሕክምና ካረጋገጠ ወደ ሌላ ቦታ የመመደብ
- ከመውለዷ በፊትና በኋላ ወይም ፅንስ ማቋረጥ እንዳጋጠማት በሕክምና ሲረጋገጥ በህጉ የተመለከተውን ፈቃድ ከደሞዝ ጋር የማግኘት እና ነፍሰጡር በሆነች ጊዜ ምርመራ ለማድረግ የሚያስፈልጋት ፈቃድ ከደሞዝ ጋር የማግኘት
መብት እንዳላቸው በግልፅ ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ የፌደራል የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 በአንቀጽ 41 በወሊድ ጊዜ እና ፅንስ ማቋረጥ ሲገጥም ከደሞዝ ጋር ሊሰጥ ስለሚጋባው ፈቃድ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
በሌላ በኩል በ1996 ዓ.ም የወታውና በሥራ ላይ ያለው ወንጀል ሕግ ከሴቶች መብት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎችንና የሚያስከትሉትን ቅጣት ደንግጓል፡፡ ለአብነት በአንቀጽ 561፣ 562፣ 565፣ 566 በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የሚስከትሉትን የወንጀል ተጠያቂነት በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ በተመሳሳይ አንቀጽ 638 ያለዕድሜ ጋብቻ፣ አንቀጽ 587 ሴትን መጥለፍ፣ በሴቶችና በልጆች መነገድን የተመለከቱ ድንጋጌዎች የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በዓለም ዓቀፍ እና በሀገራችን ደረጃ የሴቶችን መብት በተመለከተ ያሉት የሕግ ማዕቀፎች ከላይ የተገለፁት ሲሆኑ ሕግጋቱን ማክበርና ማስከበር የሁላችንም ሃለፊነት መሆኑን አውቀን ሀላፊነታችንን እንድንወጣ አደራ እንላለን፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት