የሕይወት መድን ውል በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

በዚህ ዘመናዊ ዓለም መድን ወይም የመድን አሠራር ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የሚሆነው መድን ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በመጋራትና ወደ ራሱ በማስተላለፍ በአደጋ የሚደርስ ጉዳት ስጋትን ስለሚቀንስ ነው፡፡

ዓለም በደረሰበት ውስብስብነት ባለው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የአደጋ ስጋት መጠኑ በዛው ልክ መጨመሩ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም መድን በዚህ ሂደት ውስጥ የሰዎችን ሕይወት እና ንብረት በመጠበቅ ረገድ ወሳኝ የሆነ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የመድን ገቢው ሕይወት ካለፈ በኋላም ቢሆን ለተጠቃሚዎች (ጥገኞች) ድጋፍነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለ ሕይወት መድን ምንነት፣ የሕይወት መድን ውል ባህርያት እና የሕይወት መድን ውል ዓይነቶች የሚሉትን እንመለከታለን፡፡

የሕይወት መድን ምንነት

የሕይወት መድን ውል በበርካታ ሀገሮች የሚታወቅ እና በየሀገራቱ ባለው የመድን ሕግ ትርጓሜ የተሰጠው ሲሆን የህንዱን የመድን ሕግ መሠረት በማድረግ ህንዳዊው የሕግ ምሁር ዲፒ ጃይን (D.P Jain, 1991 Mercantile Law) በሚለው መጽሀፉ እንደሚከተለው ተርጉሞት ይገኛል፡፡

“Life insurance is a contract by which the insurer in consideration of premium undertakes to pay a sum of money on the death of a person whose life is insured or on the expiry of a certain period whichever is earlier.”

ወደ አማርኛ ሲተረጎም የሕይወት መድን ውል ማለት መድን ሰጪው ስለ መድን ውሉ ሊከፍል የሚገባውን አረቦን ተቀብሎ፣ መድን ገቢው የሞተ እንደሆነ ወይም እስከተወሰነ ጊዜ በሕይወት የቆየ እንደሆነ (ከሁለቱ ሁኔታዎች ቀድሞ በተከሰተው)፣ ለመድን ገቢው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል የሚደረግ የውል ዓይነት ነው፡፡

በእኛም ሀገር በ1952 የንግድ ሕግ ቁጥር 691 ላይ ተመሳሳይ ትርጓሜ ተሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡

ይኸውም፡-

  • “የሕይወት ኢንሹራንስ (መድን) ማለት ባለኢንሹራንሱ አንድ ጊዜ ወይም ከአንድ ጊዜ በበለጠ ስለ ኢንሹራንሱ የሚከፍለውን ገንዘብ ተቀብሎ በተዋዋዩ ወይም ኢንሹራንስ በተገባበት ሦስተኛ ወገን ሕይወት ወይም ሞት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሁኔታዎች በደረሱ ጊዜ የተወሰነ ገንዘብ ለተዋዋዩ ወይም ለተጠቃሚው ለመክፈል የሚዋዋለው ውል ነው” በማለት ትርጓሜ ሰጥቶበት እናገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመድን ሥራን በጠቅላለው ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 746/2004 በአንቀጽ 2(23) ስር እንዲህ በማለት አስቀምጧል፡፡
  • “የሕይወት መድን“ ማለት መድን ሰጪው አረቦን በመቀበል የመድን ገቢው በሕይወት የመኖር ወይም ሞት ላይ ተመስርቶ በተፈፀመ ውል ለመድን ገቢው ወይም ለሌላ ተጠቃሚ አስቀድሞ የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል የሚገባው የመድን ውል ዓይነት ነው በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ጠቅለል ባለመልኩ ሲታይ በሕይወት መድን ውል ውስጥ ውሉ ሊይዝ የሚገባውን ዝርዝር ፍሬ ነገር የ1952ቱ የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አንደሚከተለው አስቀምጦ እናገኛለን፡፡

እነርሱም፡-

  • ሀ. ስለ ህይወት ኢንሹራንስ (መድን) የተደረገለት ሰው የግል ስም፣ የቤተ ዘመድ ስም እና የተወለደበት ቀን፣
  • ለ. ተጠቃሚው ተለይቶ የታወቀ እንደሆነ የተጠቃሚው ቤተ ዘመድ ስም እና የግል ስም፣
  • ሐ. የተስማሙበት ገንዘብ እንዲከፈል የሚደረግበት ሁኔታ፣
  • መ. ቅናሽ የሚደረግበትና መልሶ የሚገዛበት ሁኔታ በኢንሹራንስ (መድን) ፖሊሲው ውስጥ በትክክል መገለጽ አለበት፡፡ ይህም በ1952 የንግድ ሕግ ቁጥር 695 ላይ ተደንግጓል፡፡

የሕይወት ኢንሹራንስ (መድን) የሚባለው በመድን ገቢውና በመድን ሰጪው መካከል የሚደረግ የውል ስምምነት ሲሆን ውሉ ተነፃፃሪ ግዴታን የሚጥል ነው፡፡ ይህም ማለት በአንድ በኩል መድን የገባው ሰው ለመድን ሰጪው አረቦን የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን በሌላ በኩል መድን ገቢው ወይም መድን የተገባለት ሰው በሞተ ጊዜ መድን ሰጪው በፖሊሲው (የመድን ውል) ላይ ተጠቃሚ ነው ተብሎ ለተጠቀሰው ሰው የፖሊሲውን ገንዘብ የመክፍል ግዴታ አለበት፡፡ ከሕይወት መድን አጀማመር ጀርባ ያለው ምክንያት ለሰው ልጅ ሕይወት ክብርና ዋጋ ለመስጠት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

የመድን ውል ፈራሽ የሚሆንበት ሁኔታዎች

የሕይወት መድን ውል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1678 የተገለጹትን የውል አቋሞች ማለትም ውል ለመዋዋል ችሎታ ባላቸው ሰዎች መካከል፣ ጉድለት የሌለው ስምምነት መኖር፣ በቂ የሆነ እና እርግጠኝነት ያለው፣ የሚቻልና ሕጋዊ የሆነ ጉዳይ ላይ ብቻ መሆን ይገባዋል፡፡ ይኸውም የውሉ አፃፃፍ ፎርም (አይነት) በሕግ የታዘዘ ሆኖ እንደ ትዕዛዙ ባይፈፀም ፈራሽነትን የሚያሰከተል ሲሆን አንድ ልዩ ፎርም መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ በንግድ ሕጉ ቁጥር 694 ችሎታ በሌለው ሰው ወይም እንደራሴው ቢስማማም የሞተ እንደሆነ ተብሎ ችሎታ በሌለው ሰው የሚደርግ የመድን ውል ፈራሽ ነው፡፡

ማናቸውም ጥቅም ያለው ሰው ባቀረበው ጥያቄ የመድን ውል እንዲፈርስ ያደርጋል፡፡ ለመግቢያ የተከፈለውም ገንዘብ በሙሉ መመለስ አለበት በሚል መደንገጉ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1678 የተገለፁት የውል አቋሞች የግዴታ አስፈላጊ መሆናቸውን ያጠናክራል፡፡

የሕይወት መድን ውል ባህርያት

የሕይወት መድን ውል ከሌሎች የመድን ውል ዓይነቶች ለየት የሚያደርጉት የራሱ ልዩ ባህርያት አሉት፡-

  • መድን የሚገባበት ጉዳይ፡- በሕይወት መድን ለመድን ውል ፖሊሲ ወይም መድን ሽፋን የሚሰጠው ለሰው ልጅ ሕይወት ነው፡፡ በሌሎች የመድን ዓይነቶች የመድን ሽፋን ውስጥ የሚገባው ንብረት ወይም ዕቃ ነው፡፡ የሕይወት መድን የሚገባው ለሰዎች ሕይወት ነው፡፡
  • የድርጊቱ እርግጠኝነት፡- የመድን ሽፋን እንዲኖረው የተደረገ ንብረት ወይም ዕቃ ምንም ዓይነት አዳጋ ላይደርስበት ይችላል፡፡ በሕይወት መድን ሲገባ ሞት የማይቀር መሆኑን በማመን ነው፡፡ ሕይወት መድን የማይታወቀው ሞቱ መች ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡
  • ጉዳትን አለመካስ፡- ሰዎች የሕይወት መድን ሲገቡ ከሞት በኋላ ላሉት ተጠቃሚዎች በማሰብ የሚገቡት ነው፡፡ በመሆኑም በሕይወት መድን የሞትን ጉዳት መካስ አይቻልም፡፡

ጉዳትን መካስ የሚባለው በንብረት ወይም በዕቃ ላይ የደረሰውን አደጋ በገንዘብ መልክ (In cash) ወይም በአይነት በመተካት (Replacing) የደረሰውን ጉዳት በመካስ ተጎጂው ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ነው፡፡ ለሕይወት መድን የገባ ሰው ቢሞት ጉዳትን ለመካስ በሚል ወደ ነበረበት መመለስ አይችልም። የሰው ልጅ ሕይወትም በገንዘብ የሚተመን አይደለም። ምክንያቱም ጥፋቱ(ጉዳቱ) የሚመጣው በሞት ምክንያት በመሆኑ ነው። የሕይወት መድን ሲገባ ሕይወትን በገንዘብ መተመን አይቻልም። ነገር ግን ዋጋ ያለው ውል ነው (Valued Contract) በመሆኑም ተዋዋይ ወገኖች በስምምነት ምን ያህል አረቦን እና የመድን ክፍያ ሊከፈል እንደሚችል ሊወስኑ ይገባል፡፡ በንግድ ሕግ ቁጥር 689 እና 690 ላይ እንደተገለፀው የሕይወት መድን የሟችን ጥገኞች (ተጠቃሚዎች) ሊመጣባቸው ከሚችለው ኢኮኖሚ ቀውስ ለመከላከል ጠቀሜታ አለው፡፡

የውል ዘመን፡- ሌሎች የመድን ዓይነቶች የውል ቆይታቸው ዓመት ወይም ከዚያም በታች ሊሆኑ ይችላሉ። የሕይወት መድን የውል ስምምነት ግን ረዘም ላለ ጊዜ ለ10 ወይም ለ20 ዓመታት ያህል የሚቆይ ሊሆን ይችላል፡፡

የሕይወት መድን ውል ዓይነቶች

በኢትዮጵያ በ1952 ዓ.ም በወጣው የንግድ ሕግ ዕውቅና የተሰጣቸው የሕይወት መድን ውሎች ሦስት ሲሆኑ እነሱም ኢንደውመንት የሕይወት መድን (endowment life insurance)፣ የዕድሜ ልክ የሕይወት መድን (whole life insurance) እና የሁለቱ ቅንጅት ናቸው፡፡

እንደየ ሀገራቱ ሁኔታ የተለያዩ የሕይወት መድን ውሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሕንድ ሀገር የመድን ሕግ ውስጥ የሕይወት መድን ውል ”whole life insurance” እና “endowment insurance” ተብለው ለሁለት በሚከፈሉ ምድቦች ይታወቃሉ። ቀጥለን የኢትዮጵያን የሕይወት መድን ውሎች የምንዳስስ ይሆናል።

  1. ኢንደውመንት የሕይወት መድን፡- በአንዳንድ የመድን ፖሊሲዎች አረቦን የሚከፈለው በአንድ የተወሰነ ጊዜ ድረስ ይሆናል፡፡ ይህ በውሉ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ መድን ገቢው በሕይወት ካለ በውሉ ይከፈላል ተብሎ የተወሰነው ገንዘብ ለመድን ገቢው ይከፈለዋል። ነገር ግን ከዚህ ከተወሰነው ቀን በፊት መድን ገቢው የሞተ እንደሆነ የአረቦን ክፍያው መከፈሉ ወዲያው ያቆማል። መድን ገቢው የዚህ ዓይነት ፖሊሲ ሲገዛ ሊስማማ የሚችለው ለምሳሌ የዛሬ 20 ዓመት በሕይወት ካለሁ የፖሊሲው ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት ሊሆን ይችላል፡፡ የንግድ ሕጉ ቁጥር 692(1) ስለ ኢንደውመንት የሕይወት መድን ሲደነግግ “የሕይወት ኢንሹራንስ (መድን) የሚዋዋለው ኢንሹራንስ ሰጪ ኢንሹራንስ የገባው ሰው በኢንሹራንሱ ውል ውሰጥ በተወሰነ ጊዜ በሕይወት ያለ እንደሆነ የተወሰነ ዋና ገንዘብ በሕይወት እስካለ ድረስ ወይም በየጊዜው የሚከፈል ገንዘብ ለመክፈል ነው” በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡ በሕይወት ከቆየ በእርጅናው ጊዜ የሚያጋጥሙትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቋቋም ሲሆን ክፍያው በአንድ ጊዜ ወይም በተወሰነ ጊዜ ሊፈፀም ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህ ዓይነቱ የህይወት መድን አስገዳጅ የሆነ ቁጠባን በማበረታት ኢንቨስትመንትን ያሳድጋል፡፡
  2. የዕድሜ ልክ የሕይወት መድን፡- በአንዳንድ የመድን ፖሊሲዎች መድን ገቢው በሕይወት እስካለ ድረስ አረቦን መክፈል አይቆምም፡፡ አረቦን መክፈል የሚቆመው መድን ገቢው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እና የኢንሹራንሱ ገንዘብ ለተጠቃሚው ሲከፈል ይሆናል፡፡ በመሆኑም በዕድሜ ልክ የሕይወት ኢንሹራንስ የመድን ገቢውን ሞት ተከትሎ የፖሊሲው ገንዘብ ለተጠቃሚዎች ይከፋፈላል፡፡ የዕድሜ ልክ የሕይወት ኢንሹራንስ (መድን) ፖሊሲ ብዙ ጊዜ ከፍ ያለ ክፍያ የሚጠየቅበት ሲሆን ውሉ በአንድ አጋጣሚ ቢፈርስ መድን ገቢው ውሉ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረሰ የከፈለውን አረቦን ተስልቶ ተመላሽ ይደረግለታል፡፡ የዕደሜ ልክ የሕይወት መድን ለሞት የሚገባ መድን ተብሎ በንግድ ሕጉ በቁጥር 692(2) ላይ የተመለከተ ሲሆን የድንጋጌው ይዘትም መድን ሰጪው የተዋዋለው ኢንሹራንስ ስለገባው ሰው ሞት የሆነ እንደሆነ ኢንሹራንስ ከገባው ሰው መብት ላላቸው ውይም በመድን ውል ውስጥ ለተጠቀሰው ተጠቃሚ የተወሰነ ዋና ገንዘብ ወይም በሕይወት እስካለ ድረስ በየጊዜው የሚከፈል ገንዘብ መድን ገቢው በሞተ ጊዜ ለመክፈል የሚል ነው፡፡
  3. የሁለቱ ቅንጅት፡- በሦስተኛነት በንግድ ሕጉ ዕውቅና የተሰጠው የሕይወት መድን ውል የሁለቱ ቅንጅት ነው፡፡ ይህም ማለት በንግድ ሕግ ቁጥር 692(3) መሠረት መድን ሰጪው በዚህ ቁጥር ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሰውን የመክፈል ግዴታ የገባ ሲሆን የተጣመረ የመድን ውል መዋዋል እንደሚችል ተመላክቷል፡፡ በዚህ መሠረት መድን ገቢው ከመድን ሰጪው ጋር የሚዋዋለው በተወሰነ ቀን ወይም ጊዜ ውስጥ በሕይወት ኖሬ ከተገኘው የፖሊሲው ገንዘብ ለራሴ ይከፈለኝ፣ ነገር ግን የተባለው ቀን ከመድረሱ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየሁ እንደሆነ በውሉ ላይ ለተጠቀሰው ተጠቃሚ የፖሊሲው ገንዘብ ይከፈል የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

የመድንን ውል ቀሪ ስለማድርግ (Termination of Insurance Policy)

ተዋዋይ ወገኖች የውል ግዴታ ለማቋቋም እንደሚችሉ ሁሉ ይህንን ግዴታ ለማስቀረት መብት ይኖራቸዋል፡፡ ውል ንብረትን የሚመለከት ግዴታ የሚቋቋምበት፣ የተቋቋመው ግዴታ ቀሪ የሚደረግበት ወይም የሚሻሻልበት ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1675 ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ የመድን ፖሊሲ በ1952 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ቁጥር 654(1) መሠረት በራሱ ውል ነው፡፡ የመድን ውል በሚከተሉት ምክንያቶች ቀሪ ሊሆን ይችላል፡፡

  • ውሉ በተዋዋይ ወገኖች በመፈፀሙ፣
  • የመድን ገቢው (የመድን ሰጪው) በመክሰሩ፣
  • የመድን ውል ተጠቃሚው በመሞቱ፣
  • የመድን ሽፋን የተሰጠው ንብረት ለሌላ በመተላለፉ፣ እና
  • የመድን ሰጪውን የአዳጋ አስተያየት ሊለውጥበት የሚችል ፍሬ ነገርን ሆነ ብሎ መሸሸግ የሚሉት ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የሕይወት መድንን ስናነሳ የሰው ልጆች መቼ ጉዳት ሊደርሰብን እንደሚችል፣ መቼ እንደምንሞት አለማወቃችን የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡

የሕይወት መድን ሰዎች በድንገት ሕይወታቸው ሲያልፍ በእነርሱ ስር የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን ለመጠበቅ የሚያስችል ስለሆነ የሟች ጥገኞች (ተጠቃሚዎች) ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ለመከላከል የሕይወት መድን መግባት ጠቃሚ ነው።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይክቶሬት የተዘጋጀ