የማህበራዊ ሚዲያን ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ በሆነና የሰዎችን ነፃነትና ክብር በሚጋፋ መልኩ መጠቀም የሚያስከትለው ተጠያቂነት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መጠኑ ይብዛም ይነስም ብዙዎቻችን የዕለት ተዕለት ስራዎቻችንን ለመከወን ከምንጠቀምባቸው ነገሮች መካከል ከበይነመረብ (Internet) ጋር የተቆራኙ የተለያዩ መተግበሪያዎች (Application) ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን የተለያዩ መልእክቶችን ለመለዋወጥ፣ ስራዎቻችንን እና አገልግሎታችንን ለማስተዋወቅ፣ የተለያዩ ስሌቶችንና ትንታኔዎችን ለማከናወን፣ ከፍ ሲልም እንደ ChatGPT እና DeepSeek የመሳሰሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በመጠቀም በባህሪያቸው ከዚህ ቀደም የሰው ልጅ ብቻ ሊያከናውናቸው የሚችሉ የፈጠራና ኪነጥበባዊ ይዘት ያላቸው ስራዎች ሳይቀሩ በበይነመረብ አማካይነት በቀላሉ መሥራት የሚቻልበት ወቅት ላይ ተደርሷል። በይነመረብ ተደራሽነታቸውን ካቀለላቸውና በሰፊው ከምንጠቀማቸው እጅግ በጣም ዝነኛ ከሆኑ መካነ ድሮች መካከል የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች ይገኙበታል። ከአለም ሕዝብ በጠቅላላው 63.9% የሚሆነው ቢያንስ አንደኛውን አይነት የማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀም መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተገነቡት የተለያዩ ትምህርታዊ ሃሳቦችንና መረጃዎችን፣ ፎቶግራፎችን እና የግል መረጃን ለማጋራት፣ የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ እና በጠቅላላው ማኅበራዊ ቁርኝትን ለማጠናከር ነው። በዚህም ሂደት ዜጎች “ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ” ሰብዓዊ መብታቸውን ከምንግዜውም በተሻለ መጠን እንዲጠቀሙበት አስችሏል። በዓለም ዓቀፍም ሆነ በሀገር ደረጃ ማንኛውም ሰው በነጻነት የመናገርና የመሰለውን ሀሳብ የመግለጽ መብት አለው። ይህ በሀገራችን ህገ መንግሥት እንዲሁም ሀገራችን ባፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የሕግ ጥበቃ የተደረገለት መብት ነው፡፡ ሆኖም እነዚሁ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች መብቱ በጠባቡም ቢሆን ሊገደብ ስለሚችልበት ሁኔታ አመላክተዋል፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው በሕግና ይህን መብት ለመገደብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ሲሆን ይህ መብት ከሚገደብባቸው ምክንያቶች መካከል የሌላን ሰው መብት ለመጠበቅ፤ የማህበረሰቡን ሞራል (Public morals) ለመጠበቅ፤ የማህበረሰቡን ሰላምና ደኅንነት (Public order) ለመጠበቅ እንደሆነ ከህጎቹ አጠቃላይ መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ ዜጎች የማኅበራዊ ገፆችን በመጠቀም ሀሳባቸውን በነጻነት የመግለፅ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ ግን አገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የአለም ሀገራት ውስጥ ሰዎች እነዚህን ድረገጾች ለታለመላቸው በጎ ተግባራት ከማዋል ይልቅ በተቃራኒው ለእኩይ ተግባራት ለምሳሌ የጥላቻ ንግግሮችን እና የሐሰት መረጃዎችን ለማሰራጨት፣ ኢ-ግበረገባዊ እና የማህበረሰቡን እሴቶች የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ሲጠቀሙት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ መነሻ በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ ናቸው ስለሚባሉ ተግባራት ምንነት፣ እንዲሁም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነና የሰዎችን ነጻነትና ክብር የመጋፋት ይዘት ያላቸውን ፅሁፎች፣ ምስሎች፣ ቪዲዮች እና የመሳሰሉትን ነገሮች በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ማሰራጨት ስለሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት ለመዳሰስ ተሞክሯል።

ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር ምንነት

ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር ማለት ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው፣ የማያስከብር፣ ጨዋነት የጎደለው፣ ወይም በቀላሉ መጥፎ የሆነ ተግባር ማለት ነው። ይህ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን እንደ ሁኔታው የተለያዩ ድርጊቶችን ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ፦

  • ባህላዊ እሴቶችን መጣስ:- በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ አክብሮት፣ ታማኝነት፣ እና ጨዋነት ያሉ እሴቶች ሲጣሱ።
  • የሞራል መርሆዎችን አለማክበር:- እንደ ሐቀኝነት፣ ፍትሕ፣ እና ርህራሄ ያሉ መርሆችን አለመከተል።
  • ሌሎችን መጉዳት:- አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ማኅበራዊ ጉዳት ማድረስ።
  • ማጭበርበር እና ማታለል:- ሌሎችን ለግል ጥቅም መጠቀም።
  • ስርቆት እና ዝርፊያ:- የሌላ ሰው ንብረት ያለፈቃድ መውሰድ ወዘተ የመሳሰሉትን ሊያጠቃልል ይችላል።

በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ “ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር” ማለት ምን ማለት እንደሆነ በቀጥታ በትርጉም ባያስቀምጥም ተግባራቱ ምንን እንደሚያካትቱ በዝርዝር ተቀምጠው እናገኛለን። ለምሳሌ፡- በወንጀል ህጉ አንቀጽ 639 የብልግናና አሳፋሪ ስራን በአደባባይ መፈፀም፣ አንቀጽ 640 ፀያፍ ወይም የብልግና ነገሮችን ለሕዝብ መግለፅ፣ አንቀጽ 641 ፀያፍ የሆኑ ነገሮችን ማሳየት ፣ አንቀጽ 643 ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ መግለጫዎችና ማስታወቂያዎችን ለሕዝብ እይታ ማቅረብ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ እንደሆነ ተግባር ይቆጠራል። በአጠቃላይ “ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር” ማለት ከህብረተሰቡ መልካም እሴቶች እና መርሆች ጋር የማይስማማ ማንኛውም ተግባር ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያን ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ በሆነ ያልተገባ መንገድ መጠቀም የሚያስከትለው ተጠያቂነት

ያልተገባ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሲባል ሌሎችን የሚጎዳ፣ የሚያስቀይም፣ የሚያዋርድ፣ ወይም በአጠቃላይ ከተገቢ የስነምግባር ደንቦች ጋር የማይጣጣም ማንኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ነው። ይህ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፦ የጥላቻ ንግግር እና አድልዎ (በዘር፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በጾታዊ ዝንባሌ፣ ወዘተ ላይ የተመሠረተ ጥቃት ወይም መድልዎ)፣ ትንኮሳ እና ዛቻ (ሌሎችን ሰዎች ማስፈራራት፣ ማስጨነቅ ወይም ማዋረድ)፣ ስም ማጥፋት እና ስድብ (ስለ አንድ ሰው የተሳሳቱ ወይም ጎጂ መረጃዎችን ማሰራጨት)፣ ግላዊነትን መጣስ (የሌላ ሰው የግል መረጃዎችን ያለፈቃዱ ማጋለጥ ወይም ማሰራጨት)፣ የሐሰት መረጃ ማሰራጨት (ሆን ተብሎ የተሳሳቱ ወይም የተዛቡ መረጃዎችን ማሰራጨት)፣ አግባብ ያልሆነ ይዘት ማጋራት (እንደ ፖርኖግራፊ፣ ጥቃት፣ ወይም ራስን ማጥፋትን የሚያበረታቱ ምስሎች ወይም ቪዲዮዎች ያሉ ናቸው)።

መሰል ተግባሮች በግለሰቦች መብት እና በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ተግባራት ስለመሆናቸው በተለያዩ ህጎች ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል የተወሰኑትን ከዚህ በታች እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን፡-

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 640 ስር ጸያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለሕዝብ መግለጽ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሲሆን ማንም ሰው ጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ በጽሁፍ፤ ምስሎችን፤ ስዕላዊ መግለጫዎችን /ፖስተሮችን/፤ ፊልሞችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ያዘጋጀ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጭ ሀገር የላከ፤ ያጓጓዘ፤ የተቀበለ፤ የያዘ፤ ለሕዝብ ያሳየ፤ ለሽያጭ ወይም ለኪራይ ያቀረበ፤ ያከፋፈለ፣ ያሰራጨ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ከቦታ ቦታ ያዟዟረ ወይም እነዚህን ነገሮች የነገደ እንደሆነ ነገሮቹ ተወርሰው ከመወገዳቸው በተጨማሪ ከ6 ወር በማያንስ ቀላል እስራትና በመቀጮ ይቀጣል። በተመሳሳይ መልኩ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 641 መሠረት ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን እንዲታይ ያደረገ ሰው በወንጀል እንደሚቀጣ ይደነግጋል። ሌላው የወንጀል ህጉ አንቀጽ 644 መሠረት ማንም ሰው ለጥቅም ወይም ስሜትን ለመቀስቀስ ሲል ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን የግብረ ስጋ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ከልክ በላይ ለመቀስቀስ፣ ለማበላሸት ወይም ለማሳሳት ወይም ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የጭካኔ ወይም የገዳይነት ዝንባሌን ወይም ጸረ ማኅበራዊ የሆኑ ወይም ቤተሰባዊ ኑሮ የሚያናጉ ስሜቶችን ከመጠን በላይ ለማነሳሳት፣ ለመቀስቀስ ወይም ለማሳደር የሚችሉ ፅሁፎችን፣ ምስሎችን፣ ወይም ነገሮችን ለሕዝብ ሊታይ በሚችል ስፍራ በማስቀመጥ በቪዲዮ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ እንዲታይ ያደረገ፣ ለአካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ እያወቀ ያቀረበ እንደሆነ እንደአስፈላጊነቱ የእቃው መወረስ እንዳለ ሆኖ ከ6 ወር እስከ 3ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራትና በመቀጮ ይቀጣል።

የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ 958/2008

የኮምፒውተር ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 12(ሀ) እና (ለ) መሠረት ማንም ሰው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ወሲባዊ ድርጊት ሲፈፅም የሚያሳይ ወይም አዋቂ ሰው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ መስሎ ወሲባዊ ድርጊት በግልፅ ሲፈፅም የሚያሳይ ስዕላዊ መግለጫ፣ ፖስተር፣ ቪዲዮ ወይም ምስል የኮምፒውተር ስርዓትን በመጠቀም ያዘጋጀ፣ ያሰራጨ፣ ሌሎች እንዲያገኙት ያመቻቸ ወይም ያለፍቃድ ይዞ የተገኘ ከ3 ዓመት እስከ 10ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ የደነገገ ሲሆን በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር (2) ስር ደግሞ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮችን፣ ስዕሎችን፣ የጽሑፍ መልእክቶችን ወይም ቪዲዮዎችን በኮምፒውተር ስርዓት አማካይነት በማሰራጨት ወይም በመላክ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን ለወሲባዊ ድርጊት ያነሳሳ ወይም የመለመለ እንደሆነ ከ5 ዓመት እስከ 10 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል። አሁን አሁን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተለይም በቴሌግራም፣ በቲክቶክ እና ፌስቡክ ላይ የተለያዩ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ፀያፍ ፅሁፎችንና ምስሎችን ማጋራት እና ቪዲዮዎቹንም ሌሎች ሰዎች በቀላሉ እንዲያገኙት ለማስቻል የሚከፈቱ ቻናሎችን ማየት እየተለመደ የመጣ ተግባር ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ይህ ተግባር ፍጹም ከስነምግባር ያፈነገጠ መሆኑን ቢረዳም የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አያውቅም፣ ቢያወቅም በቸልተኝነት ያልፈዋል። ስለሆነም ህብረተሰቡ ይህን በመገንዘብ የዚህ አይነት ተግባር ሲፈጸም ባየና ባወቀ ሰዓት ለፍትሕ አካል ጥቆማ በማድረግ የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።

ማኅበራዊ ሚዲያን የሰዎችን ነጻነትና ክብር በሚጋፋ መልኩ መጠቀም የሚያስከትለው ተጠያቂነት

ሌላኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ካመጣቸው ነገሮች መካከል አንዱ የግለሰቦች ግላዊ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ ለሌሎች ሰዎች ተጋላጭ እንዲሆን ማድረጉ ነው። ይሄም ዜጎችን በተለያየ መልኩ ለሚቃጣ ወንጀሎች አጋልጧቸዋል። በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገፆች ላይ የሰዎችን ክብር የሚነኩ ስድቦች፣ ዛቻዎች፣ ግለሰባዊ ሚስጥሮችን ማጋለጥ የመሳሰሉ የሰዎችን ሰላማዊ ህይወት የሚያናጉ ተግባሮችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል። መሰል የወንጀል ድርጊቶች የሚያስከትሉትን የወንጀል ተጠያቂነት ቀድሞ በማሳወቅ ለመከላከል እና ተፈፅመውም ሲገኙ ፈፃሚዎቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማስቻል ታስበው ከወጡ ህጎች መካከል አንዱ የሆነውን የኮምፒውተር ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 13 (1) የተመለከትን እንደሆነ ማንኛውም ሰው የኮምፒዩተር ሥርዓትን በመጠቀም በሚያሰራጨው ጽሁፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ ወይም ስዕል አማካኝነት በሌላ ሰው ወይም በተጎጂው ቤተሰቦች ላይ ከባድ ጉዳት ወይም አደጋ ለማድረስ በማሰብ ያስፈራራ ወይም የዛተ እንደሆነ ከ3 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም እንደወንጀሉ ከባድነት ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል። የዚሁ ድንጋጌ ንዑስ ቁጥር (2) ደግሞ ማንን ሰው ተጎጂውን ወይም ቤተሰቦቹን የሚመለከት መረጃ ወይም መልእክት በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካኝነት በተደጋጋሚ በመላክ፣ በማሰራጨት ወይም የተበዳዩን የኮምፒዩተር ኮምዩኒኬሽን በመከታተል ፍርሃትን፣ ስጋትን ወይም የሥነ-ልቦና ጫናን የፈጠረ እንደሆነ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም እንደወንጀሉ ከባድነት ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል። ንዑስ ቁጥር (3) ስር ማንም ሰው የሌላን ሰው ክብር ወይም መልካም ስም የሚያጎድፍ ጽሁፍ፣ ንግግር፣ ስዕል ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒዩተር ሥርዓት አማካኝነት ያሰራጨ እንደሆነ፣ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከብር 30ሺ በማይበልጥ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል በማለት ይደነግጋል። በተመሳሳይ መልኩ ከግለሰቦች መልካም ስምና ክብር አጠባበቅና ግለሰባዊ ነጻነት ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈፃሚዎች ተጠያቂ የሚሆኑባቸው የሕግ ድንጋጌዎች በወንጀል ህጉም ላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ።

ሌሎች አግባብነት በሌለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ምክንያት የሚኖሩ ተጠያቂነቶች

ከፍ ሲል የተዘረዘሩት የሕግ ማዕቀፎች ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያን ኢ- ግብረገባዊ ለሆኑ እና እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮችን እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማሰራጨት በሚያውሉበት ጊዜ ሊኖር የሚችል ተጠያቂነት የሚያመላክቱ ናቸው። ነገር ግን ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ ጭምር የሚውሉ እንደመሆኑ በዚህም ረገድ የማስታወቂያ ሕግን (አዋጅ ቁጥር 759/2004) ማወቅ የሚገባ ሲሆን በአዋጁ በማስታወቂያ ሂደት ልንከተላቸው የሚገቡ ጉዳዮችንና ይህንኑ ስንተላለፍ የሚያስከትሉት ቅጣት በዝርዝር ደንግጓል። ሌላው የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ 1112/2012 አንቀጽ 67(19) የተመለከትን እንደሆነ በአዋጁ እና አዋጁን ለማስፈፀም በሚወጡ ህጎች መሠረት ማስተዋወቅ፣ ፕሮሞት ወይም ስፖንሰር ማድረግ የተከለከለን ቁጥጥር የሚደረግበትን እንደ ምግብ፣ መድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያ፣ የውበት መጠበቂያ፣ ትምባሆ ወዘተ የመሳሰሉ ምርቶች ማስተዋወቅ ከ3ዓመት በማይበልጥ እስራት እና ከብር 50ሺ በማያንስ መቀጮ ያስቀጣል። ሌላው ይሄንን የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመግታት ታስበው ከወጡ ህጎች መካከል አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ዋነኛው ነው። በዚህ አዋጅ መሠረት አሰተኛ ንግግርን እና የጥላቻ ንግግሮችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ማሰራጨት የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ መቀጮ እና የእስራት ቅጣቶች እንደሚያስቀጣ ተደንግጎ ይገኛል።

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ከፍ ሲል ከተጠቀሱት የወንጀል ቅጣቶች በተጨማሪ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ለሚያስከትለው ጉዳት የፍትሀ ብሔር ተጠያቂነት ጭምር ሊያስከትልብን እንደሚችል ተገንዝበን ማኅበራዊ ሚዲያ ካስገኘልን በጎ በጎ ነገሮች በተጨማሪ ከአጠቃቀማችን በሚመነጭ የሕግ መተላለፍ ምክንያት ከሚመጣ ተጠያቂነት ራሳችንን መጠበቅ ይገባል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና የተዘጋጀ