መግቢያ
በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት በሰፊ እና በድምቀት ከሚከበርባቸው ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በዓላትን ለማድመቅ ዜጎች የተለያዩ ግባዓቶችን ከአዘቦት ቀናት በተለየ በብዛት የሚጠቀሙበት እና የሚሸምቱበት ወቅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዓላት በመጡ ቁጥር የግባዓቶች ዋጋ መናር ይታያል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ዋጋ ማናርና ሸቀጦችን የመደበቅ ተግባር የሕግና የሞራል ተጠያቂነት በአጭሩ ይዳሰሳል፡፡
ተገቢ ያልሆነ ዋጋ መጨመር
ለአንድ ሀገር የዋጋ ንረት መከሰት በዋነኝነት ሁለት ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች ያሉ መሆናቸውን የስነ-ቁጠባ ባለሞያዎች ይገልፃሉ። እነዚህም ከፍላጎት መጨመር የመነጨ የዋጋ ንረት(demand push inflation) እና የማምረቻ ዋጋ መጨመር(cost push inflation) ናቸው። ከእነዚህ ምክንያቶች አንፃር ሲመዘን በሀገራችን የተከሰተው የዋጋ ንረት እዚህ ደረጃ ሊደርስ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አመክንዮ የለውም ወደሚለው ድምዳሜም ይደርሳሉ ምሁራኑ።
ሀገራችን የምትከተለው የኢኮኖሚ ስርዓት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ቢሆንም በየትኛውም ሀገር ቢሆን መንግሥት ጣልቃ የማይገባበት የገበያ ኢኮኖሚ የለም። መጠኑ ይለያይ እንጂ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ የሚከተሉ የበለጸጉትም ሆኑ ታዳጊ ሀገራት የገበያ ጉድለት ሲያጋጥማቸው መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ጉድለቱን የሚሞላበት አሠራር አለ። ኢትዮጵያም ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ ልትሆን አትችልም።
በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/06 በአንቀጽ 25 ሥር “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የንግና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዋጋ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ጥናት አድርጎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በማስፈቀድ ዝርዝራቸውንና ዋጋቸውን በሕዝብ ማስታወቅያ ሊያሳውቅ ይችላል” በማለት ተደንግጓል፡፡
በመሆኑም የንግዱ ማሕበረሰብ ይህ አሠራር ያለ መሆኑን ተገንዝቦ በተለይም በበዓላት ወቅት ሊተገበር የሚችል በመሆኑ ነቅቶ መከታተልና መተግበር ይጠበቅበታል፡፡ የንግድ ሚኒሰቴርም በሸማቹ ሕብረተሰብ ለበዓላት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የሆኑትን ምርቶች የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው እየለየ ሕጉ ባስቀመጠለት ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ቁጥጥር፣ ክትትል እና እርምት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡
በበዓላት ወቅት በርካታ ወገኖች ካላቸው ጥቂት ነገር ለተቸገረው በማካፈል ለወገን አለኝታነታቸውን በማስመስከር ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በዓላትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በእጃቸው ላይ ያለን የንግድ ዕቃ በሕገ-ወጥ መንገድ በመደበቅ ገበያው ላይ ሰው ሰራሽ ዕጥረት እንዲፈጠር በማድረግ ሸማቹ እንዳይረጋጋና አማራጭ እንዲያጣ ካደረጉ በኋላ ባሻቸው ዋጋ የሚሸጡ፤ በወቅቱ ወደገበያ ያቀረቡትን ዕቃም ቢሆን ተመሳጥረው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ተመን በመተመን ተገቢ ያልሆነ ትርፍ የሚያጋብሱ ግልሰቦች አሉ፡፡
ነገር ግን ይህ በሀገር እና በወገን ላይ ከፍተኛ ጫና በሚያሳድር መልኩ የሚደረግ የዋጋ ማናር ተግባር ከሐይማኖቶች አስተምህሮም ሆነ ከሞራል አንፃር ብናየው በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለውና አስነዋሪ ድርጊት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን የበዓላት ወቅት ሁሉም እንዲደሰት ተባብረንና ተደጋግፈን ማለፍ የሚገባን ሆኖ ሳለ በሀገርና በወገን ላይ ሌላ ተጨማሪ ችግር መፍጠር የአንድ መልካም ዜጋ መገለጫ አይደለምና በጥብቅ ልናስብበት ይገባል፡፡
የንግድ ዕቃን ስለማከማቸት/መደበቅ
ዕቃን ማከማቸት እና መደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር የገቢያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረትን ከሚያስከትሉ ተግባራት መካከል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የዕቃውን በገበያ ላይ ያለውን ተፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአቅርቦት ችግር በሌለበት ሁኔታ የአቅርቦት ችግር ያለ በማስመሰል በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ሊያከማቹ እና ሰው ሰራሽ እጥረት ፈጥረው በከፍተኛ ዋጋ የመሸጥ ተግባር ሲፈፅሙ ይስተዋላሉ። ይህ የንግዱ ማኅበረሰብም ሆነ ሸማቹ ያለአግባብ የንግድ ዕቃን የማከማቸት ተግባር በዜጎች ላይ ወይም እንደ አጠቃላይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተፅእኖ በጣም ከባድ ነው።
በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት አንድ ነጋዴ ከመደበኛ የግብይት ስርዓት ውጭ ወይም ነጋዴ ያልሆነ ሰው ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውል መጠን በላይ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በገቢያ ላይ እጥረት ያለበት መሆኑ በወጣ የሕዝብ ማስታወቂያ የተገለፀ የንግድ ዕቃን ማከማቸት ወይም መደበቅ ክልክል መሆኑ ተደንግጓል። ነገር ግን ከተገቢው የንግድ አሠራር ውጪ ማከማቸትም ሆነ መደበቅ የማይቻለው በገበያ ላይ ዕጥረት ያለበትን የንግድ ዕቃ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የንግድ ዕቃ መሆኑን የአዋጁን አንቀጽ 23(3) እና 24ን በጣምራ በማንበብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይኼውም በአንቀጽ 23(3) ላይ “ሚኒስቴሩና ቢሮዎች በነጋዴዎች የሚፈፀም የንግድ ዕቃዎች ክምችት ወይም የመደበቅ ተግባር ላይ ቁጥጥር ያደርጋሉ” ተብሎ መደንገጉ ሲታይ የተጠቀሱት ተቋማት በሕገወጥ ነጋዴዎች የሚደረግን የምርት ማከማቸትና መደበቅ እየተቆጣጠሩ የንግድ ሥርዓቱን ሚዛን የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም የንግዱ ማሕበረሰብ ማንኛውንም ዓይነት የንግድ ዕቃ መደበቅ ወይም ማከማቸት ክልክል መሆኑን ተገንዝቦ እራሱን ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር መቆጠብ ይጠበቅበታል፡፡
የማከማቸት እንዲሁም የመደበቅ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን በተመለከተ የአዋጁ አንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 ላይ የተቀመጡ ድንጋጋጌዎች የተከማቸውን እቃ እንዲሁም ማጓጓዣውን መውረስን ጨምሮ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እና የገንዘብ ቅጣቶችን አስቀምጠዋል።
ማጠቃለያ
በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ እንዲሁም በሞራል ደረጃም የሕዝብ በዓላትን ጠብቆ ዋጋ ማናር እንዲሁም እቃዎችን ከገቢያ ላይ መደበቅ ተገብነት የለሌው በሕግም የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ተግባር የሚፈፅሙ ኃላፊነት የጎደላቸው ነጋዴዎች ከዚህ ተግባራቸ መቆጠብ እና ለህብረተቡ በተገቢው እና ተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን ማቅረብ ይሆርባቸዋል፡፡ አንዲሁም ሸማቾችም እንዲህ ያለ ተግባር የሚፈፅሙ ነጋዴዎችን በመጠቆም መብታቸውን ማስከበር ይኖርባቸዋል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ