መግቢያ
የመሬት ሀብት የከበረና ውስን ሀብት በመሆኑ አጠቃቀሙ በጥንቃቄ ሊመራ ያስፈልጋል፡፡ የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ሀገራት የተለያየ ፖሊሲ ይከተላሉ፡፡ በሀገራችን ኢትዮያጵያ ስለመሬት ባለቤትነትና ይዞታ ከፖሊሲም በላይ በሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ የሚመራ መሠረታዊ ሀብት ነው፡፡
በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 40(3) መሠረት የመሬት ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት በግለሰብ ደረጃ መሬትን የመጠቀም እንጂ በባለቤትነት የመያዝ መብት የለም ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው መንግሥት የግል ንብረትን መውሰድ እንደሚችል በዚሁ ድንጋጌ በንዑስ አንቀጽ 8 ስር ተደንግጓል፡፡ የግል ንብረት በሚወሰድበት ጊዜ በነፃ ሳይሆን አስፈላጊው ካሳና የማቋቋሚያ እርምጃዎች ተወስደው መሆን ስለሚገባው እራሱን የቻለ ሕግና ስርዓት ያስፈልገዋል፡፡ መሬት የግል ንብረት ባይሆንም በመሬቱ ላይ የሚያርፍ የግል ባለይዞታዎች መዋእለ ንዋይ ስለሚኖር ሲለቀቅም ይህንን መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡
በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ፅሑፍ የመሬት መለቀቅን አስመልክቶ ያሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን ማለትም ስለመሬት ማስለቀቅና የሕዝብ ጥቅም ምንነት፣ መሬትን በማስለቀቅ ጊዜ ስለሚፈፀም ስነ-ስርዓት፣ ስለካሳ አከፋፈልና መልሶ ማቋቋም የምንዳስስ ይሆናል፡፡
የመሬት ይዞታ ማስለቀቅ ምንነትና አስፈላጊነት
የመሬት ይዞታ መስለቀቅን አስመልክቶ ገዥው ሕግ “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1161/2011” እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 1336/2016 ሲሆን የመሬት ይዞታ ማስለቀቅ ምንድን ነው? ለሚለው ፅንሰ ሀሳብ ቀጥተኛ ትርጉም አልሰጠውም። ሆኖም የመሬት ይዞታ ማስለቀቅ ማለት በግለሰቦች ወይም በደርጅቶች የተያዙ መሬቶች ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆነው ሲገኙ በቋሚነት ወይም በጊዚያዊነት በመንግሥት የሚወሰድበትና ለሌላ ዓለማ የሚውልበት ስርዓት ስለመሆኑ ከአዋጁ አጠቃላይ ይዘት መረዳት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለው ነጥብ ነው። ለሕዝብ ጥቅም የሚለው ሀረግ ከተለያዩ ዓላማዎች አንፃር የተለያየ አንድምታና ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ለምሳሌ ከወንጀል ፍትሕ አንፃር ሲታይ ክስ ላለመመስረት እና ክስ ለመመስረት የሕዝብን ጥቅም የሚሰጠው ትርጓሜ የተለያየ ሲሆን፤ ክስ ላለመመስረት ሲሆን የወንጀሉ ዓይነት በጣም ቀላል መሆን፣ የተከሳሹ በዕድሜ መጃጀት ወይም በማይድን በሽታ መያዝና ጉዳዩን በፍርድ ቤት መከታተል አለመቻል፣ የባህላዊ ሕጎች ተግባራዊነት፣ ብሔራዊ ደኅንነት ወይም ዓለማቀፋዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ጉዳት ወዘተ ግምት ውስጥ ይገባሉ። ክስ ለመመስረት ሲሆን ደግሞ በኢትዮጵያ ሕጎች እና ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ በሰው ልጅ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀልች ተብለው የተደነገጉትን የሰው ዘር በማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ በመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን በመሰወር ወይም ኢ-ሰብዓዊ ድብደባ የመፈፀም ወንጀል የሕዝብ ጥቅም የሚለውን መስፈርት እንደሚያሟሉ በኢ.ፌ.ድ.ሪ. የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ቁጥር 3.12 እና 3.13 ስር ሰፍሯል። የመሬት ይዞታ ማስለቀቅን በተመለከተ ግን ከዚህ አረዳድ በተለየ መልኩ የሚታይና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማጎልበት እንዲሁም ለሕዝብ የተሻለ የጋራ ጥቅምና ዕድገት ያመጣል ተብሎ በካቢኔ ታምኖበት የሚወሰን ውሳኔ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 2(1) ላይ ተደንግጓል። ካቢኔው ወደዚህ ውሳኔና መደምደሚያ የሚደርሰውም በዘፈቀደ ሳይሆን የመሬት አጠቃቀም ዕቅድን፣ አጠቃላይ የልማት ዕቅድን ወይም የመሰረተ ልማት መሪ ፕላንን መሠረት አድርጎ መወሰን እንደሚገባው በድንጋጌው ላይ ተመላክቷል።
የመሬት ይዞታን ለማስለቀቅ ስለሚፈፀም ስነ-ስርዓት
ለተሻለ የሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬቱ መለቀቅ አስፈላጊ ቢሆንም የመሬት ባለይዞታዎች ከመሬታቸው ሲለቁ የሚደርስባቸው በርካታ ችግሮች እንደሚኖሩ እሙን ነው። በመሆኑም ሁለቱን ጉዳዮች ሚዛናዊ የሚያደርግ ስረዓት መዘርጋት አስፈላጊ ስለሆነ በአዋጁ ላይ ዝርዝር የአካሄድ እና የአፈፃፀም ስርዓት ተዘርግቶለታል።
መሬት ለማስለቀቅ ስለሚፈፀም ስነ-ስርዓት
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የሚመለከተው አካል የመሬት ይዞታን ከማስለቀቁ በፊት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ቀዳሚው የሚለቀቀው መሬት ለሕዝብ ጥቅም መሆኑን ማረጋገጥና በቅድሚያ መወሰን ይገባል (አ/ቁ 1161/11 አን. 5)። አግባብ ያለው የመንግሥት አካል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬት እንዲለቀቅ ሲወስን በተጓዳኝ ለካሳና ለመልሶ መቋቋሚያ የሚያስፈልገው በጀት በማን እንደሚሸፈን ጭምር አብሮ መወሰን ይገባዋል። የልማት ተነሺን ከቦታው ማስነሳት የሚቻለው ካሳና ምትክ ቦታ/ቤት ከተሰጠ በኋላ ስለሆነ የካሳና ምትክ ቦታ ጉዳይም ቀድሞ መዘጋጀት ወይም መለየት ያለበት ጉዳይ ነው (አ/ቁ 1161/11 አን. 8(1)(ሰ))።
የሚመለከተው አካል መሬት ሲያስለቅቅ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች መከተል እንደሚገባው በአ/ቁ 1161/11 አን. 8(1) ተደንግጓል፡-
- ተነሺዎች ከመነሳታቸው በፊት ቢያንስ ከ1 ዓመት በፊት እንዲያውቁት ማድረግ፤ አስቸኳይ በሚሆን ጊዜ ቢያንስ ከ6 ወር በፊት በማወያየት እንዲያውቁት ማድረግ (ደንብ ቁጥር 472/12 አን. 4(5))
- የባለመብትነት ማስረጃ፣ ካሳ የሚከፈልባቸውን ንብረቶች የልኬትና መጠን መረጃ መሰብሰብ፤ ከውይይት በኋላ የሚጨመሩ ንብረቶች ካሳ ላይ አይካተቱም
- ካሳና ሌሎች ተያያዥ ክፍያዎችን መክፈል
- ለተነሺዎች በፅሑፍ የማስለቀቂያ ትእዛዝ መስጠት
- በመጨረሻም ካሳና ምትክ ቦታ የተጠናቀቀባቸውን ቦታዎች መረከብ የሚሉ ናቸው።
ቅድሚያ የማልማት መብት
የመሬት ይዞታዎች ለተሻለ የሕዝብ ጥቅም ያስፈልጋሉ ተብለው ቢወሰኑም ባለይዞታዎች የማልማት ፍልጎት ካለቸው ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው በአዋጁ አንቀጽ 7 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ነገር ግን ማንኛውም ባለይዞታ አለማለሁ ስላለ ብቻ ይሰጠዋል ማለት ሳይሆን የአካባቢው ማስተር ፕላንና ሊሰራ ከታቀደው ልማት አንፃር እንዲሁም የባለይዞታው የማልማት አቅም በጥንቃቄ ተጠንቶ ሊሆን ይገባዋል። ለምሳሌ በሚለቀቀው መሬት ላይ ሊሰራ የታሰበው ልማት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከሆነ የቅድሚያ ማልማት መብት የሚባለው ጉዳይ ሊቀርብ የሚችል አይደለም። ነገር ግን እንደ ፋብሪካ ወይም ሆቴል ወይም መዝናኛ ስፍራ ከሆነ ግን በፕላኑ መሠረት ለመሥራት በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው ማልማት የሚችሉ መሆኑን በደንቡ አንቀጽ 8 እስከ 12 ባሉት ድንጋጌዎች እስከ ዝርዝር አፈፃፀሙ ሰፍሯል።
የካሳ አከፋፈል እና ምትክ ቦታ ስለመስጠት እና መልሶ ስለማቋቋም
ስለካሳ
ስለካሳ አሰላልና አከፋፈል የተለያዩ ጉዳዮች ግምት ውስጥ ገብተው ነው የሚሰላው። የሚለቀቀው መሬት የከተማ ወይስ የገጠር ነው የሚለው የራሱ የሆነ የአሰላል ልዩነት ስላለው ቀድሞ መለየት ያለበት ጉዳይ ሲሆን እንደሚከተለው ይሰላል፡-
- የከተማ መሬት ሲሆን፡-
የሚለቀቀው መሬት የከተማ ሲሆን ሦስት የካሳ ዓይነቶች ማለትም የንብረት፣ የኢኮኖሚ ጉዳት እና ለማሕበራዊ ትስስር መቋረጥና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶች የሚከፈሉ ካሳዎች ናቸው።
የንብረት ካሳ (አን. 12)፡- የሚለቀቅ መሬትን አሰመልክቶ የሚሰላው ካሳ በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እና በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ ማሻሻያ (ምንጣሮ፣ ድልደላና የእርከን ስራ፣ ውሃ መከተር፣ የግቢ ንጣፍና ማስዋብ የመሳሰሉት) የሚያጠቃልል ሆኖ ሁሉም ሲሰላ የወቅቱንና የአከባቢውን የገበያ ዋጋ መሠረት ያደረገ እና ቢያንስ ዝቅተኛውን የቤት መስሪያ ዋጋ ሊሆን ይገባል።
የኢኮኖሚ ጉዳት (አንቀጽ 14)፡- የኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ የሚከፈለው ቦታው በመለቀቁ ምክንያት ከአካባቢው የሚኖሩና ያልለቀቁ ሰዎች ቦታው በመለቀቁ ምክንያት ከመቀጠር፣ ከመነገድ ወይም ከማከራየት ያገኙ የነበረው ገቢ ሲቀርባቸው የሚከፈል ካሳ ነው።
የማኅበራዊ መቋረጥና የስነ-ልቦናዊ ጉዳት ካሳ፡- ከአካባቢያቸው የሚለቁ ሰዎች ለዓመታት የገነቡት ማሕበራዊ ትስስር ስለሚቋረጥባቸው በዚህ ሳቢያ በስነ-ልቦና መጎዳታቸው አይቀሬ ነው። ለዚህም ስነልቦናቸውን ለመጠገን የሚያስችል በአንድ ጊዜ የሚከፈል ከ25 ሺ እስከ 60 ሺ ሊደርስ የሚችል ካሳ እንደሚከፈል በደንቡ አን. 30 ላይ ተደንግጓል። የስነ-ልቦና ጉዳት ካሳው ለሚነሱት ብቻ ሳይሆን ጉዳቱ መድረሱ እስከተረጋገጠ ድረስ ላልተነሱት የማሕበረሳብ ክፍሎችም ተግባራዊ እንደሚደረግ ተደንግጓል።
- የገጠር መሬት ሲሆን (አን. 13)
የሚለቀቀው መሬት የገጠር የእርሻ መሬት ከሆነ ከተወሰደበት መሬት ተመጣጣኝ ምርት የሚያስገኝ መሬት (ከተገኘ) እና በተጨማሪነትም ከመልቀቁ በፊት በነበሩት 3 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛውን የ1 ዓመት ገቢ በወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ እንዲከፈለው ይደረጋል። ምትክ መሬት ካልተገኘለት ግን በመሬቱ ላይ ሲያገኝ የነበረውን ከፍተኛውን ዓመታዊ ገቢ በ15 ተባዝቶ መከፈል አለበት። ይህ ስለ እርሻ ቦታ የሚመለከት ሲሆን ከመኖሪያው ለሚነሳ የገጠር ነዋሪ ምትክ ቦታና የልማት ተነሺ ድጋፍ ይደረግለታል።
ጠቅለል ሲል የመሬት ይዞታ የሚለቀቀው ለተሻለ ልማታዊ ፋይዳ ሲባል ብቻ እና የሕዝብ ጥቅም የሚያስከብር ስለመሆኑ በሚመለከተው ካቢኔ ወይም እሱ በወከላቸው አካላት ከተረጋገጠና ከተወሰነ በኋላ መሆን ይኖርበታል። እነዚህም አካላት ውሳኔውን ሲያሳልፉ እንደ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ፣ የልማት ዕቅድና ማስተር ፕላንን መሠረት ሊያደርጉ ይገባል። ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ከአንድ ዓመት በፊት ሕዝቡን ማወያየትና አስፈላጊ የሚባሉ የሰነድ ማጥራት፣ የመረጃ ማሰባበሰብ፣ ካሳ የመክፈል፣ ምትክ ቦታ የማዘጋጀት እንዲሁም ተነሺዎችን መልሶ ስለማቋቋም ስራዎች አብረው ጎን ለጎን መሰራት ያለባቸው ስለመሆናቸው በሕጉ ተመላክተዋል።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና የተዘጋጀ