የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ዳኝነት ችሎት በአዋጅ ቁጥር 813/2006 የተቋቋመ ሲሆን ዓላማውም የንግድ ስራ ሀገሪቱ በምትከተለው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት ህጋዊ የሆነ አሠራርን ተከትሎ እንዲሄድ ለማድረግ፣ የንግዱን ህበረተሰብ ከጸረ- ውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ለመከላከል እንዲሁም ሸማቹ ህብረተሰብ ላወጣው ዋጋ ተመጣጣኝ የሆኑ የንግድ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተቋቋመ ነው፡፡
የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ዳኝነት ችሎት ሥልጣን እና ኃላፊነት
ዳኝነት ችሎቱ ፡- በመቋቋሚያ አዋጁ ክፍል ሁለት ላይ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በመተላላፍ የሚፈጸሙ ተግባራት ሲኖሩ ማለትም ፡-
የገበያ የበላይነትን አለአግባብ መጠቀም ፣ በነጋዴዎች መካከል የሚደረጉ ጸረ-ውድድር ስምምነቶች ፣ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር ተግባራት እና ህገወጥ ውህደት በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ ውይም ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እና ቅጣት የመጣል እንዲሁም ጉዳት የደረሰበት ነጋዴ ለደረሰበት ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንዲካስ የማድረግ እንዲሁም የሸማቾች መብቶችን በአዲስ አበባ እና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በተፈፀመ ግብይት የተነሳ ጉዳት የደረሰባቸው ሸማቾች ለደረሰባቸው ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንዲካሱ የማድረግ ሥልጣን አለው ፡፡
ችሎቱ የሚወስዳቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች እና ቅጣቶች
አስተዳደራዊ እርምጃዎች
- ተገቢ አይደለም የተባለው ድርጊት እንዲቆም ማድረግ፣
- የተጎጂውን የመወዳደር አቅም ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ የሚያስችል ተገቢ እርምጃ መውሰድ፣
- የአጥፊውን የንግድ ፍቃድ እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ ማድረግ
አስተዳደራዊ ቅጣት
ድንጋጌዎች በተላለፉ ነጋዴዎች ላይ ችሎቱ ከነጋዴው አጠቃላይ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢ ላይ ከ 5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት የመቅጣት እና ይህንን ተከታትሎ የማስፈፀም ሥልጣን እና ተግባር አለው ፡፡
ችሎቱ የአስፈጻሚ አከላትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት በፍትሕ ሚኒስቴር ስር ሆኖ እንዲደራጅ በደነገገው መሠረት በአዋጅ ቁጥር 813/2006 የተሰጠውን ስራ እና ኃላፊነት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ስር ሆኖ ስራውን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን የሚገኝበት አድራሻም አራዳ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፊት ለፊት የፍትሕ ሚኒስቴር አራዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በሚገኝበት ሕንጻ 8ኛ ፎቅ ላይ ነው፡፡
በመሆኑም የገበያ የበላይነትን አለአግባብ መጠቀም ፣ በነጋዴዎች መካከል የሚደረጉ ጸረ-ውድድር ስምምነቶች ፣ ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር ተግባራት እና ህገወጥ ውህደት በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ ወይም ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ክስ ወይም አቤቱታ ማቅረብ ሲፈልጉ ከላይ በተጠቀሰው ችሎት ተገኝታችሁ አገልግሎቱን ማግኘት የምትችሉ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡