መግቢያ
ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት ዓለም አቀፋዊ መብት ሲሆን ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀችው የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ (UDHR፣1948) አንቀጽ 19 ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ሀሳቡን በነጻነት የመግለጽና የመሰለውን አስተያየት የመስጠት መብት አለው። ይህ መብት ያለምንም ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነት በማናቸውም ዓይነት መገናኛ መረጃዎችና ሀሳቦችን የመፈለግ፣ የመቀበልና የማስተላለፍ ነጻነትን እንደሚጨምር በድንጋጌው ላይ ሰፍሮ ይገኛል። በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 (4) ላይ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሀሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል የመገናኛ ብዙኃን በተቋምነታቸው የአሠራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖራቸው የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።
የመገናኛ ብዙኃን መሠረታዊ ተግባር መረጃን ከአንድ ወገን ወደ ሌላው ማሰራጨት እንደመሆኑ መጠን ይህን መረጃ የማሰራጨት ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ መረጃዎቹን በነጻነት ማግኘት መብት አላቸው። በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ጽሁፍ ስለ መረጃ ነጻነት፣ መረጃ የማግኘት መብትና መረጃን ለሚዲያዎች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ስለሚኖር ግዴታና ግዴታውን አለመወጣት የሚያስከትለውን ተጠያቂነት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የመረጃ ነጻነት ምንነት
የመረጃ ነጻነት የሚለውን ሐረግ ምንነት ከማየታችን በፊት መረጃ የተባለው ወሳኝ ቃል ምንድን ነው የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል። የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 2(6) ላይ “መረጃ ማለት በማንኛውም ዓይነት ቅርፅ የተቀናበረ ማንኛውም ዓይነት ሰነድ ነው” ሲል ትርጉም ሰጥቶታል። በዚህም መሠረት መረጃ ማንኛውም ቅጂ፣ ምልልስ፣ ጥሬ ሀቅ፣ የግል አስተያየት፣ ምክር፣ የውስጥ ማስታወሻ፣ ዳታ፣ ስታቲስቲክስ፣ መፅሐፍ፣ ሥዕል፣ ዕቅድ፣ ካርታ፣ ዲያግራም፣ ፎቶግራፍ፣ የድምፅ ወይም የምስል ቅጅ፣ ወይም ማንኛውም ሊጨበጥ የሚችልና የማይጨበጥ ቁስ ሊያጠቃልል ይችላል (አማኑኤል አብርሀም “የመረጃ ነጻነት በኢትዮጵያ” ከተሰኘው መፅሐፍ)።
የመረጃ ነጻነት ሲባል ደግሞ የሰዎች የመናገር ወይም ሀሳብን የመግለፅ፣ መረጃ የመፈለግ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብትን ያካተተ ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ ነው። የመረጃ ነጻነት መኖር ዜጎች የሀገራቸውን ጉዳይ እንዲረዱና በተገቢው ሁኔታ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከማስቻሉም በላይ፤ መብትና ግዴታቸውን ተረድተው ስለመብታቸው እንዲጠይቁና ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ያስችላቸዋል።
መረጃ የማግኘት መብት
መረጃ የማግኘት መብትን በሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29(2) እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለፅ ነጻነት ያለው ሲሆን ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በህትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው ማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም አይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነትን የሚያካትት እንደሆነ በግልፅ ተቀምጦ እናገኘዋለን (አዋጅ ቁጥር 1238/13 አንቀጽ 48ን ይመለከታል)።
ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረት ዴሞክራሲያዊ መብት በመሆኑ ይህ መብት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታ አለ። በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 29(6) እንደተመለከተው የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት ላይ ሕግን መሠረት ያደረገ ገደብ ሊደረግ ይችላል። ሌላው ጦርነትን የሚቀሰቅሱ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ መሠረት በሕግ የተከለከሉ እንደሆነ ተመላክቷል። ዜጎች ወይም ማንኛውም ህጋዊ የሚዲያ አካል መረጃን በተቻለ መጠን በፍጥነትና በዝቅተኛ ወጭ የማግኘት መብት አላቸው።
የመረጃ ጥያቄ በፍጥነትና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መስተናገድ አለበት። ይህን ሊፈታ የሚችል የመረጃ ጥያቄ አቀረራብና ቅሬታ አሰማም ሥርዓት ያስፈልገዋል። መረጃን የማግኘት መብት በመረጃ ፈላጊው አካል ሲጠይቅ እና ሳይጠየቅ የሚፈፀም መብት ሲሆን መረጃ ሳይጠየቅ መረጃ የማግኘት መብት የሚተገበረው መረጃው በመንግሥት አካል ሲገለፅ ነው። የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ እና በተጠያቂነት መርህ መከናወን እንዳለበት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። የመንግሥት አካላት በግልፅነትና በተጠያቂነት መንፈስ ስራቸውን ማከናወን ያለባቸው በመሆኑ ለሕዝብ መገለፅ ያለባቸውን ጉዳዮች በተለያዩ መረጃ ማሰራጫ መንገዶች የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።
በጠቅላላው መረጃን የማግኘት መብትን በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 12 ላይ እንደሚከተለው ተደንግጓል፡-
- ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግስታዊ አካል መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት አለው፤
- በመንግሥት ተቋም የሚገኝን መረጃ የመመልከት፣ ማስታወሻ የመያዝና ግልባጭ የመውሰድ መብት አለው።
መረጃን ለሚድያ ተደራሽ የማድረግ ግዴታ
መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩት መረጃ የመንግሥትን የአሠራር ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና ውጤታማነት በመመዘን የመንግሥት አሠራርንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በመሆኑም የመንግሥት አካላት መረጃን ለመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። በመረጃ ነጻነት ሕጉ መረጃ የማግኘት መብትና መረጃን የመስጠት ግዴታን አስመልክቶ የሚከተሉትን ዓላማዎች ለማሳካት ሊተገበሩ እንደሚገባቸው በአንቀጽ 10 ስር ደንግጓል። እነዚህም፡- ሕግን መሠረት ያደረጉ ገደቦች እንደተጠበቁ ሆነው ማንኛውም መንግስታዊ አካል ዜጎች መረጃን ለመጠየቅ፣ ለማግኘትና ለማስተላለፍ ያላቸውን መብት ተፈፃሚ የማድረግ፤ መረጃ ፈላጊዎች መረጃዎችን በተቻለ ፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ ሳይደክሙ የሚያገኙበትን አሠራርና ስነ-ስርዓት በመመስረት መብቱን ተፈፃሚ የማድረግ እና የሕዝብ ተሳትፎን የሥልጣን ባለቤትነትን የማረጋገጥና እንዲሁም የአሠራር ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራርንና መልካም አስተዳደርን የማጠናከር ዓላማን መሠረት አድርጎ የሚተገበር ይሆናል።
መረጃን ለሚድያ ተደራሽ አለማድረግ የሚያስከትለው ተጠያቂነት
መረጃን ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ በግዴታነት መቀመጡ ብቻ በቂ አይሆንም። ግዴታው በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውልና እንዲፈፀም አስገዳጅ ሕግ ሊቀመጥለት ይገባል። ሰዎች በሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ከሚያስችሉት መንገዶች ዋነኛው ሕጉን በሚጥሱት ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት መጣል ነው። በያዝነው ርዕሰ ጉዳይ ላይም የመረጃ ነጻነት አዋጁ መረጃን ተደራሽ የማድረግ ግዴታቸውን በማይወጡት ላይ የሚከተለውን ቅጣት አስቀምጧል። በዚህም መሠረት ማንም ሰው መረጃ የማግኘት መብትን ለመጣስ በማሰብ ማንኛውንም ሰነድ ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ፣ የሰረዘ፣ የደበቀ፣ በተንኮል የከለከለ፣ ያፋለሰ ወይም ሀሰተኛ ሰነድ የሰራ በገንዘብ መቀጮ ወይም ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል (አንቀጽ 39(5))።
ማጠቃለያ
በጠቅላላው ማንኛውም ሰው በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ከማንኛውም አካል በዋናነት ከመንግሥት አካላት መረጃን የማግኘት እና የማሰራጨት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑንና የመንግሥት አካላትም መረጃዎችን ለሕዝብ በተለይም ለመገናኛ ብዙኃን በፍጥነት፣ በዝቅተኛ ወጪ ተደራሽ የማድረግ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ በመረጃ ነጻነት አዋጁ ሰፍሯል። አዋጁ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሕጉን በሚተላለፉት ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት የጣለ ስለሆነ የመንግሥት አካላት ይህንን ተገንዝበው በሕግ እገዳ ከተጣለባቸው መረጃዎች ውጪ ያሉትን በሙሉ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሕዝብ በተገቢው መንገድ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ