ሰላም ጤና ይስጥልን የፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ድረ ገፅ ተከታዬቻችን እንደምን አላችሁ! በዛሬዉ ፅሁፋችን የመገናኛ ብዙሀን ሀሳብን የመግለፅ ነጻነት እና ገደቦቹን፣መገናኛ ብዙሃንና የሚያከናውኑት ተግባራት፣ ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣የመገናኛ ብዙሀን ላይ ያሉ የተከለከሉ ተግባራት እና የሚስከትለው ተጠያቂነት እና ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ ጽሑፍ ወደናንተ ልናደርስ ወደናል፡፡
መረጃዉን ለሰጡን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከሆኑት ሳራ ሳሙኤል ስለሰጡን መረጃ ከወዲሁ እያመሰገንን አንብባችሁ ታተርፉበት ዘንድ ጋበዝን መልካም ንባብ!
በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ በእጅ ጽሁፍ ለሕዝብ ከሚደርስ መረጃ ተነስቶ በሬድዮ እና አሁን ባለንበት ዘመን በቴሌቭዝን ብሎም በበይነመረብ ደረጃ እያደገ የመጣ ሲሆን የመገናኛ ብዙሃን ማለት በየጊዜው የሚወጣ ህትመትን የብሮድካስት አገልግሎትን እና የበይነመረብ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የዜና ወይም የፕሮግራም አገልግሎት ለሕዝብ ለማቅረብ የተቋቋሙ አካላት ሲሆኑ መጻሕፍትን፣ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃንን፣ ጦማሮችን እና በየጊዜው የሚወጣ ህትመት አካል ያልሆኑ ፎቶ፣ ስዕልና ካርቱንን ሳይጨምር የዜና አገልግሎት ድርጅቶችን ያካትታል፡፡
የፕሬስ (የመገናኛ ብዙሃን) ነጻነት
ፕሬስ በሬድዮ፣ቴሌቭዥን እና በጋዜጣ ህትመቶች ሀሳብን የምንገለፅበት መንገድ ሲሆን ስለሚዲያ ነጻነት ሲነሳ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 29 የአመለካካት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብትን ዲሞክራሲያዊ መብት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ዜጎች ማናቸውንም ዓይነት ሀሳቦቻቸውን በተናጠልም ይሁን ተደራጅተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ በነጻነት እንዲገልፁ የሕግ ከለላ ይሰጣቸዋል። ማንኛውም ዓይነት አስተሳሰብ ያለ አንዳች ገደብ መንሸራሸር እንዲያስችል ህገመንግስቱ ሀሳብን በነጻነት የመያዝ መብት ከፕሬስ ነጻነት ጋር ያያይዘዋል፡፡ በህገመንግስቱም አንቀጽ 29(2) ስር ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡ ይኸውም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሀሳቦችና አመለካካቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነጻነት እና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል ሲል ደንግጎል፡፡
የሚዲያ ነጻነት ያለው ገደብ
ፕሬስ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደ እኛ ባሉ በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም እዲሉ የሚዲያ አጠቃቀም ዓላማውን ስቶ ጉዳት የማድረስ እድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው፡፡ በመርህ ደረጃ የመናገር ነጻነት በፕሬስ እንደተጠበቀ ሁሉ ይህን መብት ካስቀመጠ በኋላ በልዪ ሁኔታ ግን ለወጣት ደኅንነት እና ለሰዎች ሰብዓዊ ክብር ሲባል በነጻነት ሀሳብን የመግለፅ እና የማሰራጨት መብት ሊገደብ እንደሚችል ይኸው ህገመንግሥት ያስቀምጣል፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 29(6)ይህ መብት ገደብ ሊደረግበት የሚችለው ይህን ሕግ ተከትለው በሚውጡ ህጎች አማካኝነት ብቻ ሲሆን ገደቡም የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሆም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን በመከልከል በሕግ ገደብ ሊደረግ እንደሚችል ተድግጎ ይገኛል፡፡ የሕዝብ ጥቅም የመገናኛ ብዙሀን አዋጁ ሲተረጉመው ከግል ወይም ከጥቂት ቡድኖች የጥቅም ፍላጎት በተቃራኒ የማኅበረሰቡን የደኅንነት፣ የምጣኔ ሃብት፣ የባህል፣ የፖለቲካ እና መሰል ተፈጥሮ ያላቸውን ጥቅሞች ጨምሮ የሰፊው ሕዝብ ተጠቃሚነት ነው በሚል ይተረጉመዋል፡፡ በተቋሙ ወይም ተቋሙ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ሀሳቦችን በነጻነት ሲያንሸራሽሩ የወጣቱን ደኅንነት ሰብዓዊ ክብሩን የጦርነት ቅስቀሳ አይነት ይዘት ያላቸውን አመለካከቶች ላይ ያለውን ክልከላዎች ማየት እና መቆጠብ ተገቢ ነው፡፡ በህገመንግስቱ አንቀጽ 29(5) ደግሞ በመንግሥት ባለቤትነት ያላቸው ሚዲዎች የተለያየ ቋንቋ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ሲገልጥ ለዚህም ብዙ ቋንቋ በሀገራችን ያሉ በመሆኑ ሁሉንም ቋንቋዎች ለማሳደግ ካለ እሳቤ ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉትን መገናኛ ብዙሀን ኃላፊነት በይበልጥ ሚያሳይ ሲሆን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተጠሪነታቸው ለሕዝብ (ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም ወገኖች በእኩልነት የማስተናገድ ሕጋዊም ይሁን ሙያዊ ግዴታ አለባቸው።ይህ ግዴታ የብሄረሰቦችን የተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎች እና አመለካካት ያካተተ መሆን እንዳለበት በህገመንግስቱ በግልፅ ተደንግጓል፡፡
የመገናኛ ብዙሀን ላይ ያሉ የተከለከሉ ተግባራት እና የሚስከትለው ተጠያቂነት
በአዲሱ የመገናኛ ብዙሀን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ዓ.ም መሠረት የተከለከሉትን ዝርዝር ተግባራት መፈፀም የአስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃዎች እንዳሉት ተቀምጧል፡፡ አስተዳደራዊ እርምጃዎች በአዋጁ መሠረት በግልፅ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚያስወስድ ነው በሚል ካልተቀመጠ በስተቀር እርምጃ በዘፈቀደ መውሰድ እንደማይቻል አስረግጦ አስቀምጧል፡፡ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በገንዘብ እና ጥሰት የተፈፀመበትን ፕሮግራም ማገድ ወይም መሰረዝ ውሳኔ በቦርዱ ይሰጣል፡፡ በቦርዱ በሰጠው የመጨረሻ ዉሳኔ ላይ ቅር የተሰኘ ወገንም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ህጋዊ እርምጃን በተመለከተ በመሠረታዊነት መገናኛ ብዙሀን ሕግን አክብረው መገኘት እናዳለባቸው መሠረታዊ እሳቤ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ሀሳብን በነጻነት ከመግለፅ መብትን ባላጣበበ መልኩ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡አንዱ ህጋዊ እርምጃ የስም ማጥፋት ተግባር በፍትሐብሄር እንደሚያስጠይቅ ነው፡፡ከዚህ በፊት የነበረው የስም ማጥፋት በአዲስ መልክ የወንጀል ተጠያቂነት ቀርቶ ሲሆን የሥም ማጥፋት ተግባር በመገናኛ ብዙሀን ሲፈጸም ከፍትሀብሔር ኃላፊነት በስተቀር በወንጀል አያስጠይቅም በማለት በፍትሐብሔር የካሳ መክፈል ኃላፊነት ግዴታ ጥሏል፡፡ በብሮድካስት አገልግሎት ማንኛውም ኘሮግራም ወይም ዜና ኘሮግራሞች ወይም ዜናዎችን የተለያዩ አመለካከቶችን በማንፀባረቅ አጠቃላይ ሕብረተሰቡን እንዲያገለግል ሚዛናዊና ከአድሎዎ የፀዳ አድርጎ ማቅረብ፤ እና የሚሰራጨው ኘሮግራም ወይም ዜና ይዘትና ምንጭ እውነተኛና ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ አሠራጩ ሪፖርቱ ላይ ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ስህተት ሲገኝም እንዲያርም ይጠበቅበታል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን በቀረበ የፍሬ ነገር ዘገባ መልካም ስሙና ክብሩ በሐሰት ወይም በአሉታዊ ጎኑ ተጎዳብኝ ያለ ማንኛውም ሰው ዘገባው በቀረበበት መገናኛ ብዙሃን ላይ በተመጣጣኝና በተመሳሳይ ጊዜ በግልፅ ያለ ክፍያ እርማት የመጠየቅ አጠቃላይ መብት አለው፡፡ የሕዝብ ጥቅምን ለማስከበር ከሕገ መንግስታዊ የመናገር መበትን በንፅፅራዊ እይታ መርህ የሆነውን መሠረታዊ የሚዲያ ነፃነቶችን በማያሳጣ መልኩ ልዩ ሁኔታ እንደመሆኑ በጠባቡ የሚተረጎም ነው፡፡ ለዛም ነው በአዋጁ አንቀጽ 83(3) ሕጋዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ በሕግ መሠረት የሚከናወኑና ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን በማያጠብ መልኩ የሚተገበሩ መሆኑ፡፡ስለዚህ የመናገር መብት በመገናኛ ብዙሀን በሰፊው ሲንሸራሸር በመናገር መብት ሂደት ውሰጥ ሊታይ የሚገቡትን የግለሰቦች እና የህዝቦችን ጥቅም ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር የተቀመጡትን ግዴታዎች እና ገደቦች ባመጣጠነ መልኩ መሆን አለበት፡፡