ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

የሰው ልጅ በእለት ተእለት እንቅስቃሴው በርካታ ተግባራትን ያከውናል፡፡ በዚህ ሂደትም አለመግባባቶች ሊፈጠሩ መቻላቸው የገሀዱ አለም እውነታ ነው፡፡ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ሰዎች በራሳቸው ለመፍታት ጥረት ከማድረግ በተጨማሪ በራሳቸው ሊፈቷቸው ያልቻሏቸውን ጉዳዮች በሌላ ሶስተኛ ወገን እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ አለመግባባቶች ከሚፈቱባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ፍርድ ቤት ሲሆን ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ መሄድና መከራከር የሕግ እውቀት ይጠይቃል፡፡ በዚህም የፍርድ ቤት ሂደትን የማያውቁና የሕግ እውቀት የሌላቸው ደግሞ ለሕግ ባለሞያ (ጠበቃ) ገንዘብ ከፍለው መከራከር ይኖርባቸዋል፡፡ ለሕግ ባለሞያ ገንዘብ ከፍለው ለመከራከር አቅም የሌላቸው ሰዎች ደግሞ በራሳቸው ፍርድ ቤት ቀርበው የሚከራከሩ ሲሆን ክርክር በሚያደርጉበት ጊዜ በርካታ የሥነ-ሥርአት ግድፈት የሚፈጽሙ በመሆኑ መሠረታዊ የሆኑ መብቶቻቸውን ሲያጡ ይሰተዋላል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም ነፃ ሕግ ድጋፍ እንደመፍትሄ በሕግ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ነፃ የሕግ ድጋፍ ምንነትንና ተያያዥ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡

ነፃ የሕግ ድጋፍ ምንነት

ነፃ የሕግ ድጋፍ ወይም አገልግሎት ማለት በነጻ ወይም እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ የሕግ አገልግሎት የመስጠት ተግባር ሲሆን ይህ የሕግ አገልግሎት የምክር አገልግሎት፣ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጽሁፎችን ማዘጋጀት እንዲሁም ሌሎች የሕግ ማመልከቻዎችን በጽሁፍ ማዘጋጀት፣ ደንበኛን ወክሎ መከራከር፣ ማስማማት ወይም ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት እንዲታይ ማድረግ እና የመሳሰሉትን የሚያካትት ተግባር ነው፡፡

ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት

ነፃ የሕግ ድጋፍ በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶች አማካኝነት የሚሰጥ ሲሆን አገልግሎቱን ከሚሰጡ ተቋማት መካከል ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ጠበቆች ወይም የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም የሕግ ትምህርት ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር

ፍትሕ ሚኒስቴር በአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት ከተቋቋሙ አስፈፃሚ አካላት አንዱ ሲሆን በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/08 ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተሰጥተው የነበሩ ሥልጣንና ተግባራት ተላልፈውለታል፡፡ በዚህም በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(4)(ሠ) እና (ረ) መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር፡-

  • በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ክስ ለመመሥረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ወክሎ የመከራከር፤
  • የገንዘብ አቅም የሌላቸው የወንጀል ተጎጂ የሆኑ ተበዳዩች እንዲካሱ መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከጉዳቱ የተያያዙ የፍትሐብሔር ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እነሱን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ ማቅረብና እነሱን ወክሎ መደረደር እንደሚችል በግልፅ ተደንግጓል፡፡

በመሆኑም ፍትሕ ሚኒሲቴር የሕግ ባለሞያ ወይም ጠበቃ ቀጥረው መከራከር ለማይችሉ በተለይም ከላይ ለተጠቀሱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ ድጋፍ ወይም አገልግሎት በራሱ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት

ጠበቃ ወይም የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ነፃ የሕግ ድጋፍ ወይም አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑን የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀጽ 31 ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረትም ማንኛውም በጥብቅና ድርጅት ውስጥ ሸሪክ ሆኖ ወይም ተቀጥሮ የሚሰራ ጠበቃ ወይም በግሉ የሚሰራ ጠበቃ

  • የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች፣
  • ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ ለሲቪክ ማኅበራት፤ እና ለማኅበረሰብ ተቋማት፣
  • ፍርድ ቤት የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ለሚጠይቅላቸው ሰዎች፣
  • ሕግን፤ የሕግ ሙያን እና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ለሚሰሩ ኮሚቴዎች እና ድርጅቶች

እንደጉዳዩ ክብደት እና ቅለት እየታየ በትንሹ በዓመት ለሶስት ጉዳዮች የጥብቅና አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ነጻ የሕግ ድጋፍ የሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወይም ባለጉዳዮች መርጦ ለጠበቆች የመምራትና የመከታተል ኃላፊነት የፍትሕ ሚኒስቴር እንደሆነ በዚሁ አዋጅ ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ፍርድ ቤት (የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት)

ፍርድ ቤት የተከራካሪ ወገኖችን የክርክር ሂደት ከመምራትና ውሳኔ ከመስጠት በተጨማሪ በተለይ ጠበቃ ለመቅጠር አቅም የሌላቸው በወንጀል ተከሰው የቀረቡ ሰዎች ነፃ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ በሀገሪቱ ባሉ ፍርድ ቤቶች የሚቀጠሩ ተከላካይ ጠበቆች ያሉ ሲሆን እነዚህ ተከላካይ ጠበቆች በፍርድ ቤት ትእዛዝ በወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች ጥብቅና ቆመው እንዲከራከሩ የሚደረግ ሲሆን በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጥያቄ ሲያቀርብ ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምለት ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተከላካይ ጠበቃ የሚቆምላቸው ጠበቃ ለመቅጠር አቅም ለሌላቸው ለወጣት አጥፊዎችና ከባድ ወንጀል ፈጽመው ጠበቃ ቀጥረው መከራከር ለማይችሉ ወንጀል ፈጻሚዎች ነው፡፡

የሕግ ትምህርት ቤቶች እና የሞያ ማህበራት

ሌላው ነፃ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ የሕግ ትምህርት ቤቶቸ ሲሆኑ እነዚህ ተቋማት ፍርድ ቤት ላይ ቆመው ባለጉዳዮችን ወክለው መከራከር የማይችሉ በመሆኑ በአብዛኛው አገልገሎቱን የሚሰጡት በማማከር እና ክስና መልስ በመጻፍ ነው፡፡ ከሕግ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ አንዳንድ የሞያ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ለማሳያ ያህል ሴት የሕግ ባለሞያዎች ማህበር ለሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ ከሚያደርጉ ማህበራት መካከል አንዱ ነው፡፡

የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለማግኘት ወይም አገልግሎቱን እያገኘ ያለ ተገልጋይ በዋናነት መፈፀም ያለበት ተግባር ወይም ግዴታዎች

  • ተገልጋዩ ቀደም ሲል በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ይዞ መቅረብ የለበትም
  • ጠበቃ እንዲመደብለት የገንዘብ አቅም የሌለው ስለመሆኑ ትክክለኛና በምስክሮች የተረጋገጠ ማስረጃ ከሚኖርበት ቀበሌ ማቅረብ አለበት፡፡
  • ተገልጋዩ የሐሰት ጉዳይ ይዞ ወይም መብት ሳይኖረው ለጠበቃው ማቅረብ የለበትም:: ተገልጋዩ የደረሰበትን ጉዳይ ወይም ያጣውን መብት ለማግኘት ወይም ለማስከበር ያስችሉኛል የሚላቸውን ማስረጃዎች አሟልቶ ለጠበቃው የማቅረብ ግዴታ አለበት::
  • ተገልጋዩ ለጠበቃው ከሚያቀርበው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጠበቃው ሲጠይቀው የቻለውን ያህል ማስረዳት አለበት፡፡
  • ተገልጋዩ ከአገልግሎቱ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ነገር ግን ሙያዊ ያልሆኑ ስራዎች ማለትም የፍርድ ቤት መጥሪያ እና መልስ መስጠትና መቀበል፣ ትእዛዝ፣ የፍርድ ግልባጭ እና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን ለሚመለከተው ክፍል ማድረስና መቀበል አለበት፡፡
  • ከክርክር ጋር የተያያዙ ከፍያዎች እና ወጪዎች ማለትም የዳኘነት፣ የቴምብር ቀረጥ፣ የፎቶ ኮፒ እና የመሳሰሉት ወጪዎችን ነፃ የጥብቅና አገልግሎት ተጠቃሚው መክፈል አለበት፡፡
  • ከጠበቃው ጋር መልካም የስራ ግንኙነት የመፍጠርና ችግር ሲያጋጠም ተነጋግሮ የመፍታት ካልሆነ ግን ሁኔታውን ለፍትሕ ሚኒስቴር ማሳወቅ አለበት፡፡

ማጠቃለያ

ነፃ የሕግ ድጋፍ ገንዘብ ከፍለው የሕግ ባለሞያ (የጠበቃ) እርዳታ ማግኘት የማይችሉ ሰዎች ሕግ ባለማወቃቸውና ገንዘብ ከፍለው የባለሞያ እርዳታ ማግኘት ባለመቻላቸው መብቶቻቸውን እንዳያጡ በመፍትሄነት የሕግ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም የገንዘብ አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን በመጠቀም በሕግ ባለሞያ ድጋፍ እጦት ምክንያት ከሚደርስባቸው ጉዳት እራሳቸውን ሊጠብቁ እንዲሁም የጥብቅና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ያለባቸው አና ሌሎችም ይህን አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ ተቋማት ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ